Wednesday 30 December 2020

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፫)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

·        ኀጢአት

በመጽሐፍ ቅዱስ ኀጢአት ወይም ኀጢአትን ማድረግ አንድና ወጥ ትርጉም ያለው ብቻ አይደለም፤ በተለይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአምስት በተለያዩ መንገዶች ተገልጦ እንመለከተዋለን፤

1.   ሃማርቲያ[ሺያ]፦ (ዒላማን መሳት)፦ ይህ ቃል በአዲስ ቃል ውስጥ ኀጢአት ወይም ኀጢአተኛ ተብሎ ከ250 ጊዜ በላይ ተጠቅሶአል፤ ትርጕሙም እግዚአብሔር ወዳቀደላቸው ዓላማና ግብ ኀጢአትን በማድረግ፣ በገዛ ፈቃዳቸው ወይም ምርጫቸው ባለመድረሳቸው አዳምና ሔዋን[የሰው ልጆች] ዒላማ መሳታቸውን የሚያመለክት ነው፤ እግዚአብሔር ወዳሰበላቸውና ወዳቀደላቸው ዐሳብና ክብር አልደረሱምና ከእግዚአብሔር ክብር ጎደሉ (ማቴ. 9፥2፤ ዮሐ. 1፥29፤ ሮሜ 3፥23)።


2.   አድክያ(ዐመፃ)፦ መሠረታዊ ዐሳቡ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ከሰጠን የሕይወት መሥፈርት ጋር አለመስማማታችንን የሚገልጥ ነው። በተለይም የሰውን በትክክለኛ መንገድ አለመሄድን የሚያመለክት ነው፤ “ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ …” እንዲል (ሮሜ 2፥8፤ 2ቆሮ. 7፥12)።

3.   ፓራፕቶማ(በደል፣ መተላለፍ)፦ ይህ ከእግዚአብሔር መንገድ መውጣትን፣ በራስ መንገድ መሄድን የሚያመለክት ነው፤ (ማቴ. 6፥14፤ ሮሜ 5፥15፤ ቈላ. 2፥13)።

4.   አኖሚያ(ዐመፅ)፦ ያለ ሕግ መኖር፣ ከሕግ ውጭ መኖርን ያመለክታል። በተለይም ቅዱሳት የኾኑት ትእዛዛቱን በመቃወም በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመን ዐመጽና ፍጹም አለመታዘዝን የሚያመለክት ነው።[1] ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ፣ “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው።” (1ዮሐ. 3፥4) እንዲል፤ በተጨማሪ 2ተሰ. 2፥7፤ ቲቶ 2፥14 ይመልከቱ)።

5.   ኦፋይሊቲስ (ባለ ዕዳ፣ ዕዳ[2] ወይም ግዴታ ያለበት)፦ ሰው የሚፈለግበትን ነገር ለመመለስ ወይም ለመክፈል የማይችል መኾኑን የሚያመለክት ዐሳብ ነው፤ (ማቴ. 6፥12፤ ሮሜ 15፥27፤ ገላ. 5፥3)።[3]

6.   ኃጢአት ውጫዊ ተግባር ብቻ አይደለም፦ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጣዊ ዝንባሌን፣ ኅሊናዊ ዕድፈትን፣ የልብን ዐሳብ ኹሉ “ኀጢአት” በማለት ይጠራዋል። “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” (ኤር. 17፥9)፣ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።” (ማቴ. 5፥28)፣ “እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ፦ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና።” (ሮሜ 7፥7)፣ “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ” (ገላ. 5፥24) እንዲል። እኒህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሰውን ውጫዊ ተግባር ብቻ ሳይኾን፣ ልቡ፣ ኅሊናው፣ ውስጣዊ ዕድፋዊነቱን ጭምር ገላጭ ናቸው።

እኒህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ተከትለን፣ አዳምና ሔዋን ኀጢአትን የሠሩት በኹለንተናቸው እንጂ በተወሰነ ማንነታቸው እንዳልኾነ እንረዳለን። የእግዚአብሔርን ጌትነት ንቀው በራሳቸው መጌይተይ ሲፈልጉ፤ ከእግዚአብሔር እቅፍ ወጡ፤ ተለዩ። ከዚህም የተነሣ ቅጣታቸው ሞት ኾነ። “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ …”፣ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤” (ሮሜ 5፥17፤ 6፥23) እንዲል።

በክፍል ፪ ላይ እንደ ተመለከትነው፣ በምሥራቃውያን የጥንተ አብሶ ዕይታ፣ ኃጢአት ኅሊናዊ እንጂ ባሕርያዊ ዕድፈትን የማያስከትል፣ እንደ ደንብ መተላለፍ፣ በደል የሚመለከቱትና ሰውንም የገጠመው የሞት አደጋ ብቻ እንደ ኾነ ተመልክተናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የገጠመን አደጋ ብቻ ሳይኾን፣ የባሕርይ ዕድፈትና ፍጹም ከእግዚአብሔር በመለየት ሞት ያገኘን መኾኑን በእርግጠኝነት ይናገራል። “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ … በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።” (ኤፌ. 2፥1፡ 12) እንዲል።

በሰው ልጅ ላይ የተጋረጠው አደገኛው መውጊያ ሞት፤ የኃጢአት ኃይል ነው (1ቆሮ. 15፥21)። ሞትን ያመጣው ደግሞ ከላይ ያየነው የሰው ልጅ የሠራው ኀጢአት፣ ዐመፃ፣ በደል፣ መተላለፍ፣ ዐመፅ፣ ብቁ ያለ መኾን ማንነቱ ጭምር እንጂ አንዱ ብቻ አይደለም። እንደ ምሥራቃውያን ደንብ በመተላለፉ ወይም በመበደሉ ብቻ፣ እንደ ምዕራባውያን ደግሞ ያለ ማመንን ኀጢአት በማድረጉ ብቻ ሳይኾን በደልና ኀጢአትን በኹለንተናዊ ማንነቱ በመፈጸሙ ወይም በማድረጉ  ነው።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ስለ ኀጢአት ትርጕም እንዲህ ይሳሳታል!

“በምዕራባውያን አስተምህሮ በአብዛኛው የመጀመሪያው በደል(ኃጢአት) የሚሉት አለመታዘዝ (Disobedience) ሲኾን በምሥራቃውያን (በኦርቶዶክሳውን) አስተምህሮ ግን የመጀመሪያው በደል አለማመን፣ ሕጸተ ሃይማኖት (Disbelief) ነው። አለመታዘዝ ያለማመን መገለጫና ውጤት ነው።”[4]

በማለት፣ ኀጢአትን አለመታዘዝ ብለው የተረጐሙት ምዕራባዊ አቀራረብ ያላቸው መምህራን እንደ ኾኑና፣ ትክክለኛ ትርጉሙ ግን የምሥራቃውያን ነው በማለት፣ ትክክለኛ ትርጉሙም “በእግዚአብሔር አለማመን ነው” ይላል። ሊቀ ጉባኤ አበራ ግን እንዲህ ይላሉ፣

“የመጀመሪያው በደልና ኃጢአት … ትእዛዝ የማፍረስ ኀጢአት ወይም ያለመታዘዝ ኃጢአት ሊባል ይችላል።”[5]

ኹለቱም ትርጕሞች ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖራቸውን፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ለማስተዋል የወደደ አይመስልም፣ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፦ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ …” (ሮሜ 5፥19) ሲል፣ ኀጢአትን አለመታዘዝ እያለው እንደ ኾነ ማንም አይስተውምና። በሌላ ስፍራ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ እንዳስተማረን፣ “ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤” በማለት ኀጢአት በእርሱ አለማመን እንደ ኾነ በግልጥ አስተምሮናል፤ (ዮሐ. 16፥9፤ በተጨማሪም መዝ. 51፥4፤ ሉቃ. 15፥18 ይመልከቱ)።

