Wednesday 25 November 2020

በኢየሱስ የሚያፍሩ የማርያም ባርያዎች!

 Please read in PDF

መግቢያ

ተአምረ ማርያምን የስህተት መጽሐፍ ከሚያሰኘው እልፍ ነገሮች አንዱ፣ “ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ፣ የእመቤታችን ክብሯ ምስጋናዋ ሁሉ ተጽፎ ቢኾን ምን ብራና በቻለው ነበር፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እርስዋን አክብሯት ለእናንተ ለኀጥአን መድኀኒታችሁ ናትና …” የሚሉ ሐረጋትን በመጠቀም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናውቃት ከኢየሱስ እናት ማርያም በተቃራኒ፣ እንግዳና ልዩ የኾነችውን፣ አምልኮ ወዳድዋን ማርያምን ለመሳል በብርቱ በመጣሩ ነው። ይህ ላይደንቅ ይችላል፤ ነገር ግን ወንጌል ተረዳን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አነበብን፣ እንዘምራለን፣ እንሰብካለን፣ ዐሰረ ክህነት አለን … የሚሉቱ ከተአምረ ማርያም ያነሰ እውቀት መያዛቸው፣ ጌታችን ኢየሱስ በናዝሬት ሰዎች የተደነቀውን ያህል እኛም እጅግ እንደነቅባቸዋለን። አለማመናቸው በእውነት ያስደንቃል!

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ተሐድሶ ነበርን፤ እናም ተሐድሶዎች እንዲህና እንዲያ ናቸው፤ እኛ ግን “ወደ እውነት ተመልሰናል፤ ንስሐ ገብተናል፤ ወደ እውነተኛይቱ ቤታችን ተመልሰናል” በማለት ስለማያውቁት ዓለም ሲያወሩ በመስማቴ፣ ሰዎቹ ፍጥረትን በተሐድሶ የሚመራውንና ማለዳ ማለዳ አዲስ የኾነውን እግዚአብሔርን አያውቁትም፤ ደግሞም እውነተኛ ሐዳስያንን አያውቁም ለማለት ይህን ጻፍኹ።

ጥቂት ስለ መጽሐፍ ቅዱሷ ማርያም ጠባይ

1.   ለጌታ ብቻ ዘማሪ ናት፦ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቃት ማርያም እንደ ቅዱሳን ነቢያት አምላክዋን በዝማሬ ቅኔ የምታመሰግን ናት። ይህን ሉቃስ ወንጌላዊ አስፍቶ አምልቶ ጽፎልናል፤ እንዲህ ብላ መዘመርዋን፣ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና።” (ሉቃ. 1፥47-48)። ለድንግል ማርያም ሐሴትና ክብሯ ጌታዋና አምላክዋ ያህዌ ኤሎሂም ብቻ ነው። ሰዎችና ተአምረ ማርያም እንደሚሉት የራስዋ ደስታና ክብር ያላትም አይደለችም።

2.   መድኀኒትዋ ጌታ የኾነላት ናት፦ ተአምረ ማርያምና የማርያም ባሪያዎች እንደሚሉት ድንግል ማርያም እንከን አልባ፣ በደል የለሽ፣ መድኀኒት የማያስፈልጋት አይደለችም። ይልቅ ራስዋ በአንደበትዋ እንደ ዘመረችው አምላክዋ ብቻ መድኀኒት የኾናት ናት። አምላክዋን መድኀኒቴ የምትለው መድኀኒት ስለሚያስፈልጋትና ያለ እርሱም መድኀኒትነት መዳን ስለማይቻላትም ነው።

3.   ትሁት ናት፦ ድንግል ማርያም ከመልአኩ ጋር ስትነጋገር እጅግ ትሁት ነበረች። ትህትናዋንም ያልገባትን ነገር አብራርቶ እንዲነግራት መልአኩን በመጠየቅ አሳይታለች። እርሷ ወንድ ሳታውቅ መውለድ እንደማትችል ስትናገር፣ መልአኩ ግን በእርሷ የሚደረገው ነገር ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል መኾኑን በነገራት ጊዜ በትሁት ልብ አምና ተቀብላለች። የተአምረ ማርያሟ ማርያም ግን እጅግ ዐመጸኛ መኾኗን ተአምሯን ያነበበ ያስተውለዋል።

