Saturday 20 June 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፰ - የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
8.   ምስክርነት፦ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ምስክርነት ከድፍረት ጋር በቀጥታ ተጠቅሶ እንመለከተዋለን፤ ሐዋርያት ሲጸልዩ እንዲህ ብለው ጸለዩ፣ “… ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው” በማለት፣ “ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።” (ሐዋ. 4፥29፡ 31)፤ አስቀድሞም ወንጌልን ይመሰክሩ የነበሩት በድፍረት፤ ያለ አንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ ነበር፤ (2፥29፤ 4፥13)።


   የአይሁድ ሸንጐ በአንድነት ተሰባስበው፣ ሐዋርያትን “ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው … ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው” (ሐዋ. 4፥17-18) በማለት፣ በብርቱ ማስጠንቀቂያ በማስፈራራት ማዘዛቸውን ይነግረናል። ነገር ግን ሐዋርያት ለሰሙት ዛቻ አንዳችም የፍርሃት ምልክት አላሳዩም፤ ይልቁን፣ “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።” (19-20)።

   ምስክርነት፣ መንፈስ ቅዱስን ስንሞላ፣ በእውነት ላይ ቆመን ፈጽመን በድፍረት የምንናገረው የአማኞች የዘወትር ሕይወት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በእስርና በእንግልት በነበረበት ወራትም ኾነ፣ በሰላም ጊዜ ወንጌልን ይመሰክር የነበረው በግልጥ ወይም በድፍረት ነበር፤ (ሐዋ. 19፥8፤ 26፥26)። ምስክርነት ላመንነው እውነት ዋጋ መክፈልና አለማፈርን ይጠይቃል። ለዚህም ነው ሐዋርያው፣ በድፍረት መናገር ይችል ዘንድ እንዲጸልዩለት አማኞችን የጠየቀው፤ (ኤፌ. 6፥19-20)። ሐዋርያት በግልጥ የሚመሰክሩት የማይኖሩትን ሕይወት አይደለም፤ የሚኖሩትንና የማያፍሩበትን፤ ደግሞም የተሰጡለትን ሕይወትና ትምህርት ነው።

    የስህተት መምህራን ግን እንዲህ አይደሉም፤ የመጀመሪያው እውነትን በግልጥ የሚናገሩ ቢኾኑ እንኳ፣ ነገር ግን በሥራቸው ይክዱታል፤ “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።” (ቲቶ 1፥16)። እውነትን የሚናገር ብቻ ምስክር አይደለም፤ ነገር ግን የሚናገረው ሊኖረው ይገባል፤ የሚናገረውን የማይኖር፣ እውነትን ብቻ ግን በግልጥ የሚናገር እርሱ ሐሰተኛ መምህር ወይም አገልጋይ ነው። ሐሰተኛ አገልጋዮች እግዚአብሔርን በፍጹም የሚክዱት በትምህርታቸው ብቻ ሳይኾን በሕይወታቸውም ጭምር ነው።

    ስለዚህ የሕይወት ምስክርነት ከሌላቸው አገልጋዮች መጠበቅ ይገባናል፤ አንዳንዴ ሰዎች፣ “ስለ ሥራቸው ምን ያገባናል?፤ ጌታ ላይ እንጂ ሥራቸው ላይ አናፈጥም” ይላሉ፤ ጳውሎስ በሥራቸው እንደሚክዱ የተናገረውን ቃል አናቃልል፤ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ፣ “ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” (ማቴ. 7፥20-21)።

   ለምን ይኾን፣ ብዙ ሐዋርያት ነን የሚሉ ባሉበት፣ አንድ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ የጠፋው?! ስተው የሚያስቱ ቢበዙ አይደለምን?!

9.   መሠረታዊ የክርስትና ትምህርቶችን፦ ሌላው፤ የስህተት መምህራን ለክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች ፈጽሞ ግድ የላቸውም። የስህተት መምህራን ኹሉም ሊያስብል በሚችል መልኩ ዶግማ ወይም ዶክትሪን የላቸውም፤ እንዲያውም “እንዲህ እናምናለን፤ ይህን ደግሞ አናምንም” የሚል አንቀጸ ሃይማኖት ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ትምህርቶችን አይከተሉም፤ እንደሚያምኑም ሲናገሩ አይሰሙም። ይህ የስህተት ትምህርቶቻቸው ልክ አልባና አያሌ እንዲኾን ያደርገዋል

