Wednesday 16 December 2020

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፩)

 Please read in PDF

መግቢያ

እውነተኛ መድሎተ ጽድቅ ወይም የእውነት ሚዛን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። “መሠረቱ የጌታችንና እርሱ አድሮባቸው ቀድመው ትንቢት የተናገሩ የነቢያት በኋላም ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የተረጐሙና ያስተማሩ የሐዋርያት ትምህርት ነው። ከዚህ ውጭ አልተንቀሳቀሱም።”[1] ራሱ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ምንም ሊነጻጸርና ሊወዳደር በማይችል መልኩ አክብራና አልቃ የምታምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው” በማለት ቢመሰክርም፣ ለዚህ ታላቅ እውነት ግን ጸሐፊውም ኾነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተግባራዊ ምላሽ ሲሰጡ አይስተዋልም።[2]



መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፣ ካቶሊካውያኑ “… ኢትዮጵያን ከመንበረ ጴጥሮስ ለያችኋት” ለሚለው ወቀሳ በሰጡት መልሳቸው እንዲህ ብለዋል፤ “እናንተ ቁም ነገር አድርጋችሁ የያዛችሁት የጴጥሮስን ወንበር ነው፤ እኛ ግን ቁም ነገር አድርገን የያዝነው የጴጥሮስን ትምህርት ነው፤ ስለዚህ ጴጥሮስ ካስተማረው ትምህርት ወጥተን አንገኝ እንጂ ከወንበሩ በመለየታችን አናዝንም።”[3] በማለት፣ የጴጥሮስን ትምህርት መሠረት ዘወትር ሊይዙት እንደሚገባ ሲናገሩ፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ግን የጴጥሮስን ትምህርት ከመያዝ ይልቅ አዲስ ስሁት ሚዛን ማበጀቱን እንመለከታለን።

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው “መድሎተ ጽድቅ” ቅጽ ፩ በሚል ርዕስ፣ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በተባለ ሰው፣ በመጋቢት ፳፻፯ ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጠው ከክርስትና መሠረታውያን ትምርቶች አንጻር ምላሽ ለመስጠት ነው። መጽሐፉ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉትን የስህተት ግልጥ ትምህርቶች፣ በአዲስ መልክ አደራጅቶ ከማቅረቡ በዘለለ፣ እንደ ዘመነኛው ኑፋቄያት መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱሳት ዐሳቦቹን እንደገና የመተርጐም አደገኛ መንገድን ይከተላል። በዚህም ሳያበቃ አዳዲስ እንግዳ ትምህርቶችንም ይዞ ብቅ ያለ መጽሐፍም ነው። ስለዚህም በመጽሐፉ ላይ መልስን አዘጋጅ ዘንድ ባነሳሳኝ በጌታ መንፈስ በመታገዝ ሥራውን እሠራ ዘንድ እተጋለሁ።

በድጋሚ መናገር እንደምንፈልገው፣ “መድሎተ ጽድቅ” ብሎ ራሱን የሚጠራው መጽሐፍ፣ መድሎተ ስሑትነቱን በተለይም በሐዳስያን የተጻፉትን መጻሕፍት ተገን በማድረግ፣ ሙሉ ለሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በመሻር ወይም በመቃወምና የክርስቶስ ኢየሱስን ቤዛነትና ማዳን በማልኰስኰስ፤ በማክፋፋት፣ የቀደመውንና አምልኮተ ቅዱሳንን፣ አግንኖተ ቊሳትን [እንደ መስቀል፣ እመትና እምነትን ሌሎችም…] መልሶ በሰው ልብ ለማስረጽ፣ ከዐውድ ውጭ በኾነ ወይም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በተተረጐመ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም ማቅረቡንና ማደራጀቱን በአማናዊው ቱንቢ በመጽሐፍ ቅዱስ መትሮ፣ ቈርጦ ይለያል።

በርዕስነት “መድሎተ ስሑት ወይስ መድሎተ ጽድቅ” ለማለት የመረጥኹበት ምክንያትም፣ “መድሎተ ጽድቅ” የተባለው መጽሐፍ አማናዊውን መድሎተ ጽድቅ መጽሐፍ ቅዱስን ከመፈከርና በትክክል በዓውዱ ከመተርጐም ይልቅ የቅዱሳት መጻሕፍትን ዐሳብ እጅግ በማጣመም ስለ ተካነ፣ እንደ ስሙ እውነተኛ ሚዛን ከመኾን ይልቅ ስሑትነቱ በማድላቱ ምክንያት ነው። ይህንም ወደፊት በምናያቸው ርዕሳን ውስጥ፣ የመጽሐፉ ጸሐፊ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የማታምናቸውን እንግዳ ትምህርቶች በመጽሐፉ ውስጥ በማካተቱም ጭምር፣ ሥራው ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክል ሥራም እንደ ኾነ ለማሳየትም ነው።

