Thursday, 22 October 2020

ፖፑን ምን ነካቸው?

 Please read in PDF

መግቢያ

የሮሙ ፖፕ ፍራንሲስ ያለፈው ማክሰኞ ግብረ ሰዶማውያን በአንድነት እንዲኖሩ መፍቀዳቸውን፣ ይህም የእግዚአብሔር ፈቃድ መኾኑንና እኛም ዕውቅና ልንሰጣቸው እንደሚገባቸው መናገራቸውን እየሰቀጠጠኝ ተመልክቻለሁ። ምክንያታቸውንም ሲያቀርቡ፣ “እነሱ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ግብረ ሰዶማውን የቤተሰቡ አባል የመኾን መብት አላቸው። … እኛ መፍጠር ለብን የሲቪል ማኅበራት ሕግ ነው። በዚያ መንገድ በሕጋዊነት ተሸፍነዋል። ለዚህም ቆሜአለሁ።”  በማለት ተናግረዋል።[1]



ፖፑ እንዲህ ያለውን ጸያፍ ተግባር ለምን በአደባባይ መናገር ፈለጉ? ምንስ ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ ፈልገው ይኾን? እጅግ ልብ የሚሰብርና የሚያደማ ጸያፍ ተግባር ነው።

ፖፑን በሙግት ቃል!

የትኛውም ኀጢአተኛ የእግዚአብሔር ፍጡር አይደለምን? ለግብረ ሰዶማውያን ማን የተለየ “የልጅነት ሥልጣን” ሰጣቸው? ቤተ ክርስቲያን ለየትኛውም ኀጢአተኛ አንዳች አድልዎ ሳታደርግ፣ ትማልዳለች፤ ትጸልያለች፤ ትማልላለች እንጂ አንዱን ኀጢአተኛ አቅርባ ሌላውን የምታርቅበት አንዳች መንፈሳዊም አመክንዮአዊም ምክንያት የላትም። እንዲያውም ፖፑ፣ ሰዶማውያን ኾን ብለው መንፈሳዊ የኾኑ ተቋማትን በመተናኰል ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ሳይታወቃቸው ቀርቶ ነውን?

ለግብረ ሰዶማውያን የተለየ ድጋፍ መስጠት ለምን አስፈለገ? ጫፍ የነካ ዓመጽ መኾኑን ሳይታወቃቸው ቀርቶ ነውን? ለምን ግን ነፍሰ ገዳዮችን አልደገፉም? ለምን በአደባባይ አደንጻዥ ዕጽ ደጋፊዎችን “እሰይ አበጃችሁ!” አላሉም? ለምን የሶርያን ምድር ደም መፍሰስ በቸልታ አለፉ? ስለ ምን በግሪክ ደሴቶች ስላሉ ስደተኞች መጠለያቸው መቃጠልና ሰቆቃቸው አንዳች ነገር ሳይናገሩ ሰዶማውያንን በአደባባይ ሊደግፉ ወጡ? … በእርግጥ ለምን ግብረ ሰዶማውያንን እንደሚደግፉ አንስተውም። እጅግ ዓመጸኞችና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ከመገዛት በመውጣት በእግዚአብሔር መንግሥት ለማመጽ ወደዋልና!

የሚያምጽም ያምጽ!

ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥” (ራእ. 22፥11) በዓመጽና በክፋት የሚጸኑ ሰዎች በደልና ኀጢአትን በመፈጸም ፍጹም ይጸናሉ፤ በደልንም በመጨመር ፍጹም ወደፊት ይቀጥላሉ። በሚያደርጉትም ዓመጽና ኀጢአት ንስሐ መግባትን አይወዱም፤ከሚፈጽሙት በደልና ነውርም የተነሣ ልባቸው ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ ይጠነክራል። ለኢየሱስ ቅዱስ ቃሎች ለመታዘዝ ባልወደዱ መጠን፣ አብ ዓለምን የወደደበትን ፍቅር ባላስተዋሉ መጠን፣ የመንፈስ ቅዱስን አብርሖት ለመቀበል ባልወደዱ መጠን፣ ለማይረባ አእምሮ ተላለፈው ይሰጣሉ።

ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ መሰጠት ለአሕዛብ ብቻ አይደለም፤ ይልቁን ጌታችን ኢየሱስን እናውቀዋለን ካሉ በኋላ፣ ወደ ኋላ በተመለሱም ዓመጸኞች ኹሉም ላይ እንጂ። “የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤” (ሮሜ 1፥23-24) እንዲል።

ነገር ግን በክርስቶስ የታመኑት፣ መልካምን፤ ጽድቅን፤ መንፈሳዊ ፍሬ ማድረግንና ማፍራትን ሊተዉ አይገባቸውም፤ እንዲያውም በጽድቅ መቀጠልና መበርታት ይገባቸዋል፤ “ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ።” (ዳን. 12፥10)።

ማጠቃለያ

“የተለጠውና የተነገረው የእግዝአብሔር ቃልና ትእዛዛቱ እውነትና ፈጽሞ ከሐሰት ጋር የማይስማማ ነው (2ሳሙ. 7፥28፤ መዝ. 118(119)፥86፡ 142፡ 160፤ ዮሐ. 17፥17) ስለዚህም የእግዚአብሔርን ቅዱስና እውነት የኾነውን ቃል ከሰው ሃሳብና አመክንዮ፣ ግምትና አመለካከት ጋር በመሸቃቀጥ ልናቀርብና ልንናገረው አይገባንም። የክርስቶስ ቃል ብቻውን የየትኛውንም የሰው ሃሳብና አመለካከት እርዳታ ሳያስፈልገው የሰውን ሕይወት መለወትና መቀደስ ይቻለዋል። በዚሁ በእርሱ ቃል ላይ አንዳች ቃል ብቻ ሳይኾን “እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴ. 5፥18) ተብሎአልና ሥርዓተ ነጥቡ እንኳ የሚሻር አይደለም።

በኀጢአት መጽናትና ከኀጢአተኝነት ጋር በግልጥ መስማማት ከማስተዋል መጉደል ነው፤ የዳንበት ጸጋ “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት እንክድ ዘንድ” እንጂ፣ እንተባበር ወይም እንደግፍ ዘንድ አይደለም። ፖፑን ጌታ ምሕረት እንዲደርግለት በጽኑ እንማልዳለን፤ በዚኹ የሚጸኑና የሚበረቱ ከኾኑ ግን ጳውሎስ እንዳስተማረን፣ “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዳችን ነው።” (1ቆሮ. 5፥5)። ጌታ ኢየሱስ ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ቤተ ክርስቲያንህን ጠብቅ፤ አሜን።


[1] https://www.wxyz.com/news/world/pope-francis-endorses-same-sex-civil-unions-for-the-first-time-as-head-of-catholic-church?fbclid=IwAR22StwaCvFLA3HBkzysHD94Tdw2D523xyqxXJakteqnKbK5xfOc7LHSKKc

[2] https://abenezerteklu.blogspot.com/2015/07/blog-post_20.html#more

4 comments:

  1. የሮምን ሚስጥራዊ ታሪክ ያጠና ከጥንት ጀምሮ የአውሬውን መንገድ እንደሚከተሉ ጠንቅቆ ያውቃል

    ReplyDelete
  2. ኢነሊላሂ ወኢነኢለይሂ ራጂዑን

    ReplyDelete