  ለምሳሌ፦ በእግዚአብሔር ስለ ማመንና መታመን፣ የኢየሱስ ብቻ ጌትነት (ሮሜ 10፥9)፣ የቅዱሳት መጻሕፍት አይሻሬነት (ዮሐ. 10፥35)፣ የሰውን ልጅ ፍጹም ኀጢአተኝነት (ሮሜ 3፥10-12፡ 23)፣ በክርስቶስ ስለሚገኝ የዘላለም ሕይወት (ሮሜ 6፥23)፣ በእግዚአብሔር ወይም በወንጌል ስለ ማመን (ዮሐ. 14፥1)፣ ስለ ሙታን ትንሣኤ፣ ስለ ፍርድና የዘላለም ሕይወት እኒህና ከዚህ ጋር የተያያዙት ትምህርቶች የክርስትና መሠረተ እምነቶች ወይም ዶክትሪኖች ናቸው።

   የስህተት መምህራን እኒህን ትምህርቶች ማስተማር አይደፍሩም፤ ይልቅ ከእግዚአብሔርና ከልጁ መስቀል፣ ከዘላለም ፍርድና ሕይወት ይልቅ ከዚህ በሚያንስና የዘላለም ጉዳይ ባልኾኑ ነገሮች፣ ትምህርታቸውንና ልምምዳቸውን ሲመሰርቱ እንመለከታለን።

   አንዳንዶች ዶክትሪን አያስፈልገኝም፣ የማንንም ቤተ ክርስቲያን ዶክትሪን አያስፈልገኝም … እንደ ዋዛ ሲሉ እንሰማቸዋለን፤ ነገር ግን ይኸው ንግግራቸው እንኳ ዶክትሪን እንደ ኾነ የዘነጉት ይመስላል። ዶክትሪን በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረትነት ላይ ያለ የምናምነውን እውነት እንጂ፣ ቀንበር ወይም ሸክም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ይህን አምናለሁ፤ ይህን አላምንም የምትል እንጂ ኹሉን የምትቀበልና የምትከተል ነሁላላ አይደለችም።

   ለአንዳንድ ሰዎች ትምህርት ዕውቀት ብቻ ነው፤ እምነታቸውን ከትምህርት ጋር ማስተባበር አይፈልጉም፤ ትምህርታቸው ደግሞ ከእምነት ጋር አይገጥምም፤ በክርስትና ከርቱዕ ትምህርት መነቀል ከሕይወት መነቀል ነው፤ በርቱዕ ትምህርት መተከል ደግሞ በሕይወት መተከልና ማፍራት ነው። የስህተት መምህራን ለክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች ግድ የማይሰጣቸው፣ “የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ክደው” ስለሚያስክዱ ጭምር ነው፤ (1ጢሞ. 4፥1-2)።

   ስለዚህ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች፣ ታማኞች በመኾን ከስህተት መምህራን መጠበቅን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባንም፤ ምን እንደምንሰማ ካልተጠነቀቅን፣ የሰማነው ነገር የሕይወታችንን መሠረት፣ የአምልኮአችንን ልምምድ ጨርሶ ሊያናጋው ወይም ሊደመስሰው ይችላል። እናም ሐሰተኞች መሠረታዊ የክርስትና ትምህርቶችን እንደማያስተምሩ ወይም እንደሚያጣጥሉ መዘንጋት የለብንም።

ማጠቃለያ

   እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የጌታቸው የኢየሱስን ድምጽ በትክክል አጥርተው መስማት ይችላሉ። በበግ ካባ ተተግነው በተኩላነት ማንነታቸው የሚገለጡትን የስህተት መምህራን ደግሞ አጥርተው በመለየትም የታወቁ ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ … በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።” (ዮሐ. 10፥4-5)፤ እውነተኛ በጎች የሚያውቁት የእውነተኛውን እረኛ ድምጽ ብቻ ነው፤ የሌሎችን ድምጽ ለማወቅ፤ አዳዲስ ትምህርትና እንግዳ እውቀቶችን በማጋበስ አትድከሙ፤ የእውነተኛውን እረኛ ድምጽ ተገናኙት፤ ግላዊ የሕይወት ግንኙነት ይኑራችሁ፤ ልመዱት፤ እርሱን ብቻ በመከተል ዕረፉ፤ ተጽናኑም። ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛላችሁ፤ አሜን።
ተፈጸመ።

2 comments:

  1. እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የጌታቸው የኢየሱስን ድምጽ በትክክል አጥርተው መስማት ይችላሉ።

    ReplyDelete
  2. የሚሰማ የለም እንጂ የዘህ ልጅ መልክት በጣም ጥልቅ ነው

    ReplyDelete