Sunday, 28 June 2020

የእምነት እንቅስቃሴ አገልጋዮች የክርስቶስን ዘላለማዊ ልጅነት አያምኑም!


(“የእምነት እንቅስቃሴ - የዛሬቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና”፣ ከሚለው መጽሐፍ ገጽ 61-63 የተወሰደ)
3.1.   ከአምላክነቱ ያልተነጠለ ልጅነቱን መካድ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ የተናገረውንና የተነገረለትን ልክ ለመለኮቱ እንደ ተነገረ ተቈጥሮ ሲካድ እንመለከታለን። ለዚህም እንደ ዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት፣ “የክርስቶስን ከዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ አለመኾኑን” ኹለት ሃሳቦችን በአንድነት በመስፋት ነው። እንዲህ በማለት፦


… አብና ወልድ … እኩል አይደሉም፤ አብ ወልድን ይበልጣል፤ … ገብርኤል እንዳለው ስሙ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ ከዛ በፊት አባታችን ነው፤ ሌላ ማስረጃ በዕብ. 2 ላይ “ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱም እንዲሁ በሥጋና በደም ተካፈለ፤ ማን ተካፈለ? አባታቸው። ስሙ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል በሚል የእግዚአብሔር ልጅ ብሎታል፤ ከዛ በፊት ልጅ አልነበረም ወይ? ልጅ አልነበረም፤ አባታችን ነው። አባትና ልጅ መሆንም አይችልም። … ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ልጅ ከነበረ ለዘለዓለም ከአብ ያንስ ነበር ማለት ነው። ምክንያቱም ሥጋ የለበሰው መች እንደ ኾነ እናውቃለንና፤ ሥጋ የለበሰው የዛሬ ኹለት ሺህ ዓመት ገደማ ከድንግል ማርያም በተወለደበት ጊዜ ነው ልጅ የኾነው። ያን ጊዜ “officially” [በግልጥ ወይም በይፋ ለማለት ይመስላል] እግዚአብሔር የነበረው ሥጋ ሲኾን፣ አብ ከእኔ ይበልጣል፤ ብታምኑስ አብ ከእኔ ይበልጣል ብሏል፤ አብ ስለሚበልጠው እንደውም በኹሉ ነገር ይጸልይ ነበር እንደ ማንኛውም ሰው፤ እርሱ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው ኢየሱስ ክርስቶስ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ከኾነ “some how” [እንደ ምንም] የኾነ ቦታ ተወልዷል ማለት ነው፤ …የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር አይደለም። [1] (አጽንኦት የእኔ)
በማለት።
 ኃይሉ ዮሐንስ በስብከቱ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ልጅ ከነበረ ለዘለዓለም ከአብ ያንስ ነበር ማለት ነው። … ሥጋ የለበሰው የዛሬ ኹለት ሺህ ዓመት ገደማ ከድንግል ማርያም በተወለደበት ጊዜ ነው ልጅ የኾነው።” ሲል፣ የተረዳው አረዳድ የመጽሐፍ ቅዱሱን ተቃራኒ አረዳድ ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነት ሲናገር፣ ከዘላለም እግዚአብሔር መኾኑን እንጂ ልጅነቱ የሚያንስ መኾኑን ለማመልከት የተናገረው አይደለም።
  የኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ልጅነት የሚያመለክተው የዘላለም አምላክ መኾኑን ነው። የዘላለም አምላክ ስለ ኾነ ነው፤  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ፤” (ዮሐ. 8፥58) በማለት በግልጥ የተናገረው። ከቅድስት ድንግል የተወለደው በእግዚአብሔር ዘንድ በአምላክነት ሳይለይ የነበረው ነው። ድንግል የወለደችው ፈጣሪዋን እንጂ ከእርሷ ከተወለደ በኋላ አምላክነትን ያገኘ አይደለም። “ሞኖ ጌኖስ” ተብሎ እርሱ ብቻ የተጠራውም፣ ከድንግል ሲወለድ ሳይኾን ከዘላለም ከባሕርይ አባቱ ዘንድ ሳለ ነው፤ (ዮሐ. 1፥14፤ 18፤ 3፥16፤ 18፤ 1ዮሐ. 4፥9)።
ቅዱስ ጳውሎስም የክርስቶስን በኵርነት ሲያስረዳ፣ ክርስቶስ መጀመሪያ የተወለደ እንጂ (Prototokos) መጀመሪያ የተፈጠረ (Protoktikos) መኾኑን አያስረዳንም፤ (ቈላ. 1፥15-16)። መጀመሪያ የተወለደ ስለ ኾነም ክርስቶስ የፍጥረት “በኵር” በመኾኑ፣ በፍጥረት ኹሉ ላይ መብትና ሥልጣን ያለው መኾኑን ያሳያል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር፣ “Prototokos”ን እንጂ “Protoktikos” አልተጠቀመም። በቈላስይስ መልእክቱ የተጠቀመውን ማየት በቂ ማስረጃችን ነው። በቈላ. 1፥15 ላይ “በሰማይና በምድር ያሉት ኹሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ኹሉ በፊት በኵር ነው፤ ኹሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤” በማለት ሲናገር የተጠቀመው “Prototokos”ን ነው። የዕብራውያን ጸሐፊም የሚጠቀመው ይኸንኑ ቃል ነው፤ (ዕብ. 1፥6)።
         የእግዚአብሔር አባትነት ለኹሉም እንደ ኾነ ከላይ ቢገለጽም የባሕርይ አባትነቱ ግን ተቀዳሚ ተከታይ ለሌለው ለአንዱ የባሕርይ ልጁ ብቻ እንደ ኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። እርሱም ከእግዚአብሔር አብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል የተገኘ (የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ) አንድያ ልጁ (ወልድ ዋህድ) ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ በቀር ሌላ የባሕርይ ልጅ የለውም። የእግዚአብሔር አብ አካላዊ ቃል የተባለ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር የነበረ በኋለኛው ዘመን እኛን ለማዳን ሰው የኾነ አምላክ ወልደ አምላክ ክርስቶስ ብቻ ነው።[2]
  ስለዚህ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነት የባሕርይ ልጅነትና ዘላለማዊ አምላክነትን የሚያመለክት ነው። እኛ ግን በእርሱ የተፈጠርን እንጂ የባሕርይ ልጆች አይደለንም። ኃይሉ ዮሐንስ የባሕርይ ልጅነትን በዚህ መንገድ ሲተረጉም እናየዋለን።[3] ጌታችን ኢየሱስ ከዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ በመኾኑ የሚያንስም አይደለም፤ እኩል የኾነ ነው እንጂ። ይህን የመጀመሪያዎቹ ሰሚዎች ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እግዚአብሔር ልጅነቱ ሲናገር ልክ እንደ እግዚአብሔር የኾነ አምላክ መኾኑን ተረድተዋል፤ (ዮሐ. 5፥18)።
(ለበለጠ ማብራሪያ መጽሐፉን እጋብዛችኋለሁ)


