Saturday, 13 June 2020

ባላንጣዎቹ ደቀ መዛሙርት

Please read in PDF

ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የጠራቸው እጅግ ከተለያየ ቦታና ከተለያየ የሥራ ገበታቸው ነው። የአንዳንዶቹ ተግባራት ፈጽሞ የሚያቀራርባቸው ብቻ ያይደለ ደም የሚያቃባቸውም ጭምር እንደ ነበር ታሪካዊ ዳራዎችን ስናጠና ማስተዋል እንችላለን። ለዚህም በምሳሌነት ከአሥራ ኹለቱ መካከል ኹለቱን ደቀ መዛሙርት በማንሳት እንችላለን።

ከኢየሱስ ጥሪ በፊት

  ቅዱስ ማቴዎስና ቀናተኛው ስምኦን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠራቸው ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት መካከል ናቸው፤ ማቴዎስ የተጠራው ከቀራጭነት ቦታ ሲኾን (ማቴ. 9፥9)፣ ቀናተኛው ስምዖን ደግሞ በቅጽል ስሙ እንደ ተጠራው ቀናተኞች ከኾኑት አይሁድ መካከል ነው። ማቴዎስ አይሁዳዊ ቢኾንም ለሮማውያን ተቀጣሪ በመኾኑና ግብርን ከአይሁድ ተቀብሎ ለሮማውያም በመሰብሰቡ በአይሁድ ዘንድ ፈጽሞ የተጠላ ነው። የትኞቹም አይሁድ ለሮማውያን የሚሠሩ አይሁድን የሚመለከቱት እንደ ከዳተኛና ከአሕዛብ ጋር እንደሚተባበሩ ነው።


   ቀናተኞች ከ6 ዓ.ዓ በፊት በታላቁ ሄሮድስ ዘመን፣ በቀናዕያን (Zealot) አይሁድ የተጀመረና ብዙም ሳይቆይ በ70 ዓ.ም ጅማሬ ላይ ያከተመ ለእስራኤል ነጻ መውጣት የሚቀኑ አይሁዳውያን ማኅበር ወይም ቡድን ነበር። እኒህ ቡድኖች በዋናነት ለእግዚአብሔር ብቻ መገዛትና ለአረማውያን ግብርን መክፈል የለብንም በማለት አጥብቀው ተቃወሙ፤ ከዚህም የተነሳ በእስራኤል ምድር ይሰበሰብ የነበረውን የቀረጥና የግብር ሥርዓት ሰብሳቢዎችን ብዙ ጊዜ በመግደልና ከፍ ባለ ጥላቻ በመጥላት ይታወቁም ነበር፤ እንግዲህ ማቴዎስ በእስራኤል ምድር ቀረጥ ሰብሳቢና ግብር አስከፋይ ሲኾን፣ ስምኦን ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ከሚገድሉና አብዝተው ከሚጠሉ ቡድኖች መካከል የነበሩ ናቸው።

ከኢየሱስ ጥሪ በኋላ

    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቃራኒ መንገድ ላይ ያሉትን ኹለቱንም ደቀ መዛሙርት፣ አገልጋይ አድርጎ ሊሾማቸው በመንገዳቸው ፊት ለፊት ሄደ፤ በአስደናቂና ስፍር፣ ወሰን በማይገኝለት የምሕረቱ ባለጠግነት የማይስማሙትን፤ በደም የሚፈላለጉትን፤ ጨርሾ አንድ የሚያደርግ ነገር የሌላቸውን በአንድ ማዕድ፤ በአንድ ኅብረት፤ በአንድ መንፈስ፤ በአንድ መንጋ ውስጥ ይኾኑ ዘንድ ጠራቸው፤ የመጣው ለማይገባቸውና ፍጹም ኀጢአተኞች ለኾኑ ሰዎች ነውና። “ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል።” ተብሎ በትንቢት እንደ ተነገረ፣ ጌታችን ኢየሱስ በትክክል ለማን መቅናትና ማንን ማገልገል እንዳለባቸው ያውቁና ያስተውሉ ዘንድ፣ ፍጹም ዓመጸኞቹን ወደ መንግሥቱ ጋበዘ።

    ኹለቱ ተቃራኒ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ወደ ራሱ ከጠራቸው በኋላ፣ በመታመን ፍጹም ተከተሉት፤ ታዘዙትም። በዋለበት ዋሉ፤ ባደረበት አደሩ፣ ትምህርቱን ብቻ ያይደለ ሕይወቱንም ጭምር ወደዱት፤ ትምህርቱን ያደነቁትን ያህል ሕይወቱንም ፍጹም አደነቁ፤ ትምህርቱን ወደው ሕይወቱን የጠሉት አይደሉምና የቀደመ የበቀልና የጥላቻ ሕይወታቸው ከኢየሱስ ፍጹም የምሕረትና የቸርነት ሕይወት የተነሳ ዘነጉት፤ ተዉት፤ ረሱት፤ አንዱን የፍቅርና የምሕረት ጌታ፣ በፍጹም መዋደድ፤ በይቅርታና በርኅራኄ ተከተሉት።

መንፈስ ቅዱስ በወረደበትና የቤተ ክርስቲያን ልደት በተበሠረበት ዕለት፣ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ …” (ሐዋ. 2፥14)፤ እርስ በእርስ ለሞት ይፈላለጉ የነበሩቱ፣ ከጌታ ታላቅ ምሕረት የተነሳ አኹን፣ ለተገለጠላቸው፣ ላመኑት፣ ከኢየሱስ ለሰሙትና ለተማሩት እውነት ሳይፈሩና ሳያፍሩ አንድ ኾነው ለምስክርነት ቆሙ። እኒያ ባላንጣ ደቀ መዛሙርት በማይፈታ በጽኑዕ የፍቅር ገመድ ታስረዋልና አንድ ኾነው ቆሙ፤ ጎራነትና ልዩነት አበቃ፤ የኢየሱስ መንግሥት ኹሉን ጠቀለለ፤ ወረሰ፤ አንድ አደረገች።

ዛሬም የኢየሱስ እጆች ሕያው ናቸው!

   በአብያተ ክርስቲያናት፣ በፖለቲካው መድረክ፣ በብሔር መካከል፣ በቤተሰብ፣ በመንደሮቻችን ውስጥ አያሌ ባላንጣነት ተሰልፎ አለ፤ ማንም አይፈታውም የሚባሉ አያሌ ልዩነቶቻችን በምድራችን ዘመናትን ተሻግረው አሉ፤ የእኒህ ኹሉ ትብትብና ውል አልባ ባላንጣነቶች መፍቻው ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣትና ትምህርቱን ሕይወቱን ከቅዱሳት መጻሕፍት በመመልከት ማመንና መታዘዝ ነው። የቂም ልብ በኢየሱስ ይሽራል፤ የደመኝነት ልብ በኢየሱስ ደም ይጠራል፤ ልክ አልባ ጥላቻ በኢየሱስ ምሕረት ጸጥ ወዳለ ሰላም ይለወጣል።

   በኢየሱስ ትምህርት አንድ ከኾንን፣ ፍጹም ፍቅርና እውነተኛ መዋደድ ይታይብን፤ ኢየሱስን የሚከተል የቀደመ ቂሙንና ጥላቻውን ፈጽሞ የጣለ ነው፤ ኢየሱስን ቂምና ባላንጣነትን ሳንጥል መከተል አንችልም፤ ምሕረትና ይቅርታ ኢየሱስን ለሚከተሉ ኹሉ መገለጫቸውና መታወቂያቸው ነው፤ የኢየሱስ እጆች ዛሬም ሕያዋን ናቸውና፣ ለሚከተሉት ኹሉ አብዝቶ ሰጥቶአል፤ አትረፍርፎአልም፤ በደሙም አጽንቶአል፤ በትንሣኤው አረጋግጦአል፤ እንዲህ የተከተላችኹት ደስ ይበላችሁ፤ በምሕረቱና በይቅርታው የዋርካ ጥላ ሥር ያረፋችሁ ኹሉ ደስ ይበላችሁ፤ አሜን።

4 comments:

  1. desalegngizachew920@gmail.com

    ReplyDelete
  2. አሁን የአገራችን ህዝቦች ያሉበትን ሁኔታና መፍትሄውን የሚጠቁም ትምህርት ስለሆነ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክህ።

    ReplyDelete
  3. በጣም ትክክል ትምህርት

    ReplyDelete
  4. ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።

    ReplyDelete