እንዲህ ነበርን!
አዳም “የመታዘዝን ፍሬ” ባለመብላት እንዲታዘዝ ቢነገረውም፣ እርሱ ግን የሰይጣንን ድምጽ ተከትሎ በመሄድና የተከለከለውን ወስዶ ከበላበት ቀን ጀምሮ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እርሱና ልጆቹ ሁሉ፣ እግዚአብሔር የተወን እየመሰለን አብዝተን ኃጢአትን ሠራን፤ ጨመርንም። ከዚህም የተነሣ፦
- እጅግ ኀጢአተኞች ኾንን፦ “… ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች
ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን
የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ
እነዚህ ነበራችሁ፤ …” (1ቆሮ. 6፥9-11)
እንዲል ኹላችን ይህን ኹሉና ከዚህ ጋር ተመሳሳዩን ኹሉ ነበርን።
የኀጢአተኝነት ዝንባሌ ከመጀመሪያው የተበላሸው፣ ሰው
ከእግዚአብሔር በመለየቱና በእግዚአብሔር ላይ በማመጹ ምክንያት ነው። ስለዚህም እጅግ ባለመታዘዝ እጅግ ኀጢአተኞች ኾንን። በዚህም
እግዚአብሔርን የምንመስልበትን መልክ አሳደፍን (ዘፍ. 5፥3)።
- በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ኾንን፦ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤” (ኤፌ. 2፥1)፤ የኀጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር
መለየት፣ እርሱ መንፈሳዊ ሞት ነው። ስለዚህም በኀጢአት የሞተ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ማድረግ እጅግ ይሳነዋል።
እኛ በኀጢአታችን ከእግዚአብሔር በመለየታችን እንኖር
የነበረው፣ በሞት ጥላ ውስጥ ወይም በሙታን በተወረረ የሙታን መንደር ውስጥ ነው። ይህ በመንፈሳዊው እውነት በቅዱስ ሚዛን ላስተዋለው፣
እጅግ አስከፊና መራራ ሕይወት ነው። ፍጻሜው ደግሞ ከተጣሉት መላእክት ጋር በአብሮነት መጣል፤ መተው ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር
በምሕረቱ ባለጠጋ ነውና እንደ ቸርነቱ መጠን ደረሰልን፤ አሜን።
- ያለ ክርስቶስም ነበርን፦ “በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ
በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።” (ኤፌ. 2፥12) እንዲል በኤፌሶናውያን
ላይ የወደቀው ወቀሳ እኛንም በቀጥታ ያገኘናል፤ ምክንያቱም በርግጥም እኛ መጀመሪያ ሕግንና ኪዳንን ከተቀበሉ ወገኖች መካከል
አልነበርንም፤ የኪዳኑም ተካፋዮች አልነበርንም፤ ከኹሉ ይልቅ ደግሞ እውነተኛውን አምላክ እግዚአብሔርን ባለማወቅ ያለ ክርስቶስ
ነበርን።
ያለ ክርስቶስ መኾን ከሕይወት መነቀል ነውና፣ ያለ
ክርስቶስ ምንም፤ ባዶዎች ነበርን። ያለ ክርስቶስ በነበርንባቸው ዘመናት ኹሉ ያለ ተስፋ በባዶ ነበርን፤ ክርስቶስንም ባለማወቅ ጥልቅ
ጨለማ ውስጥ ስንርመሰመስ ነበርን። ከዚህም ባሻገር እጅግ ርቀንም ነበርን (ኤፌ. 2፥13፤ 17)፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥
እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ፤ (መዝ. 103፣12)፤ አሜን።
- ጨለማ ነበርን፦ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤” (ኤፌ. 5፥8)። በአዲስ ኪዳን ምንባባት
ውስጥ፣ “ጨለማ” ከብርሃን ተቃራኒነቱ ባሻገር፣ ፍጹም ክፋትን ገላጭ ዐሳብ ነው፤ (2ቆሮ. 4፥6፤ 1ዮሐ. 1፥6)። ሰው
ኀጢአትን ባደረገ ጊዜ ብርሃንን የሚጠላ ኾነ፤ ጨለማን ደግሞ ወደደ፤ “ብርሃንም ወደ
ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ … ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥
ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤” (ዮሐ. 3፥19-20) እንዲል ጨለማነት የፍጹም ክፋት መገለጫነት ነው፤ ስለዚህም
ኹላችን እንዲህ ነበርን።
ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው፤ በኀጢአት ጸንቶ የሚኖር
ኹሉ የክርስቶስን ብርሃንነት በመቃወም በጨለማ ኀጢአት መኖርን የመረጠ ነው። በክርስቶስ የሚኖሩ ግን ከጨለማ በመውጣት በሚያስደንቅ
ብርሃን ውስጥ ይመላለሳሉ፤ አሜን።
ይቀጥላል…
amen amen amen
ReplyDelete