[1] https://www.youtube.com/watch?v=DaSXi8EKlKk&t=2s በሚል ሊንክ ላይ ቤተልሄም ታፈሰ፣ ከኃይሉ ዮሐንስ ጋር በExodus Tv፣ ተሾመ ዳምጠው ከኃይሉ ዮሐንስ ጋር ሲከራከርና በጋሻው ደሳለኝ በግል ካስተማረው ትምህርቶች በአንድነት ተቀናብሮ የተወሰደ ነው።
[2] ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ  70

6 comments:

  1. አሜንንንንንን ዘመን ይባረከ ዳርቻህን ያሥfaው

    ReplyDelete
  2. ጌታ ዘመንህን ይባርክ

    ReplyDelete
  3. ሰሚ ያጣ ጩኸት ቢደጋገምም ለውጥ አያመጣም ሁሉም በተረዳበት መረዳት ይመላለስ አንተም ነቃፊ ሆነህ እንዳትቀር ቼክ ዩር ሰልፍ

    ReplyDelete
  4. ክብርና ምስጋና ለዘላለም በዙፋኑ ላይ አልፋና ኦሜጋ ለሆነው ለንጉሱ ይሁን!አሜን


    ReplyDelete
  5. You are 'mind re newer'!!!! your message speaks directly to my soul.

    ReplyDelete