መግቢያ
ስለ እሬቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምንሰማቸው ልዝብ አሳቦች አንዱ፣ “የኦሮሞ ባህልን የምናንጸባርቀበት ብቻ እንጂ አንዳችም አምልኮአዊ መልክ የለውም” የሚለው ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። ይህን ለማለት ያስደፈረው እውነታ ደግሞ በክርስትና ጥላ የተጠለሉ አያሌ ኦርቶዶክሳውያንና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት “አማኞች” እና ስለ እሬቻ ዘብ የቆሙ ሰዎች የሚያቀርቡት የተለሳለሰ ዐሳብ ነው። እሬቻን የሚያከብሩት ኦርቶዶክሳውያንና የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናት አማኞች፣ አምልኮአዊ መልክ እንዳለው ስለ ገባቸው ወይም ስለ ተጠራጠሩ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ “ባህላችንን እንወዳለን” የሚል አባባይ ምክንያት በመጥቀስ ለማስረዳት ሲንገታገቱ አስተውያለሁ።
ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ከአሥራ አምስት ያላነሱ በእሬቻ በአል ላይ የተገኙ
የተለያየ “ቤተ እምነት” ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችን እና በአሉን የሚያከብሩትን ዋቄፈታዎችን ለማነጋገር ሞክሬአለሁ፤ ኹሉም ግን “አምልኮአዊ
መልክ የለውም” ብለው ለመናገር አልደፈሩም፤ ሌሎች ደግሞ ለወንጌል አገልግሎት ስለሚጠቅም፣ በዚያ መካፈሉ መልካም እንደ ኾነ ከመናገር
በዘለለ፣ ተጠቅመውበት ወንጌል የሰበኩ እንደሌሉ ግን ተረድቻለሁ።
ዋቃ፣ ዋቄፈታ፣ ኢሬቻ፣ ኢሬፈታ
የእሬቻ በአል የሚከበረው በመላው የኦሮሞ ማኅበረ ሰብ ዘንድ ነው፤ የጥንት
ኦሮሞ በፍጥረት አምላክ በማመኑ ዋቄፈታ ይባላል፤ እምነቱም [Waaqa tokkicha Waaqumti beeku qofa] ራሱን የሚያውቅ አንድ አምላክ ብቻ ተብሎ ይጠራል።[1]
ይህ አንድ አምላክ ዋቃ ሲባል፣ ተከታዮቹ ደግሞ ዋቄፈታዎች ይባላሉ። ዋቃ ኹሉን የፈጠረ ነው። የሚታየውንና የማይታየውን፣ ቍሳዊ
የኾነውንና ያልኾነውን ፈጠረ። የተወሳሰበውንና የተራቀቀውንም ዓለም እንዲረዳዳ፣ እርስ በእርሱ እንዲጣበቅና እንዲፈላለግ አድርጎ
የፈጠረ ዋቃ ነው።[2]
ዋቃ አንድ ነው፤ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ወይም በተመሳሳይ ኹኔታ ደግሞ ብዙ
መኾን ይችላል። ስለዚህ በብዙ መናፍስት(አያናዎች) ራሱን ይገልጣል። በዚህም ዋቃ-አያና የሚል ምንታዌነት በውስጡ አለው። ይህም
አንዱ ብዙ መኾንን፤ ብዙው ደግሞ አንድ መኾንን የሚያመለክት ብዙ ምንታዌነትን በውስጡ የያዘ ነው። አንዱ በተመሳሳይ ሰዓትና ኹኔታ
ብዙ መኾን ይችላል፤[3] እንዲህ
ያለ እርስ በእርሱ የሚላተም ነገር፣ በጥንት ግብጾች የአምልኮ ክፍፍል ውስጥ ነበር።[4]
መዘንጋት የሌለብን ነገር በዋቄፈታ አማኞች ዘንድ ሰው ዋቃ ነው፤ ዋቃ ሰው አይደለም የሚለው ሙግት እልባት ያላገኘ ነው። አንዳንዶች
ዋቃ መንፈሱን የሰጣቸውና ዋቃን የሚረዱ ወይም ሥራውን የሚሠሩ ሰዎች አሉ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ዋቃ አይታይም፤ ሩቅ ነው የሚሉ አሉ።[5]
በኦሮሞ ወንዶች ዘንድ የጀግንነት ዝማሬ ከሚያሰጣቸው ነገሮች አንዱ ጎሽን በአደን ስፍራ መግደል ነው፤ ይህ ተግባር ጀግንነት
ብቻ አይደለም ሃይማኖታዊ ተግባርም ነው፤ እንዲህ እንዲያደርጉና አደኑን የሰጣቸው አያና(የዋቃ አካል) ነው፤ ስለዚህም ከእንሰሳው
ላይ ሥጋውን በማቅረብ ለአያና አምልኮ ይሰጡታል፤ ይህም ኢሬፈቹ ወይም “giving thanks” ምስጋና ማቅረብ ይባላል። እንግዲህ