በተለይ ዋና ትኵረታችን፣ የክርስትና ዋና ዋና ትምህርቶች ላይ ብቻ ነው። ለምሳሌም፦ ከ“መድሎተ ጽድቅ” ቅጽ ፩ መጽሐፍ ዋና ትኵረታችን ነገረ ድኅነት፣ የቅዱሳን አማላጅነት ስለሚባለው፣ ስለ ፍትሃትና ስለ በዓላት ነው። ሌሎችን እግረ መንገድ ከማንሳት በዘለለ ዋና ርዕሳችን አይኾኑም፤ ምክንያቱም ዋናውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ካስተማርንና ካጸናን ሌላው በዚያው ውስጥ መልስ ያገኛልና።

ምክንያተ ጽሒፍ

“የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ኾነን እንናገራለን።” (2ቆሮ. 2፥17)

ወንጌል ዋነኛ ዓላማው የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር መመሥረት ነው። መጥምቁ ዮሐንስና ጌታችን ኢየሱስ የስብከታቸው መጀመሪያ፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚል ነበር፤ (ማቴ. 3፥1-2፤ 4፥17)። መንግሥቱ ደግሞ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የኾነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም” (ሮሜ 14፥17)። ነገር ግን ለክርስቶስ ወንጌል የማይኖሩና የማይሠሩ ብዙዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት ሥራን ለግላቸው ወይም ትርፍን ሊያገኙበት ሲሠሩ እንመለከታለን።

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በጻፈው መልእክቱ፣ ይህን እውነት ፍንትው አድርጐ ያሳያል። ከቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ጀምሮ ብዙዎች ወንጌልን እንደ ንግድ ዕቃ በብልጣ ብልጥነት የሚሸቃቅጡት ለንግድና ለወረታቸው ትርፍ ብቻ ነው። ይህንም የወንጌልን እውነት በመቃወም፣ ከቅንነት ወርደው፣ በራሳቸው እየተመኩ፣ በትዕቢትና ክብራቸውን በመሻት ያደርጉታል። በተለይም ደግሞ እንዲህ የሚሸቃቅጡትና ወረታቸውን የሚያበዙት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እጅግ የራቁትን ይበልጥ በማራቅ፣ ተላላ ከኾኑት አማኞች ገንዘብን በመሰብሰብ ኑሮአቸውን ለማደርጀት ነው።

እውነተኛ አገልጋዮች ግን ይህን ፈጽሞ አያደርጉም፤ ምክንያቱም “ከእግዚአብሔር ተልከዋልና በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነው ቅዱሱን ወንጌል ብቻ ይናገራሉና።” በየዘመናቱ ግን በወንጌሉ ላይ የሚሸቅጡና ራሳቸውን ከወንጌሉና ከወንጌሉ ባለቤት ይልቅ እውነተኞችና ትክክለኞች አድርገው የሚያቀርቡ ሲነሱ ስንመለከት እጅግ እንደነቃለን። እንግዲህ “መድሎተ ጽድቅ”ም እንዲህ ያሉ መንገዶች ከሚከተሉት አንዱ ነው። የ“መድሎተ ጽድቅ” መጽሐፍ ከአማናዊው መድሎተ ጽድቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ራሱን የተሻለና እውነተኛ አድርጐ ማቅረቡን ስናይ ይበልጥ እንደነቃለን።

የዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ዓላማና ሥረ ምክንያቱ፣ “መድሎተ ጽድቅ” እርሱ ያቀረባቸውን አዳዲስ ትምህርቶችና ነባሮቹን ለማጽናት የተጠቀመባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሰጊግ (eisegesis)[ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጐም] ክፍሎችን እርሱ በተረጎመባቸው መንገዶች የተጠቀሱ አለመኾናቸውን ማሳየትና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛ ትምህርት ማጽናት፤ ማወጅ ነው። ስለዚህም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ በማድላት ሐሰቱንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሠራውን ሰጊጎታዊ(eisegetical) ሥራ እናፈርሳለን።

ይህ ሥራ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት ከመጠበቅ አንጻር ብቻ የቀረበ ነው፤ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ የአንዳንድ ሐዳስያንን ጽሑፍ ለመተቸትና ለመንቀስ እንደ ሠራ ቢናገርም፣ ነገር ግን እነርሱን ለመተቸት ብሎ የተላተመውና ፊት ለፊት የተጋጨው ከዘላለም በፊት ለሰው ቅንና ቅዱስ ከኾነው ከእግዚአብሔር ዐሳብና ጻድቅ ፈቃድ ጋር ነው። ከዚህም የተነሳ እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሠራውን የትኛውንም የስህተት ሥራ ስህተትነቱን ከማጋለጥ በዘለለ፣ እውነቱንም ጭምር በመናገር፣ “መድሎተ ጽድቅ” እንደ ስሙ ያይደለ፣ መድሎተ ስሑት መኾኑን እንገልጣለን።