4.   የምትሳሳት ናት፦ ሉቃስ ወንጌላዊ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በጻፈልን ወንጌል ውስጥ፣ ማርያም በአንድ ወቅት ሰው ናትና በዝንጋኤ ስህተት እንደ ነበረች ይነግረናል። የፋሲካን በዓል ለማክበር ከልጅዋ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተውና በዓሉን አክበረው ሲመለሱ ማርያምና ዮሴፍ፣ ኢየሱስን “ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥” (ሉቃ. 2፥44)። ኢየሱስን ረስተውት ችላ ብለው ነበር። እናም እንደ ዋዛ የአንድ ቀን መንገድ ሄደው፣ ፈልገው ለማግኘት ግን ከዕጥፍ በላይ ሦስት ቀን ፈጀባቸው። እናም ፈልገው በሦስተኛ ቀን በመቅደስ ሲያገኙት፣  ማርያም እንዲህ አለች፣ “ … እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” ስትል፣ ኢየሱስ የማርያምን የስህተት ንግግር አረመ፣ “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” በማለት የዮሴፍን አባትነት ሳይቀበል ገፍቶ፣ የመቅደሱን ባለቤት የያሕዌን አባትነት ሲያጸና እንመለከታለን።

5.   የጌታን ቃል በመታመን የምትጠብቅ ናት፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ካረገ በኋላ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ሲጠብቁ ድንግል ማርያምም በዚያ እንደ ነበረች፣ “ … እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።” (ሐዋ. 1፥14) በማለት ይነግረናል። ስለዚህም እንደ መጀመሪያ አማኞች ተስፋውን ታምነው ከሚጠብቁት መካከል አንዷ እንጂ በብቃትና በቅድስና ከኹሉ የምትበልጥ መኾንዋን አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አይነግረንም።

ብዙዎች ቅድስት ማርያም ከተጻፈላትና ቃሉ ከሚለው በዘለለ መናገር ለምን እንደሚቀናቸው ግልጽ አይደለም፤ ምናልባት ባልንጀርነት ላለማጣት፣ በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶዎች ዘንድ ለመወደድ፣ የእንጀራ ገመዳቸው እንዳይበጠስ … ወይም በሌላ ምክንያት ሊኾን ይችላል። ነገር ግን ኦርቶዶክሳውን ራሳቸው በማርያም መታወቅን ልክ በኢየሱስ እንደ መታወቅ ከተመኩበት፣ ሊያፍሩና አንገት ሊደፉ ይገባቸዋል። ለቅዱሳን ለሐዋርያት እንዲህ ተነገረ፣ “ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤” (ሐዋ. 4፥14)። ሐዋርያት ከማርያም ጋር ቢኖሩም ወይም ማርያም ከሐዋርያት ብትኖርም፣ ደቀ መዛሙርት ግን በከሳሾቻቸው ፊት የታወቁት ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ብቻ ነው።

የዛሬዎቹ ግን ከማርያም ጋር መኾንን ወይም ስለ ማርያም በመዘመር መታወቅን ለምን ፈለጉ? እንደ ተአምረ ማርያም ንግግር የማርያም ባሮች መኾንን ለምን ፈለጉ? ሐዋርያት ያልተከተሉትን ፈለግ መከተል ለምን መከተል አስፈለጋቸው? በኢየሱስ ቢያፍሩ አይደለምን? ዳግማዊ ደርቤና አዱኛ ፍቃዱ እና ሌሎችም ለምን በኢየሱስ ስም መነቀፍና መሰደብን ትታችሁ ለማርያም በመዘመር የሰውን ክብር ፈለጋችሁ? አንድ ቀን በኢየሱስ ፊት ስትቀርቡ ታፍሩበታላችሁ!



ለማርያም የሚዘምሩቱ ማርያምን አያውቋትም!