እሬቻ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ሙሉ አምልኮአዊ ሥርዓት ያለው ነው።
በዋቄፈታ እምነት ውስጥ አምልኮውን የሚመሩት ሴቶች የሚኾኑበት ጊዜ ብዜ ነው፤ በተለይም “አቴቴ” ወይም “የእናቶች ጉባኤ” ተብሎ የሚጠራው የአምልኮ ኅብረት
ዋና ሥራው፣ ዋቃ ዝናምን እንዲሰጥ፣ በሽታን እንዲያስወግድ፣ የጠላትን ኀይል እንዲሰብር ወይም እንዲበትን የሚለምኑ ናቸው። እኒህ
እናቶች ይህን ለዋቃ አምልኮን ሲያቀርቡ የሚዘምሩት መዝሙር አላቸው፤ እጅግ ረጅም ቢኾንም፣ በጥቀቲ ግን እንዲህ አቀርበዋለሁ።
የአቴቴዎች መዝሙር
ለምሳሌነት ይጠቅመን ዘንድ፣ “የአቴቴ የእናቶች ጉባኤ” ዝማሬን ወይም በወሊድ
ጊዜ የሚቀርበውን የአምልኮ መዝሙርን መመልከት፣ እንዴት ባለ መልኩ ብዝሃ አምላክነት በባህሉ ውስጥ የተስፋፋና ከክርስትና የራቀ
እንደ ኾነ ማስተዋል ይቻላል። መዝሙሩ እነሆ፣
Ateetee Yaa
mi’ooftuu አቴቴ ጣፋጪቱ ሆይ …
Boroo keettan sii
dalagaa በቦሮው[6]
ሥፍራ አሸበሽብልሻለሁ
Galma keettan sii
sagadaa በቅድስተ ቅዱሳንሽ ሰግድልሻለሁ
Bakka ayyaani kee
boqotu መንፈስሽ በሚያርፍበት በዚያ …
Yaa obboleetti
daggalaa በዋሻው ወዳጅ የኾንሽኝ
Mee ungulaalii
dalagii በተገቢው ኹኔታ በጸሎት “ጨፍሪ”[አሸብሽቢ] …
Ililchituun hin
deessuu እልል ባይዋ አትወልድም
Yaa Maaram[7]
situ beekaa ማርያም ሆይ አንቺ ታውቂያለሽ
Geerartuun hin
ajjeeftuu እልል ባይ አትገድልም
Yaa Balas situ
beekaa ባላስ ሆይ አንተ ታውቃለህ …
Utuun Balasiin
ta’ee ምነው ባላስን በኾንኹ
Balasii Boongaa
ta’ee የቦንጋውን[8]
ባላስ
Dhabaadhaaf mirga
kenneen ለደካማው ኀይልን ሰጥቼ
Dhadhaa keessa
lolaaseen በቅቤ አጥለቅልቄው
Akka geeraru argaa እንዲፎክር
ባየሁት(ባደረግሁት)
Utuun Maaramiin
ta’ee ምነው ማርያምን በኾንኹ
Maaram Ateetee
ta’ee የአቴቴዋን ማርያም
Dhabduu dhaa ilma
kenneen ለመካኒቱ ልጅ ሰጥቼ
Fincaan keessa
ishee ciibsee … በሽርት ውኃ ውስጥ ባስተኛኋት…
ይህ “የእናቶች ጉባኤ” የሚዘምረው መዝሙር ዐሳቡ ግልጥና የማያሻማ ነው።
ለማን ምን ብለው እንደሚዘምሩም ማንም ሊያስተባብለው አይችልም። ማርያም፣ ባላስ፣ አቴቴ፣ ቦንጋ … የሚባሉና ሌሎችም አያሌ አማልክት
በዋቄፈታ እምነት ውስጥ የታጨቁ መኾናቸውን ይህ ጥቂት ማሳያ በቂ ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ነን የሚሉቱ “ባህል ብቻ እንጂ አምልኮ
የለበትም” ብለው ቢያቀርቡ ባያፍሩ እናፍርላቸዋለን፤ በእርግጥም በክርስቶስ የተገለጠውን እግዚአብሔርን እንደማያውቁ እንመሰክርባቸዋለን።
ዋቄፈታዎች ብዝሃ አማልክት አምላኪዎች
ናቸው
ለዚህ በኢሬቻና በማለዳ ጸሎት ውስጥ የተቀመጠውን፣ ከአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ
አንደበት የማይጠፋውን ቃል መጥቀስ መልካም ነው፤ “Tokkicha maqaa dhibbaa” ትርጉም፦ “አንድ ኾነህ አእላፍ ስም ያለህ” ማለት ነው። ይህ የሚያመለክተው
አንድ ዋቃ እና አእላፍ መንፈስ መኖሩን አመልካች ከመኾኑም በዘለለ፣ አንድ አምላክ አምልኮ(Monotheism) እና ብዝሃ አምልኮ(Polytheism)
አንድ ላይ የተሰፉበት መኾኑን እናስተውላለን። ይህን ደግሞ በአቴቴው አምልኮ በሚገባ ማስተዋል ይቻላል፤ በተለይም ዋቄፈታነት ብዝሃ
አምልክትን ተከታይ መኾኑን።
ዋቄፈታ
አምልኮ እንጂ ባህል አይደለም!
