Friday 12 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፮)

Please read in PDf

5.      ስቀሉን፦ ኀጢአተኛና የወደውን ዓለም ባለመናቅ፣ ኀጢአትን ፍጹም በመጥላትና በመጠየፍ፣ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን አንድያ ልጁን በመስቀል አሳልፎ ሰጠ። በአዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ የመስቀልን ትርጉሞችን ያስቀምጥልናል፤ በሌላ ንግግር የኀጢአት መገኘት፣ ፍርድና የኀጢአት ኃይል በተጠቀሰበት የአዲስ ኪዳናት ምንባባት ውስጥ ኹሉ፣ ነገረ መስቀሉ በአብዛኛው ተያይዞ እንደ ተጠቀሰ እናስተውላለን።


  የክርስትና ዋናና ማዕከላዊ ትምህርት ወይም መሠረተ እምነት ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ፣ ማመንና መቀበል ነው። በዚህም ትምህርቱ ሙሉ ለሙሉ በክርስቶስ ሥራ ላይ ብቻ እንድንደገፍና እርሱን ብቻ እንድንመለከት በጽኑ የሚያሳስብ ትምህርት ነው። ያለ መስቀሉ ወይም ያለ ክርስቶስ ሞትና ሕማም ክርስትና የለም፤ መስቀሉ ክፉ ከኾነው ከአሁኑ ዓለም፣ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን በመስጠት (ገላ. 1፥4) እኛን አድኖናልና።

 በመስቀሉ ያልተፈጸመ መገለጥ፣ ያልተፈታ ሕልም የለም፤ ከመስቀሉ ነጥሎ የሚቀርብ ትምህርትና ስብከት እርሱ የተሰቀለው ክርስቶስ ትምህርትና ስብከት አይደለም፤ መገለጥ፣ ትንቢት፣ ስብከት፣ ሕልም፣ ትምህርት መሠረቱና ዳርቻው መስቀሉ ነው። ከመስቀሉ በቀር ሌላ ርዕስ ለሕይወት አይመጥንም፤ መስቀሉን መስበክ የዘላለም ሕይወትን መስበክ ነው። መዘንጋት የሌለብን እውነት ጌታችን ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት ስለ መስቀሉ ሰብኮአል፣ ነቢያቱ እንኳ ኤልያስና ሙሴ በመጡ ጊዜ በክብሩ ተራራ ስለ መስቀሉ ተናግረዋል፤ በተሰቀለ ጊዜም መስቀሉን በብዙ ትእግስት ተቀብሎአል፤ ከስቅለቱም በኋላና ከሙታን ትንሣኤ በኋላ ስለ መስቀሉ ለኤማሁስ መንገደኞች ተናግሮአል።

   መስቀሉ አሮጌውን ሰው ሰቅሎታል፤ ዳግመኛ እንዳይኖርም ገድሎታል፤ አማኞችም ከክርስቶስ ጋር ሞተዋል፤ ከኀጢአት ኀይልና ኩነኔ፤ ከባርነትም ነጻ ወጥተዋል (ሮሜ 6፥18)፤ የክፋት ኀይላትም ተሸንፈውላቸዋል (ቈላ. 2፥14-15)፤ በሕግ ያገኘንን እርግማንንም ምትካችን ኾኖ ክርስቶስ አስወግዶታል (ገላ. 3፥13)፤ እንደ ሞተልን ለምናምን ኹሉ ፈጽሞ አድኖአል፤ ቤዛም ኾኖናል (ዕብ. 9፥28)፤ ኀጢአታችንን ፈጽሞ ስለ እኛ በመሸከሙን በሥራው ኹሉ አርፈናል (ኢሳ. 53፥12፤ 1ጴጥ. 2፥24)። ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች ለቅድስናና ለንጽሕና ተጠርተዋልና፣ ለዚህ ያበቃቸውን የእግዚአብሔርን ጸጋ መስቀሉን ፈጽመው ሊወድዱት፤ ሊገዙለት፤ ሊመኩበትም ይገባቸዋል።

