Friday, 5 June 2020

ድኃ አገልጋዮችና “ሃብታም” አገልጋዮች


  ልከኛ አገልጋይ፣ በሰማይና በምድር ሥልጣን የተሰጠው የጌታ ኢየሱስ ኹነኛ መልእክተኛ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱን የላከው የሰማይ አምባሳደር አድርጎ በመሾም ነው፤ (2ቆሮ. 5፥20)። ሰፊው መከር፣ ወንጌል በመስማት የሚድኑ አማንያን እንደ ኾኑ እንዲኹ፣ መከሩን ለማገልገል የሚያስፈልገው በረከትና አቅም ደግሞ እዚያው በረከት ውስጥ ያለ መኾኑን እናስተውላለን። ጌታ ኢየሱስ፦ “መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ (ማቴ. 9፥፥38)።

   ትእዛዙ ከርኁሩኁ አምላክ የመነጨ፣ የርኅራኄ ትእዛዝ ነው፤ በጌታ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች የሚራራላቸው አልነበራቸውም፤ ሃይማኖተኛ መሪዎቹ “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ለተጨነቀውና ለተጣለው ሕዝብ” (9፥36) አንዳች ርኅራኄ አላሳዩም፤ እንዲያውም፣ “ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት በማስወጣት” (ማቴ. 23፥23) ጭምር “ቅሚያና ስስት ሞልቶባቸው” (ቊ. 25) ነበር፤ በተጨማሪም “በጸሎት ርዝመት እያመካኙ የመበለቶችን ቤት በመብላት” አቻ የማይገኝላቸው ነበሩ (ቊ. 14)።
    ጌታችን ኢየሱስ እረኛ የሚያስፈልጋቸው ሕዝቡን፣ እንዲህ ባሉ “ሆድ አደር” አገልጋዮች ዘወትር ተላልፈው እንዲሰጡ አይሻም፤ እናም የመከሩ ጌታ እውነተኛ የመከሩን ሠራተኞች እንዲያበዛ፣ በጊዜውም እንዲሰጥ አብዝታችሁ ማልዱ በማለት ተናገረ። ከያዝነው ርእስ ጋር ብናዛምድ፣ የጌታ ኢየሱስ ትእዛዝ በውስጡ ሦስት ዐሳቦችን ይዞአል፤
1.      ለመከሩ ሠራተኛን የሚሰጥ ጌታ ነው እንጂ እኛ በፈቃዳችን አንመርጥም፣
2.     በመከሩ ውስጥ ደግሞ ለሠራተኛው የሚያስፈልገው አለው ወይም ያገኛል፣
3.     እውነተኛ ሠራተኛን እንዲሰጥ ደግሞ የእኛ ድርሻ መጸለይ ነው።
   መከር የደረሰ ነዶ፣ የተወቃ አውድማ፣ የተከተተ ጎተራ፣ የበሰለ እህልን አመልካች ነው። ለእውነተኛ አማኞች መከሩ የምንናፍቀው የክርስቶስ መምጫ ቀናችን ነው (ማቴ. 13፥39)፤ ደግሞም ኢየሱስ እስኪመጣልን መሰብሰብን አንተውም (ዕብ. 10፥25)፤ ምክንያቱም መከሩ የመሰብሰሰባችን ምሳሌ ነውና (ሉቃ. 10፥2)፤ ደግሞም መከሩን የሚያጭድበት የራሱ ጊዜ አለው (ራእ. 14፥15-16)። እስኪመጣ ድረስ በመከሩ ውስጥ እጅግ ጥቂት የኾኑ የመከሩ ሠራተኞች አሉ። እኒህ ሠራተኞች ኹሉ ነገራቸው ያለው እዚሁ መከር ውስጥ ነው፤ “በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና።” (ሉቃ. 10፥7) እንዲል።
