Tuesday 18 August 2020

የመጽሐፍ ቅዱሱ ክርስቶስ - ክብሩና ሞቱ (ሉቃ. 9፥28-36)

  Please read in PDF

  በግርማ መለኮት የተፈራውና ማንም ሊቀርበው የማይችለው ጌታ፣ በክበበ ትስብእት በናዝሬት ከምትኖር ከአንዲት ድኻ ሴት ከማርያም ተወልዶ፣ በተዋረደው ዓለም በውርደት ተመላለሰ። ከመሰቀሉ በፊት ሰውን ሥጋ በመልበሱ ብቻ ተዋረደ። በበረት ከመወለዱ በፊት፣ በናዝሬት መንደር ከአንዲት ሴት ማኅፀን በማደሩ እጅግ፤ እጅግ ዝቅ አለ። ከኀጢአተኞች ጋር በመቈጠሩና ከእነርሱም ጋር በመዋሉ ደግሞ ኢየሱስ፣ ስድባችንን ኹሉ በመሸከም መስቀሉን በመላ ዘመኑ ታገሠ።

   ለደቀ መዛሙርቱ፣ የሰውን ልጅ ሰዎች ማን እንደሚሉት ጥያቄ ካቀረበላቸው በኋላ፣ በሳምንቱ ሊጸልይ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት በመያዝ ወደ ተራራ ወጣ። ምድር አይታ የማታውቀውን ክብር እንድታይ፣ የኢየሱስ ጸሎት ያስፈላጋታል፤ መልኩ ወደ ክብር ከመለወጡ በፊትም ኢየሱስ መጸለይ አስፈልጎታል፤ ኢየሱስ ስለ ጸሎት ያስተማረ መምህር ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ታዛዡ ልጅ በነበረበት፣ በዘመነ ትስጉቱ ኹሉ ዘወትር የሚጸልይ ሕይወቱና ትምህርቱ የተስማሙ እውነተኛ ነበር እንጂ። 

የመልኩ ወደ ክብር መለወጥ

   ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱ፣ የኢየሱስ መልክ በተራራው ወደ ክብር ሲለወጥ አዩ፤ ምክንያቱም ከስምንት ቀን ያህል በፊት፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፤ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ መስክረው ነበርና። የመሰከሩትን ሕያውና ዘላለማዊ እውነት፣ ግርማ መለኮቱን በመግለጥ እምነታቸውን ፍጹም አረጋገጠላቸው። የእግዚአብሔር ልጅ እርሱ ክርስቶስ እንደ ኾነ አመኑ፤ ያመኑትን እውነት አጸናላቸው፤ መጠራጠር እስከማይችሉት ድረስ ወደ ክብር ተለውጦ ራሱን አሳያቸው። እርሱ አምነው ለሚከተሉት ዘወትር እንዲህ ነው!

  ሥጋ የለበሰው ኢየሱስ፣ መልኩ ወደ ክብር በተለወጠ ጊዜ በሰማያዊ ክብሩ ታየ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ በፊታቸው ነጭ ኾነ፤ ልክ መልኩ ወደ ክብር በተለወጠ ጊዜ፣ ካንቀላፉት፣ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት መካከል የኾኑት ሙሴና ኤልያስ ከመሲሑ ጋር ሲያወሩ፣ ደቀ መዛሙርቱ ተመለከቱ። ሉቃስ ኹለቱ ነቢያት፣ ከኢየሱስ ጋር ያወሩ የነበረው ምን እንደ ኾነ ጽፎልናል፤ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።” በማለት (ሉቃ. 9፥31)።

   ኹለቱ ነቢያት ከኢየሱስ ጋር ያወሩ የነበረው ስለ ኢየሱስ ሞት ነው። ኹለቱ ነቢያት ሕዝቡን በኪዳን ከመምራትና ሕዝቡን ነጻ ከማውጣት አንጻር፣ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተዋል፤ ነገር ግን ሥራዎቻቸው ከፍጻሜ አልደረሰም፤ ስለዚህም ሕዝቡን ወደ አማናዊው ነጻነትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊያስገባ ስላለው እውነተኛ መሲሕ ይነጋገሩ ነበር። አማናዊው የዘፀአት ነቢይና መሪ ኢየሱስ እንደ ኾነ ይነጋገሩ ነበር። ይህንም የሚያደርገው ወደ ኢየሩሳሌም በመውጣት በሞቱ እንደ ኾነ ጭምር።

“በድጋሚ”፤ ስለ መውጣቱ ይነጋገራሉ!

    ዐሳቡ የኢየሱስን በቅርቡ መሞት አመልካች ነው፤ ፍጹም በኾነ ክብር ውስጥ የኢየሱስ ሞቱ ያልተዘነጋ ዋና ርዕስ ነው፤ እርሱ ካልወጣ ወይም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ካልሞተና ከሙታን መካከል ካልተነሣ በቀር፣ ሕዝቡ ከኀጢአት ነጻ አይወጣም፤ የሞትን ባሕር አይሻገርም፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም። ስለዚህም ለሕዝቡ ከኀጢአት ሕይወት ነጻ መውጣት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። የቀደመውን ሕዝብ በሙሴና በኤልያስ ነጻ ያወጣው ጌታ፣ አኹን ሕዝቡን ከኀጢአት ባርነት ያወጣ ዘንድ ፍጹሙን ነቢይ ወደ ምድር ሰደደልን።

   መላእክት ሲሰግዱለት ክብሩን ያየነው ጌታ፣ ክብሩ ውርደትና መቃብር፤ መሰቀልም እንደ ኾነ እንዲሁ አየን። ኢየሱስን ከመስቀል ለይተው ለመስበክና ለመነጋገር የሚሹ እነርሱ ይዋሻሉ፤ ንግግራቸውም ሐሰት ነው። ኢየሱስን ከመስቀሉ ለይተህ ልታሳየኝና ልታወራልኝ ከወደድክ፣ በእውነት አንተ ሐሰተኛ ነህ። ከጥንት እንደ ሰማን፣ የኢየሱስ መሲሐዊ ግርማ ከሞቱና ለአባቱ ፈቃድ ከመታዘዝ ጋር የተሰናሰነ ነው፤ መንግሥቱ ያለ ሞቱ አትመሠረትም፤ ነቢያቱም ያለ ሞቱ ሌላ አንዳች ወግና ንግግር፤ ጨዋታም የላቸውም። አልነበራቸውምም።

   እንኪያስ፣ እኛስ ከዚህ ከታላቁ ርዕስ በቀር ሌላ የሚበልጥ ምን ርዕስ፤ መነጋገሪያስ አለን?! ስለ ታላቁ ክብሩና ወደር ስለሌለው ግርማዊነቱ ባወራን ልክ፤ ሳንዘነጋ ሞቱንና ስቅለቱንም ጭምር እናወራለን፤ እንነጋገራለን፤ እንጨዋወታለን፤ እርሱ የነቢያት ኹሉ የጩኸታቸውና የትንቢታቸው መልስ ኾኖ ተገልጦአልና፤ ኀጢአተኞች ሆይ ደስ ይበላችሁ፤ ክብሩን የጣለውና ወደ ኢየሩሳሌም ለመሰቀል የወጣው መሲህ እናንተን ወደ ክብሩና ወደ ነጻነት መንግሥቱ ሊያወጣ ነውና።

ጸጋ ይትረፍረፍላችሁ፤ አሜን።


No comments:

Post a Comment