   ሊዘነጋ የማይገባው እውነት፣ “መድሎተ ጽድቅ” ሃሳቦችን በማድፋፋት ወደር የሌለው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ሚዛናዊነትን ከመሳቱም በላይ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን[4] ሃሳብ ኾን ብሎ ያጣምማል፤ ለገዛ መንገዱ ብቻም ይፈክራል። ጌታችን ኢየሱስ፣ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።” (ማቴ. 22፥29) ብሎ እንደ ተናገረው፣ “የመድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ፍካሬና ሐቲቱ፣ ትርጓሜውና ትምህርቱ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመ አይደለምና ስቶ፤ ያስታል። እናም ደግመን እንላለን፣ ምካቴውን ስንሠራ፣ እጅግ የምናተኵረው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጣመም በሠራቸው ሥራዎች ላይ ይኾናል። ምንም እንኳ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጣመም የከረመውንና የደረተውን ትምህርት ለማጽናት እጅግ ቢጥርም፣ ነገር ግን የመንግሥቱ ወንጌል፣ “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ የሚያፈርስ፣ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ የሚማርክ” (2ቆሮ. 10፥5) እና ድል ነሺ እንደ ኾነ እናምናለን፤ እንታመናለን።

“ሳትሞት ሞተች ብለው ምንም ቢቀብሯት

    አትሞትም፤ አትሞትም፤ አትሞትም እውነት፤

እውነት የግዜር ገንዘብ እንደግዜር ባሕርይ

ዘላለም ሕያው ናት በምድር በሰማይ።”[5]

የ“መድሎተ ጽድቅ”፣ የሽፋን ምስል!

የ“መድሎተ ጽድቅ” የሽፋን ምስል፣ በአንድ በኩል የሐዳስያንን መጻሕፍት ሲያስቀምጥ፣ በሌላ በኩል ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ[6] የሚል ጽሑፍ ያለበት መጽሐፍ በሚዛኑ ሳይቀመጥ በሰው እጅ እንደ ተያዘ ያሳያል። ጸሐፊው ይህን ያደረገበትን ምክንያት ሲያብራራ፣ “የተሐድሶዎች ትምህርት የሌሎች ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አባቶችን ትምህርት ሳይጨምር፣ ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርትም ገና አንዱ መጽሐፍ ብቻ ወደ ሚዛኑ ብቅ ሲል የአንዱን መጽሐፍ ጥላ ያህል እንኳ ለመመዘን የማይችል መኾኑን የሚያሳይ ነው” ይላል።

የዚህ ዕይታ ስሑትነት በግልጥ ይታያሉ። እኒህም፦

1.   የትኛውም የስህተት ትምህርት ስህተትነቱ የሚመዘነው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። እንደ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ አፈራረጅ፣ የሐዳስያኑ መጻሕፍት በጠቅላላ የስህተት ትምህርት ነው ቢባሉ እንኳ፣ የሚመዘኑበት ሚዛን፣ የሚሰፈሩበት መስፈሪያ በእውነተኛው መድሎተ ጽድቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር፣

2.   የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኾነ፣ የሐዳስያኑ መጻሕፍት በቅዱሳት መጻሕፍት ሚዛንነት የሚመዘኑ እንጂ፣ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወይም የቅዱስ አትናቴዎስ ጽሑፎች እንደ መጻሕፍተ መለኮታውያት እንከን አልባ ናቸው ብለን ለመመዘኛነት አንቀበላቸውም፤ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኾነ የሌሎች ጸሐፍት መጻሕፍት ኹሉ በቅዱሳት መጻሕፍት ይመዘናሉ፣ ይንቀረቀባሉ፣ ይፈተሻሉ። ቤተ ክርስቲያንም ከጥንት እንዲህ እንጂ ከዚህ ውጭ አታምንም። እንዲያውም ለሃይማኖት ክርክር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ጠቅሶ መናገር እርሱ ራሱ መናፍቅነት፣ ኹሉን በእኩልነት እንዲዳኝ አንዲት ሥልጣን የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን መጋፋትና መቃወም ነው።