ጸሐፊው፣ ኀጢአትን እንዲህ የሚተረጕመው፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ኹለት ዓይነት ዕይታ ለማጽደቅ ነው፤ ዕይታው፣ በጥምቀት የሚሠረይ ኃጢአትና ከጥምቀት በኋላ የሚሠራ ኀጢአት የሚሠረይበትን መንገድ ለማመልከት ነው፤ በጥምቀት የጥንተ አብሶ ኀጢአት የሚሠረይ ሲኾን፣ ከጥምቀት በኋላ ግን የሚሠራው ኀጢአት በንስሐና በቁርባን ይሠረያል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ኀጢአት የኅሊና እድፈት እንጂ የባሕርይ ዕድፈትንና ጕስቁልናን አላስከተለም፣ እንዲኹም ደንብ በመተላለፋችንና የኅሊና ዕድፈት ብቻ ያገኘን በመኾኑ፣ “ለጥንተ አብሶአችን ክርስቶስ ሞቶአል፣ ዛሬ ለምሠራው ኀጢአት ምሥጢራትን መፈጸምና ኀጢአትን ለካህን መናዘዝና ብቻ በቂ ነው፤” ለሚለው ትምህርት ለማንደርደርና የምሥጢራትን ትምህርት ለማጽናት ነው። ትምህርቱ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመኾኑን በሚቀጥሉት ክፍሎች በስፋት እናትታለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን በመብላታቸው፣ ደንብ ተላልፈው ተቀጡ እንጂ የእግዚአብሔር ቊጣ አላገኛቸውም የሚል ትምህርት በምሥራቃውያን ዘንድ መኖሩን መዘንጋትም አይገባም። ነገር ግን አዳም ከገነት ቢወጣም እግዚአብሔር መሲሑን በመላክ የሰጠውን ተስፋ አጸና እንጂ፣ ፈጽሞ በመጥላትና፣ በመቆጣት ቊጣውን ሲያነድድ ለዘለዓለም አልኖረም። አዳም ከገነት የወጣበት ምክንያትም ኀጢአተኛ እንደ ኾነ ሺህ ዓመት እንዲኖር ሳይኾን፣ በመሲሑ ኢየሱስ ደም መፍሰስ ሕይወትን ያገኝ ዘንድ ወደደ።

ይቀጥላል …



[1] ሉውስ በርክኾፍ(ፕሮፌሰር)፤ የትምህርተ መለኮት ጥናት፤ 1989 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ 111

[2] ዝኒ ከማኹ ገጽ 111

[3] ፤ ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ ገጽ 62-63

[4] ያረጋል አበጋዝ(ዲያቆን)፤ መድሎተ ጽድቅ ገጽ 86

[5] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 89

5 comments:

  1. ብዙ ጊዜ ተነግሮት የማይሰማ ማስተዋል የሌለው ወይም ማስተዋል የጎደለው ንስሀ የማያውቅ ከክፋቱ የማይመለስ ዲያቢሎስና የግብር ልጆቹ ብቻ ናቸው መናፍቃን ድሮ ስናውቃቸው ያደረባቸው ርኩስ መንፈስ ያፈራግጣቸው ያንፈራፍራቸው ነበር አሁን አሁን ግን ወደ ማያቋርጥ ልፍለፋ አሳድገውታል ወደ ቀደመው ማስተዋል ይመልስልን

    ReplyDelete
  2. በጣም ግልጽ የሆነ ትምህርት ነው ተባረክ

    ReplyDelete
  3. ለማወናበድ ፈልገህ እንደሆነ ግልፅ ነው

    ReplyDelete
  4. በሃይማኖታችን አስተምህሮ መሰረት ማንኛውም አዋልድ መጽሐፍ ከመጽሃፍ ቅዱስ እንደሚያንስ የተወቀ ነው ። ነገር ግን ይህን ያክል የሃይማኖት መረዳት ካለህ ፤ ከትችት በፊት ከፀሀፊው ጋር ብትነጋገር አይሻልም ነበር ? ስእላዊ መግለጫው ተስማሚ አይደለም ፤ እናም ብታነሣው መልካም ነው ።

    ReplyDelete
  5. መድሎተ ስሁት ራስህ ብቻ ።

    ReplyDelete