   የሐሰት መምህራን ግን ይህን እውነት እናድናይ፤ እንድንወድ፤ ፍጹም እንድንከተለው አይሹም፤ ምክንያቱም ይህ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ፍጹም ያጣብቃል እንጂ ወደ ማንም እንድንመለከት አያደርግም። መስቀሉ የዳንበት ብቻ ሳይኾን፣ ዓለምንና መላውን ምኞቱን የናቅንበት መንገድ ነውና፣ ይህን ዓለም በመውደድና በባለጠግነት እሾኽ ነፍሳቸው ለታነቀች የስህተት መምህራን ይህ የመስቀሉ መንገድ ፈጽሞ ይኮሰኩሳቸዋል፤ አይመቻቸውምና አይሰብኩትም።
   ነገር ግን ለምን መስቀሉን አይሰብኩም? ብለን ብንጠይቅ፦

1.      ኑሮአቸውን ይቃወማል፦ የስህተት መምህራን ኑሮአቸው የተቀማጠለና ይህን ዓለም በመመውደድ የታጠረ ነው፤ መስቀሉ ደግሞ ለዚህ ዓለም በመግደል በክርስቶስ ሕይወት ሕያው የሚያደርግ ነው። ስለዚህም ኑሮአቸውን ይቃወማል።
2.     ከሚናገሩት ወንጌል ተቃራኒ ነው፦ መስቀሉ የሚኮሰኩስበት ሌላኛው ምክንያት፣ እነርሱ ከሚያስተምሩት ወንጌል በተቃራኒ በመቆሙ ነው። የእነርሱ ወንጌል ለመዳን ዋስትናው ብእላዊ ባለጠጋነት ነው፤ ክርስቶስ ግን በሰማይ ባለ ፍጹም ባርኮትና ባለጠግነት እንጂ ለምድራዊው ብቻ ነሁልለን እንድከተል በመስቀሉ ትምህርት አላስተማረንም።
3.     መሞትን አይፈልጉም፦ የስህተት መምህራን ከዚህ ዓለም ክፋትና መጎምጀት በመላቀቅ፣ መሞትን ፈጽመው አይፈልጉም። ለዚህ ዓለም ኖረው በዚህ ዓለም መሞትን በጽኑ ይሻሉ፤ ይህን በትምህርታቸው አንመለከትም ነገር ግን ሕይወታቸውና ኑሮአቸው ላስተዋለው ይህን በትክክል ይመሰክራል። መስቀሉ ያልቸነከረው አማኝ፣ ኑሮው፣ አምሮቱ፣ መጎምጀቱ፣ መቃጥኑ፣ መሻቱ በዚሁ ዓለም መኖርና መሞት ነው። ያልሞተውን አዳም መመገብና ማፋፋት ደግሞም ለእርድ ማስባት የስህተት መምህራን ተቀዳሚና ተከታይ ዋና ሥራቸው ነው።

  መስቀሉ ዋና ትምክህታችን ነው፤ ለአንዳንዶች ሞኝነት ለሌሎች ደግሞ ማሰናከያ ቢኾንም፣ መላው የክርስትና ዓለም ሺህዎች ዓመታትን የፈካውና ትውልድን የማረከበት መንገድ መስቀሉ ነው። እግዚአብሔር ማንም ወደ እርሱ እንዲመጣ የወደደው በመስቀሉ መንገድ በኩል ነው፤ ልጁ የሠራውን ሥራ በማመንና በመቀበል፤ ከዚህ መንገድ ውጭ በሌላ መንገድ መምጣት እግዚአብሔር የሠራውን መንገድ መናቅና ማቃለል ነው፤ የስህተት መምህራን ግን ከዚህ በተቃራኒ ናቸው፤ እኛ ግን መስቀሉን እንውደደው፤ እንከተለው፤ እንደ ሠረገላ ምቹ ከኾነውና ሰፊ ከኾነው ከስህተት መምህራን መንገድ እንጠበቅ፤ እንራቅም። ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

ይቀጥላል...

1 comment:

  1. GOD BLESS YOU I REALLY APPRECIATE YOU.KEEP IT UP YOU ARE EXCELLENT

    ReplyDelete