ለማርያም የሚዘምሩ ጤናማ ባልኾነ ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የወጡ ናቸው፤ በምናባቸው የፈጠሯትና የሚሰብኳት ማርያም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጕመው (eisegetically) ያገኟት እንጂ የመጽሐፍ ቅዱሷን ማርያም ጨርሰው አያውቋትም። እኒህ ሰዎች አንዲት የሰይጣን መልካምነትን ቢያገኙ፣ ለሰይጣን እንኳ ከመዘመር የማይመለሱ ናቸው። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ለማትታወቀው ማርያም ከዘመሩ፣ አንዲት መልካም ቢገኝበት ለሰይጣንማ ብዙ መወድስ እንደሚያቀርቡ ጥርጥር የለበትም። ዳሩ ከተሰቀለው ኢየሱስ ይልቅ የሚኖሩለት ኑሮና ሆድ ስላላቸው ብቻ የምናባቸውን ማርያም ያመልካሉ።

በመጽሐፍ ቅዱሷ ማርያም እንኳ፣ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን ከእርስዋ በመወለዱ፣ የዝማሬ አምልኮ እንዲቀርብላት አያደርግም፤ እግዚአብሔር ይህን ሥራም የሠራው ከዘላለም ያቀደውን ዕቅዱን ለመፈጸም እንጂ ተአምረ ማርያም እንደሚለው ድንገት የማርያም መልካምነት ስቦትም አይደለም። በክርስቶስ ያዳነን፣ “ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ” ነው (ኤፌ. 1፥4)። ስለዚህም በዚህ ሥራ ውስጥ ማንም አልነበረም፤ አይኖርም፤ የለምም።

ማጠቃለያ

ብዙ አገልጋዮች ወንጌል እንደ ተረዱ ቢናገሩም፣ ማርያምን በተመለከተ ግን ገና ነጻ አልወጡም። ለማርያም መዘመርና የዝማሬ አምልኮ ማቅረብ ምንም ችግር እንደሌለው ሲናገሩም እንሰማቸዋለን። ለዚህም ሐዳስያንን በማርያም ለማስቀናትና ማርያምን በዝማሬ አለማምለካችን እንደ ስህተት ሲቈጥሩ እናያቸዋለን። ማርያምን በዝማሬ በማምለክ የራሳቸውን ሰዋዊ ትክክለኝነት ያሳዩናል። ደፍረን የምንናገረው እውነት፣ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር መኾናችንን ብቻ እንዲያውቁ ነው፤ ከኢየሱስ ጋር መኾናችንን ሰዎች ካወቁ፣ ከኢየሱስ ጋር ያለው ኹሉ ከእኛም ጋር ነው። ከኢየሱስ ጋር መኾንን የማይሻና ራሱን ከኢየሱስ ነጥሎ አመስግኑኝ፤ ዘምሩልኝ የሚል ግን እርሱ ጣዖት ነው። ማርያም ያመነች ብጽዕት ናት፤ ስለዚህም እንዲህ ያለ ጣዖትን እንደማትሻ እናውቃለን! እናንተ በጣዖት ፍቅር የተጠመዳችሁ ከጣዖታት ራቁ!

ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

 

 

12 comments:

  1. አቢዬ ተባረክ ወንድሜ በኢየሱስ ሁሉን ማጣት ማትረፍ እንደሆነ መረዳት ይሁን ዝማሪያችን ስብከታችን ኢየሱስ ስለሆነልን መነቀፍም በስሙ ስለሆነ ክብሩን እርሱ ብቻ ይውሰድ

    ReplyDelete
  2. ተዓምረ ማርያም የስህተት መጽሐፍ ነው ለማርያም ምስጋናን ማቅረብ ግን ስህተት የለውም። በጽሑፍና በቃል የምንለውን በዜማ ማለት ምንም ለውጥ የለውም።። አምልኮ የሚያሰኘው ነገር የለውም

    ReplyDelete
  3. ከጠላህ ሁሉንም ጥላ ከኦርቶዶክስ እ ዲያቆን ሚለውን አንሳ አታወናብድ ማህይሙ!