ልመና፣ መሥዋዕት፣ ጸሎት፣ ምስጋና፣ ዝማሬ፣ መወድስ … ይቀርብበታልና ዋቄፈታዎች
የሚፈጽሙት ኢሬቻ አምልኮ ነው፤ በውስጡ ባህል ብቻ የሚያስብል አንዳችም ትውፊት የለውም። አምልኮውም ደግሞ ከክርስትና ጋር የሚያያይዘው
አንዳችም ተዛምዶ የለውም። ምክንያቱም፦
1.
ዋቄፈታ በፍጥረት መገለጥ የቀረ እምነት ነው፦ በፍጥረቱ የተገለጠው እግዚአብሔር
ለአጠቃላይ ለፍጥረቱ መገለጡ እሙን ነው። ነገር ግን እንዲህ ባለ መገለጥ እግዚአብሔርን በትክክል ልናውቀው አንችልም። አያሌ ቤተ
እምነቶች[ይሁዲነትን ጨምሮ] በፍጥረት የተገለጠውን እግዚአብሔርን ያምናሉ። ነገር ግን በክርስቶስ የተገለጠውን እግዚአብሔርን አያውቁትም፤
አያመልኩትምም።
2.
ዋቄፈታ ወደ እውነተኛው መገለጥ አልደረሰም፦ ፍጹሙና እውነተኛው፤ የመጨረሻውም
መገለጥ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። እርሱ፣ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤” (ዕብ. 1፥1-2) እንዲል፣ በፍጥረት
የተገለጠው እግዚአብሔር በልጁ መገለጥ ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል፤ ክርስትና ይህን ያምናል፤ ይታመናል፤ ዋቄፈታና ኢሬቻ ግን ይህን
አያውቅም፤ አያምንም።
3.
ዋቄፈታ በመሥዋዕት የሚፈጸም አምልኮ እምነት ነው፦ ኢሬቻ በመሥዋዕት የወየበ እምነት ነው። የሚታረድ እንሰሳ፣ የሚያዝ ሣር፣ የሚጨበጥ አበባ፣ የሚደፋ
መጠጥ… አለው። ይህም እምነቱ በመሥዋዕት የሚፈጸም መኾኑን ግልጥ ማሳያ ነው። ነገር ግን ክርስትና በተጠናቀቀ መሥዋዕት እንጂ እንደ
ብሉይ ኪዳን የሚያቀርበው አንዳችም መሥዋዕት የለውም። ስለ ኢየሱስ እንዲህ ተብሎአል፣ “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ
ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ
ፈጽሞ አድርጎአልና።” (ዕብ. 7፥27)። አንድ ጊዜ ከቀረበው መሥዋዕት ውጭ ሌላ መሥዋዕት ለማቅረብ ማሰብ በዕብራውያን ጸሓፊ ንግግር፣
“የእግዚአብሔርን ልጅ መርገጥ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር መቍጠር የጸጋውንም መንፈስ ማክፋፋት” ነው፤
(ዕብ. 10፥29)፤ ኢሬቻና ዋቄፈታ ደግሞ፣ የክርስቶስን ፍጹም መሥዋዕትነት አይቀበልምና የክርስትና ተቃራኒ ነው።
4.