3.   የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ በአማናዊው መድሎተ ጽድቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊመዘን በሚገባው፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ የሐዳስያንን መጻሕፍት ለመመዘን ማሰቡ፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን የማይገዛ፤ ቤርያዊ ልበ ሰፊነት የማይታይበት (ሐ.ሥ. 17፥11) መኾኑን በግልጥ ያሳያል። እርሱ መናፍቃን የሚላቸውን ሐዳስያንን ቀርቶ፣ ጌታችን ኢየሱስ በሰይጣን በተፈተነ ጊዜ፣ ለሰይጣን እንኳ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንጂ ከአዋልድ መጻሕፍት አልጠቀሰም። ምክንያቱም ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ የየትኛውም ቅዱስ፣ ጻድቅ፣ መናፍቅ፣ የሰይጣንም ቃል ራሱ በቅዱሳት መጻሕፍት መመዘኑ ግድ ነውና። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ይህን የታመነ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ኾነ በዘመን መካከል ያልተዘነጋን እውነት ስቶአል።

ለአማኞች ግን እንዲህ እንላለን፣

      “አይዟችሁ በጎች አትደንግጡ - ይህን ሰርዶ ስትግጡ

ከዚሁ አለና በመንፈስ - እረኛችኹ የሱስ።

       ሰርዶውም ታሪክ የሚያጠግብ - ለሚግጠው ከልብ፤

                      አለልብ ግን መጋጥ - የበረሮ ፈሊጥ፤

       ወይም የምሥጦች ትምርት - መጣፍ ማበላሸት።”[7]

ይቀጥላል …



[1] አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ መግቢያ።

[2] ያረጋል አበጋዝ(ዲያቆን)፤ መድሎተ ጽድቅ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 38

[3] አድማሱ ጀንበሬ( መልአከ ብርሃን)፤ መድሎተ አሚን፤ ነሐሴ ፩ ፲፱፻፶፬ ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፳፬

[4] ከዚህ በኋላ “ቅዱሳት መጻሕፍት” ስንል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ማለታችንን አንባቢ እንዲያስተውል እንሻለን።

[5] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት

[6] ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ(John Chrysostom) ከ347-407 ዓመተ እግዚእ የኖረ፣ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ ነው። የሶርያ በኾነችው አንጾኪያ ከአረማዊ ግሪካዊ ቤተ ሰዎቹ የተወለደ ሲኾን፣ አባቱ በልጅነቱ ስለሞተ፣ እናቱ አንቱሳ(Anthusa) በወቅቱ ታዋቂ ከነበረው መምህር ሊባንዮስ ዘንድ በመውሰድ እንዲማር አደረገችው። እርሱም የንግግር ችሎታ (rhetoric) ሊማርበት ከገባበት ትምህርት ቤት ለግሪክ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ካለው ዝንባሌ የተነሳ ክርስትናንም ተቀበለ። ጥዑም በኾኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ስብከቶቹ፣ በነገረ ሥጋዌ ትምህርቱ፣ ለድኾች እጅግ ተሟጋች በመኾኑና ከልክ ያለፈ ብልጥግናን በመኰነን ይታወቃል።

[7] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት፤ ገጽ ፫

7 comments:

  1. ሐዋርያዊ መሰረትት እንደ መድሎተ ጽድቅ የተጠቀመ ማን አለ

    ReplyDelete
  2. የእነ ቅዱስ ዮሐንስ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስን ቅድስናቸው የተመሰከረላቸውና የአራተኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ተሻግሮ የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን ማስተማር የቻሉትን የሊቆቹን ያውም እንዳንተ ያልኖሩበትን ሳይሆን የኖሩበትን ህይወት የጻፉትን ካላመንክበትና ካልተቀበልክ ስለ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የመጻፍ ሆነ የተጻፉትን የመተቸት ሞራል የለህም አለቃዎችህ የሰጡህን ሳታላምጥ እየዋጥህ ወዲህ አታመንዥግብን።

    ReplyDelete
  3. .አይ አቢኒኒኒኒኒ

    ReplyDelete
  4. አሜን ፀጋ ይብዛልህ ❤ተባረክልኝ

    ReplyDelete
  5. አሜንንንንንን ተባረክልኝ

    ReplyDelete
  6. አይ ዲያቆን አየ

    ReplyDelete
  7. በአንድ ቤተክርስቲያን አባት ትምህርታችሁ ሲመዘን ምን እንደሆነ አየነዉ እኮ አስቀድመህ ሽፉኑን አይተህ መፀሄቶቹ ሲመዘኑ ባዶ መሆናቸዉን አየህ እንጂ ከፍተህ ብታነበዉ ትምህርታችሁ በመፀሀፍ ቅዱስ ሲመዘን በቀደምት አባቶች ስትመዘኑ ባዶ እንደሆናቹ በማስረጃ ያየንበት ነዉ እና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይሁንሎት 🙏🏽

    ReplyDelete