    ReplyDelete
  4. Abenezer teklu አንድ ነገር ልንገርህ ዳቆን ላንተ አይመለከትህም ሌላ ደግም ሰለ ድንግል ብንዘምር ምነው ጨጋራህን አስላጠህ ዘምርልኝ አላለችህ የሚዘምርላት አእላፍ ልጆች አለንላት ስለዚህ ከቻልክ ልብህ ተፀፅቶ ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትህ ተመለስ የጠፍትን የምትስበስብ ሰለሆነች በተመለሱት አትቃጠል ምን ታደርገው ያው አንተጋር የስፈረው ዲያቢሎስ ነው የሚያስቀባጥርህ

    ReplyDelete
  5. ክክክክ እይ መናፍቃን እንዴው የክህደት መርዛችሁን 1000 ጊዜ ብትረጩ ከእመቤታችን ፍቅርና ምልጃ ላታወጡን በከንቱ ባትደክሙ"ድንግል ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከጉሮሮየ ትጣበቅ"ቃሌ ነው። ለዘኢያፈቅረኪ እግዝዕትየ ውኩፈ ኢይኩን ጸሎቱ ወይጥፋ በከንቱ በአፈ መላእክት ወሰብእ ይትረገም ለእለ ሰዐቱ ዘአስተማሰሎ በተውኔት ለማህሌተ ንግስኪ ዝንቱ ጌጋዩ ወሀጢአቱ ኢተሀደግ ሎቱ።

    ReplyDelete
  6. ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ የሚለው እኮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት እያለ ያመሰግነኛል ከሚለው ጋር ያስማማል ኮ ወገናኖቼ.....ለምንድነው ግን መጽሃፍ ቅዱስን እንደ ፍልስፍና መጽሃፍ እንደፈለጋችሁ ምታደርጉት እስኪ ጥቅስ ከመሸምደድ እንዳባቶቻችን በጸሎት ትጉ ጸልዩ

    ReplyDelete
  7. ወንድሜ እግዚአብሔር ልቦና ይስጥህ ምስጢረ ስጋዌን በደንብ ሳይገባህ ለመተንተን ባትሞክር መልካም ነው ከዚያ በተረፈ ከጎን ያለችው ማረግ እስኪገባህ ድረስ ባትጠቀማት

    ReplyDelete
  8. (ራዕ.12፥17)፦ ዘንዶውም በሴቲቷ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።
    ፈጣሪ ልቦና ሰጥቷችሁ የአውሬውን አላማ ከማሳኪያነት ያድናችሁ...!!!!

    ReplyDelete
  9. ፓስተሩ አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህ የተአምረ ማርያሟ ማርያም በቤተ ክርስቲያን የሙሴ እህት ማለትም ዘማሪዋ ናት ያለህ ማነው የትስ መጸሐፍ አገኘአኸው ሲቀጥል ወላዲተ አምላክስ ማናት በእናንተ የእምነት ድርጅት ስለርሷ የምታውዋውን ልትነግረኝ ትችላለህ በመጨረሻም ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች ያለችውስ ማን እንደሆነች ልብ ብለህ አንብበኸዋል???? ስጠቀልልህ ባጭሩ ልቡናህን ይመልስልህ መረጃ ከማዛባት ይከልክልህ እላለሁ

    ReplyDelete
  10. እንግዲህ ተቃጠል አንተ ክፉ መንፈስ እኛም እንላለን ""ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ የእመቤታችን ክብሯ ምስጋናዋ ሁሉ ተፅፎ ቢሆን ምን ብራና በቻለው ነበር "" እልልልልልል አንቺን የሰጠን መድሀኒአለም ይመስገን

    ReplyDelete
  11. እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም ነጻ ያወጣል። እዉነት ደግሞ ክርስቶስ ነው። መጀመሪያ የመስቀሉ ስራ ያነሰባቸው አንዳንድ አይሁድ ያመኑትን ካልተገረዛችሁና የሙሴን ህግ ካልጠበቃችሁ አትድኑም እያሉ ያውኩ ነበር። ዛሬም እንክርዳድ ትምህርት አይናችንን ከክርስቶስ እንድንነቅል ይተጋል። መፍትኼው በመንፈስ ቅዱስ እገዛ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና እዉነት የሆነውን መቀበል ነው። ትህትና በሚመስል መንገድ የጥፋት ልድ የከበረውን ከአገሬ ቤተ ክርስቲያን ሰውሯል። ብርሐን ይሁን ጭለማው ይጥፋ።

    ReplyDelete
  12. HALLELUJAH MY LORD IS GREAT

    ReplyDelete