የትኛውም ባህል
የአምልኮ ሥርዓት የለውም፦ ኢሬቻ ባህል እንጂ አምልኮ አይደለም የሚሉ ወገኖች፣ ብዙ የምናውቃቸው
ባህሎች አምልኮና አምልኮአዊ ሥርዓቶች የላቸውም። ነገር ግን ደጋግመን እንደምንናገረው ኢሬቻ መሥዋዕት፣ የአምልኮ ሥርዓት፣ ባርኮት፣
ውዳሴ፣ ምስጋና … አለው። ስለዚህ ሊስተባበል የማይችል አምልኮ ነው።
ማጠቃለያ
ይህ እጅግ በጣም
ጥቂት እይታ፣ ዋቄፈታን ታክኮ የቆመው ኢሬቻ ከክርስትና እጅግ ሩቅ መኾኑን ያሳያል። “ባህል ነው” ተብሎ ማባበያም ሊቀርብበትም
የሚገባ አይደለም። ምክንያቱም በግልጥ በኹሉም ረገድ በብዝሃ አማልክትነት አምልኮ የሚቀርብበት እምነት ነውና። በክርስትና ትምህርት
ደግሞ እግዚአብሔርን የማያከብር ባህል፣ አምልኮ፣ ሥርዓት፣ ትምህርት፣ ፍልስፍና፣ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ … እና ማናቸውም ሃሳብና ተግባር
ኀጢአትና ዓመጽ ነው። እናም “ኢሬቻ በአል ሳይኾን ባህል ነው” የምትሉን
“የክርስትና ጭንብል አጥላቂዎች” ሆይ፤ አታዳክሙን፤ አታዝሉን፤ ክርስትና ቅይጥነት የለበትም። ክርስትና አብን በክርስቶስ የሚያመልክ
እምነት ነው፤ ከዚህ የወጣው ኹሉ ኀጢአትና ከክርስትና፤ ከዘላለም ጉዳይ የወጣ የሰው ትምህርትና ዐሳብ ነው።
ጌታ መንፈስ ቅዱስ እውነትን ማወቅና
ማስተዋልን፤ መታዘዝንም ያብዛልን። አሜን።
[1]
ስለ እሬቻ አምልኮአዊ ልምምዶች እያዘጋጀኹት ካለው መጽሐፍ የተወሰደ ትርጉም፡፡
[2]
Bartels, Lambert. Oromo religion: myths and rites of the Western Oromo of Ethiopia: an
attempt to Understand. 1983. Berlin. Kumsa Boro. Soothing the wounds of the nation: Oromo
women performing Ateetee in exile. 2009.London
[3]
Martha Kuwee Kumsa; Songs of Exile;
2013; Canada, Kitchener; Duudhaa Publishing; pp.72-74
[4]
Gadalla, Moustafa. Egyptian
Divinities: The All Who are the One. 2003. USA.
[5]
Martha Kuwee p.74
[6]
ቦሮ ከመኖሪያ ቤት ጀርባ ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል በክብር የሚዘጋጅ ሥፍራ
ነው፡፡
[7]
ማርያም ሴት አምላክ ስትኾን፣ ልጅን በመስጠት የምትባርክ እርሷ ናት፡፡ በዝማሬዎቹ
ውስጥ ማርያም አንዳንዴ “ማሬ፣ ማሪቱ” ተብላ በአክብሮትና በፍቅር ትጠራለች፡፡
[8]
ቦንጋና ባላስ የዱር መንፈስ ነው፡፡ እርሱም ለአዳኞች የአደን እንሰሳትን የሚሰጥና
የሚነሣ ነው፡፡ ልክ ማርያምና አቴቴ ወይም አቴቴዋ ማርያም ለሴቶች ልጆችን እንደምትሰጠውና እንደምትነሳው ማለት ነው፡፡ እናቶች
ባላስና ቦንጋን በተለማመኑት ጊዜ አዳኞች የአደን እንሰሳትን በማግኘት ይሳካላቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሴቶቹም ልመናቸው መመለሱ
የሚታወቀው በዱር እንሰሳት መገኘት ብቻ ሳይኾን ማኅፀናቸውም መለምለምና ምርታማ መኾን ይጀምራል ተብሎ ይታመናል፡፡
በጣም ያስደነግጣል
ReplyDeleteGod bless you for sharing. I can't wait for your upcoming book. May the LORD protect you and preserve you for his glory.
ReplyDeleteተባረክ
ReplyDeleteስህተታችንን የነገርክ የገሰጽከንም የወንጌል ጀግና ነህ!
ReplyDeleteአሜን አሜን ተባረክ
ReplyDeleteተባረክ!
ReplyDelete