Tuesday 4 August 2020

ክርስቲያኖች ወደ ቄሳር ሲጠጉ እፈራለሁ!

  ለምንኖረው ሕይወትና ለማናቸውም የክርስትናችን የኑሮ ዘይቤ፣ ማዕከሉ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ያልተኖረ የሕይወት አብነት የለንም፤ የተኖረና በድል የተጠናቀቀ የሕይወት አብነት ግን አለን፤ እርሱም የክርስቶስ። ክርስቶስ ያልኖረውን ሕይወት ኑሩ አላለንም፤ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤” (ማቴ. 11፥28) ያለን ጌታ፣ “ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልናል” (1ጴጥ. 2፥21) ስለዚህ የማይጨበጥ፣ በንግግር ብቻ የሚተረክ፣ በተመስጦአዊ ስብከቶች የሚሰበክ ብቻ ያይደለ፤ የሚኖር፣ የሚሻተት፣ የሚቀመስ፣ የሚጣጣም ቅዱስ ሕይወትን ሰጥቶናል።

  ከኀጢአት በቀር፣ በእያንዳንዱ የሕይወት ዘይቤ፣ ክርስቶስ የተኖረ ሕይወት አለው፤ አንድን ድርጊትም ኾነ ዐሳብ ወይም ንግግር፣ እንዴትና በምን መንገድ ማድረግ እንዳለብን፣ እርሱ ያስተማረን ትምህርት እጅግ የሚመስጥ፤ ቅዱስም ነው። ጌታ ኢየሱስ፣ በዘመነ ሥጋዌው ከነበሩት የፖለቲካ መሪዎች ጋር ስለ ነበረው ግንኙነትና ስለ ቀረበለት ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ነገር አለው፤ ጥቂቶቹን ብንጠቅስ፦

የቄሳርን ለቄሳር!

  በአንድ ወቅት የሃይማኖት ሰዎች ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ፣ ተከታዮቻቸውንና የቤተ መንግሥት ሰዎች ሔሮድሳውያንን በአንድነት ወደ ኢየሱስ ላኩ፤ ስለ ተላኩት ሰዎች ጠባይ ወንጌላት ያስቀመጡት እውነት እጅግ አስደናቂ ነው፤ ማቴዎስ፣ የሰዎቹን የሽንገላ ንግግር ያስቀምጣል፤ ማርቆስ፣ የንግግራቸው ምክንያት ማጥመድ እንደ ኾነ ይነግረናል፤ ሉቃስ ደግሞ፣ የተላኩት ሃይማኖተኞችና የፖለቲካ ሰዎች ማንነታቸውን፣ “… ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት።” (ማቴ. 22፥15፤ ማር. 12፥13፤ ሉቃ. 20፥20) በማለት በግልጥ ይነግረናል።

  የጠየቁት ጥያቄ ስለ ግብር ነበር፤ ነገር ግን ወንጌላት የሰዎቹን ማንነት ከገለጡ በኋላ፣ ጌታ ኢየሱስም፣ በተንኰል ለማጥመድ የመጡበትን መንገድ ተመልክቶ፣ ግብር መክፈል እንደሚገባ በመናገር፣ ሃይማኖተኞቹንና ፖለቲከኞቹን በሕዝቡ ፊት ማጥመድ አለመቻላቸውን በማሳየት አሳፍሮ መለሳቸው (ሉቃ. 20፥26)።

ያቺ ቀበሮ

  በአንድ ወቅት ከፈሪሳውያን አንዳንዶች(ለኢየሱስ ቅርብ ይመስላሉ) ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ ገዢው ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ወጥተህ ሂድ አሉት፤ ጌታ ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ፦ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት።” (ሉቃ. 13፥32) አስተውሉ፤ የሄሮድስ ባሕርይ በኢየሱስ ንግግር እንደ ቀበሮ ነበር። ቀበሮ - ብልጣ ብልጥ ጠባይ! መጥምቁ ዮሐንስን በመግደል አቁሞ፣ ኢየሱስንም ከእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ በብልጠት ለማቆም የሚሻ ብልጣ ብልጥነት። ኢየሱስን ግን አንዳች የሚያስቆመው ኀይልም፤ ብልጠትም የለም።

“መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም!”

  ኢየሱስ በምድር ዘመኑ አንዴም እንኳ፣ ከቤተ መንግሥት ጥሪ ሳይደረግለት፣ በአገልግሎቱ የመጨረሻዎቹ ቀናት ግን የፊጥኝ ታስሮ በውርደትና በእንግልት፤ በገመድ እየተጐተተ ወደ ቤተ መንግሥት ከጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ጲላጦስም ዘብነን፤ ጅንን ብሎ፣ ኢየሱስ የእሱን ዓይነት ንጉሥ መኾን፤ አለመኾኑን ጠየቀው (ዮሐ. 18፥32)፤ ጲላጦስ፣ ዐሳቡ የአይሁድ መሪዎች እንጂ የእርሱ እንዳልኾነ ሲናገር፣ ኢየሱስ ግን ምድራዊ መንግሥት እንደ ሌለው ደፍሮ በመናገር ከጲላጦስ ጋር ያለውን ውይይት ዘጋው።

  በእርግጥ ኢየሱስ ንጉሥ ነው፤ ነገር ግን የኢየሱስ ንግሥና ጲላጦስ እንደሚያስበው፤ የሃይማኖት መሪዎችም በተንኮል እንደ ከሰሱት ያለች መንግሥት ኢየሱስ የለውም፤ መንግሥቱ የሰማይ ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት፤ አገዛዙም በጽድቅና በቅድስና ነውና፣ እናም ኢየሱስ ከዚህ ዓለም የኾነች መንግሥትም፤ ደም አፍሳሽ ወታደሮችም የሉትም!

“ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?”

   ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማያት ሊያርግ ባለ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እስራኤል ከሮማ ባርነት ነጻ ስለ መውጣት ጉዳይ ጠይቀውት ነበር፤ ልክ ዛሬ በአገራችን እንዳለው ቅጥ አልባ ሙግት ማለት ነው። ኢየሱስ ስለዚህ መልስ መስጠቱን መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች ነገር አይነግረንም። ኢየሱስ ጥያቄአቸውን ሳይመልስ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መስፋት ግን ደግሞ ደጋግሞ ተናገራቸው፤ (ሐዋ. 1፥6-9)።

  በጊዜው እስራኤል፣ በሮማውያን ቅኝ ትገዛ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ስለ ነጻይቱ እስራኤል አንዳች ነገር ያደርጋል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ምንም አላደረገም፤ መልስም አልመለሰላቸውም። በግልጥ ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ከኢየሩሳሌም ተነስታ እስከ ምድር ዳርቻ ኹሉ እንደምትደርስ በግልጥ ተናገራቸው። በእርግጥም ኢየሱስ የመጣበት ዋነኛ ዓላማው መንግሥቱ ነው!

ከቤተ መንግሥት ጥሪ ያልቀረበለት መሲሐዊ ንጉሥ!

 ደግሜ እላለሁ፤ ኢየሱስ በዘመኑ ከነበሩ ነገሥታት ወይም መሪዎች አንዳችም ጥሪ ወይም ግብዣ አልቀረበለትም፤ ከላይ በተመለከትናቸው ጥቂት ምሳሌዎችም፣ ኢየሱስም ሲጓጓ አንመለከትም፤ ወንጌላትም አይመሰክሩልንም፤ ኢየሱስ ግን ሞቱ ሲቀርብ፣ ወደ ቤተ መንግሥት ድህሪት ታስሮ እየተጎተተ ገባ፤ ንጉሡ መሲሕ፣ በምድራዊው ቤተ መንግሥት ተናቀ፤ ተዘበተበትም (ሉቃ. 23፥11)። ይህ እውነታ ዛሬም ቢኾን ይለወጣል ብዬ አላምንም፤ ልክ ኢየሱስ በሥጋ ከመሞቱ በፊት የሰቀሉት አይሁድ፣ ከሙታን መካከል እንደ ተነሣ ቢናገራቸው እንደማያምኑት እንዲሁ፣ ምድራውያን መሪዎችም፣ የኢየሱስ መንግሥት ይገባቸዋል ብዬ ፈጽሞ በመጠበቅ አልሞኝም።

  ኢየሱስ በምድር ሳለ አንዳችም ጥሪ ካልቀረበለት፣ ለእኛ የሚቀርብበት አንዳች ምክንያት አይኖርም፤ ኢየሱስ በተደጋጋሚ በሸማቂዎች ለተጠየቀው የፖለቲካ ወይም የአገር ነጻነት ጥያቄ፣ የመለሰው ልከኛና የእግዚአብሔር መንግሥት ከፍ ያደረገ እንደ ኾነ እንዲሁ፤ እኛም የእግዚአብሔርን መንግሥት አሳንሰን፣ ለምድራዊው መንግሥት አንፋለምም። ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ኖረ፤ የአባቱን መንግሥት አስቀደመ፤ ለአባቱ መንግሥትና ፈቃድ በሥጋው ሞተ፤ እንኪያስ እኛስ ለዚህ የተጠራን አይደለንምን? “መጠራታችሁን ተመልከቱ!” (1ቆሮ. 1፥26)

ማጠቃለያ

  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቀው ኢየሱስ፣ ሕይወትና ትምህርቱ አያጥበረብርም፤ ነገር ግን ባለንበት ዘመን፣ አብዛኛው የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ ፖትልኳል፤ ለጸሎት ከሚንበረከኩ እግሮች ይልቅ፣ ለፖለቲካ ዲስኩርና ሽሙጥ የሚባትሉ ምላስና ልቦች በርክተዋል። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ጌታ፤ መላለሙን የደገፈ አምላክ፤ ለእያንዳንዱ የሚጠነቀቅ መጋቢ መኾኑ፣ በኹሉም አማኞች የሚታመን አይመስልም፤ እንደ ፖለቲከኞቹ በመደገፍና በመቃወም ተጠምደናል፤ ከመገዛትና(ሮሜ 13፥1) ለመንግሥታት በጸሎት ከመማለድ ድርሻችን(1ጢሞ. 2፥1-2) ተዘናግተን፣ አጋፋሪዎች መኾናችን በጥቂቱ ያስደንቃል። ክርስቲያኖች በመደገፍና በመቃወም ከምንጠመድ፣ ለሚደገፉትም ተቃውሞ ለሚቀርብባቸውም መጸለዩ ይሻለናል፤ ለገነነው ክፋት አቅማችን ጸሎት፤ ጥረታችን ከተጠቁት ጐን መቆም ነው፤ እንዲህ ስናደርግ በጽድቅ ከሚፈርደው አምላክ ጋር በአጋንንት መንግሥት ላይ “ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣን” ነው!

ጸጋ ይትረፍረፍላችሁ፤ አሜን።  


2 comments: