Monday, 16 November 2020

“ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃ. 13፥5)

 Please read in PDF

  ሉቃስ ወንጌላዊው በቅዱስ ወንጌሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለመላለሙ የመጣ መድኀኒት” እንደ ኾነ በስፋት ይጽፍልናል (2፥14፤ 3፥3፤ 9፥52፤ 10፥33)። “ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያይ” ዘንድ ሰው ኹሉ ንስሐ ይገባ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ በየመንደርና ከተሞች እየተዘዋወረ ማስተማሩን ደጋግሞ ይነግረናል። “መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥” እንዲል፤ (ሐዋ. 10፥38)።

ሉቃስ በወንጌሉ ትኵረት ከሰጣቸው ትምህርቶች አንዱ ደግሞ ንስሐና የክርስቶስን ፍጹም ርኅራኄ ነው፤ በተለይም ደግሞ ማኅበረ ሰቡ ፍጹም ስላገለላቸው ኀጢአተኞች፣ ቀራጮች፣ ሳምራውያን (7፥36፤ 9፥52፤ 10፥33፤ 15፥1፤ 19፥5)፣ ከራሱ ጋር ለተሰቀለው ወንበዴ (23፥39) ክርስቶስ ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ እንዳሳየ ሉቃስ አምልቶ ይነግረናል። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ለኀጢአተኞች ያሳየውን ርኅራኄ በሚያስደንቅ ዕይታ፣ አንጀት ስፍስፍ በሚያደርግ መልኩ ገልጦልናል። ዛሬም ድረስ ይህ እውነት ፈክቶና ደምቆ መታየቱ እንዴት ይደንቃል!?

ተቃራኒው የሰው ልብ!

  ሰዎች ግን ክርስቶስ ኀጢአተኞችን የሚመለከትበትን ልብ አያስተውሉም፤ ክርስቶስ ወደ ሰው የመጣው ሰዎች የእርሱን ፍጹም ቅድስናና እንከን አልባነት በማየት፣ ኀጢአተኝነታቸውን በመጠየፍ ልባቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ ለማድረግ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ የነበሩት ሰዎች የሌሎች ሰዎች ኀጢአተኝነት ወይም የሰዎች በአደጋ መሞት ምክንያትን በማውጠንጠንና በመመርመር የተወጠሩ ነበሩ። ለዚህም ጌታችንን መጥተው የጠየቁትን ጥያቄ ማንሳት በቂ ነው።

  ሰዎች ራሳቸውን ጥፋተኛ ወይም ኀጢአተኛ እንደ ኾኑ ማሰብ አይፈልጉም። ነገር ግን ራሳቸውን መግለጥ በማይፈልጉት ልክ ሌላውን ሲኰንኑና ሲያልኮሰኩሱ ይታያሉ። ልክ ዛሬ እንደምናየው ብዙዎች የራሳቸውን የተገለጠውን ነውር ሳይኾን፣ ሲያወሩና ሲደሰኩሩ ውለው የሚያድሩት የሌላውን ክፋትና ዓመጽ ነው። ለጌታችን ኢየሱስ ያወሩለት፣ ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕት ጋር ስለ ደባለቃቸው ሰዎች ነበር፤ ሰዎቹ በቤተ መቅደስ መሥዋዕት በማቅረብ ላይ ሳሉ፣ ድንገት በጨካኙ ጲላጦስ እጅ ወይም ትእዛዝ የተገደሉ ናቸው፤ ይህን መጥተው ለኢየሱስ አወሩለት።

  ጌታችን ኢየሱስ ሌላ ምሳሌ ጨመረላቸው፤ እንዲህ ሲል፦ “በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን?” በማለት ጠይቆ፣ አለመኾኑንም መልሶ ተናገራቸው። ሰዎች ክፉ ነገር የሚገጥማቸው አንዳች ሽሽግ ኀጢአት ወይም ክፉ በደል ቢኖርባቸው ነው የሚል ጽኑ እምነት በብዙ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ዛሬም ድረስ አለ።

የጌታችን ትምህርት!

  ሰዎች ኹሉ ከጥፋታቸው ባይመለሱ፣ ክፋታቸውን ባይተዉ፣ ንስሐ በመግባትም የእግዚአብሔርን ምሕረት ባይለማመኑ[ጡ] ፍጻሜአቸው ሞትና ጥፋት መኾኑን ጌታችን ተናገረ። ሊመለሱ ባልወደዱ ኀጢአተኞች ኹሉ ላይ፣ የማይቀርና ፈጽሞ ሊያመልጡት የማይችሉት ፍርድ አለ። ሕዝብ ባለ መታዘዝ ሲጸና ትውልድ እንደሚመክን፣ ወንጀል፣ ድህነት እንደሚንሠራፋ፣ ክፋት እንደሚያገነግን፣ ድርቁናና የአየር መዛባት፣ ጭካኔና እንሰሳዊ ጠባይ እንደሚያገረሽ … በኦሪታዊው ኪዳን ውስጥ በጕልህ መንገድ ተቀምጦአል፤ ምንም እንኳ በአዲሱ ኪዳን እግዚአብሔር ምሕረቱን አለልክ ቢያተረፈርፍም በማይመለሱና በግብዝነት ጻድቃን መስለው የሚመላለሱትን ኀጢአተኞችን አይቀጣም የሚል ትምህርት ግን የለም።

  ይልቁን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አለማመን ቅጣቱ ሞትና የዘላለም ገሃነም ነው። ዛሬ ሰዎች ኹሉ በንስሐ ፊታቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲመልሱ የቆመ ሕያው የመስቀሉ መሥዋዕት አለ፤ ኀጢአተኞች ኹሉ ይህን አምነውና ታምነው ይመለሱ ዘንድ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የሚል የሚማልድ ድምጽም አለ፤ ስንቶች ሰምተን ለመመለስ ልባችንን ገርዘነው ይኾን? ሌላው ባገኘው ክፉ ነገር ከመመጻደቅ፣ ለራሳችን ንስሐ ለመግባት ፈቅደንና ታዝዘን ይኾን?! ጌታችን ኢየሱስ ሆይ፤ ጸጋና የንስሐ ልብን አብዛልን፤ አሜን።

 

 

2 comments:

  1. What a message of hope, blessing, God bless you abundantly.

    ReplyDelete
  2. ሰቆቃወ ኤርምያስ 3
    22፤ ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። 23፤ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።
    ተባረክ በብዙ

    ReplyDelete