  የኢየሱስ መከር እንደ ተጨቈነ መስፈሪያ የተትረፈረፈ ነው፤ የሚያስፈልገን ነገር ኹሉ በዚያ አለው፤ ልብስ፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ የመጓጓዣ ክፍያዎች … አያስፈልጉምን? ያስፈልጋሉ። በእውነት ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ እርሱ እንዲህ ብሎአቸዋል፤ “ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና።” (ማቴ. 6፥32)፤ ካወቀ ታዲያ ለምን ብዙ አገልጋዮች በረሃብና በእጦት አለንጋ ይገረፋሉ? ለምንስ “ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጡ”? (ይሁዳ 7)፤ ለምንስ አንዳንዶች “በወንጌል ያላቸውን መብት በሙሉ ባለመጠቀም ለምንስ “ተጐዱ”?” (1ቆሮ. 9፥18) … የሚሉትን አያሌ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን።
   በመካከላችን አያሌ አገልጋዮች በረሃብ፣ በጥም በእርዛት አሉ፤ እጅግ ጥቂቶች ደግሞ በቊሣዊ ሙላትና በምድራዊ ብእል መትረፍረፍ አሉ፤ አብረን ብናገለግልም ተራርቀናል፤ ከአንድ ማዕድ እየቆረስን አንዳችን ተርበን፣ ሌላችን ሰክረናል፤ አንዳችን ታርዘናል ሌላችን መደረቢያና መከናነቢያ እናማርጣለን፤ ለአንዳችን የታክሲ ክፍያ የለንም፣ ለሌላችን ግን ለመኪናችን በሰልፍ ነዳጅ የሚቀዳ “አማኝና ተከታይ” አለን፤ … በእውኑ መከሩ እንዲህ ተሳከረ? በድሃና በሃብታም አገራት መካከል ያህል ያለውን ልዩነት፣ በድሃና በሃብታም አገልጋዮች መካከል ልዩነቱ ሰፊ ነው፤ ለምን? ሦስት ጠንካራ ምክንያቶች ይታዩኛል፤
       I.       ጥቂቶቹ ሃብታሞቹ አገልጋዮች የመከሩን “በረከት” የግላቸው ማድረጋቸው፦ አብዛኛዎቹ አገልጋዮች እየተራቡ ያሉት መከሩ በውስጡ ፍሬ የሌለው ኾኖ አይደለም፤ ጥቂት አገልጋዮች ሰብስበው በግል ካዝናቸው ቈልፈው ስለያዙት እንጂ፣ ከእኛም ተርፎ ለሌላውም መሰጠት የሚችል ነበር። ነገር ግን ብዙ የተሰጠን ለሌላውም መቁረስ እንድንችልበት መኾኑን ያስተዋልን እጅግ ጥቂቶች ነን። ዝንጀሮ ባልዘራው የመከር ክምር ላይ ጉብ ብሎ፣ መከሩን ሳይሳሳ እንደ ወደደ እንደሚደርግ እንዲኹ፣ የመከሩን በረከት ሰብስበን በግላችን የያዝን ብዙ ነን። እባካችሁ ይህን ቃል አስተውሉ፤ “አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?” (1ቆሮ. 4፥7)፤ “ሃብታሞቹ” ሆይ፤ ያላችሁ የእናንተ አይደለምና እባካችሁ አትመኩ!
       II.      ሃብታሞቹ መቀበል እንጂ ለድኻው ወንድማቸው መቁረስን የለመዱ አይደሉም፤ ከሃብታም አማንያን ሲቀበሉ፣ ኹሉም አገልጋይ እንደ እነርሱ ያለው እንጂ የጎደለው አይመስላቸውም። አማንያኑም ሃብታሙ አገልጋይ እንጂ፣ ድኃውና የጎደለው አገልጋይ አይታያቸውም፤ ስለዚህ ድኾች በአማኙም በአገልጋዩም የተረሱ ይኾናሉ። እባካችሁ “አማኞችና ሃብታም አገልጋዮች” ሆይ፤ ዙርያችሁን ተመልከቱ፤ ለሌላቸው አገልጋዮችና አማኞች መቁረስን ልመዱ፤ እናንተ የምትታዩና የምትጋርዱ ሃብታሞች አገልጋዮች ሆይ፤ አንዳንዴም ቢኾን እንኳ እስኪ ገለል በሉ!
   ይህን የምለው፣ ሳይኖራቸው ስለማያካፍሉት አይደለም፣ በደል አይደለምና፤ ነገር ግን እያላቸው ማካፈል ስለማይችሉት ነው። ሥራችን ወረቱ ሲበዛለትና ትርፉ ሲደራ[ለምሳሌ፦ ጳውሎስ ድንኳን ይሰፋ እንደ ነበረውና ሌሎችም ተግተው ሲሠሩ፤ ሐዋ. 18፥3፤ ኤፌ. 4፥28] አገልግሎታችንን የሚደግፉ ከበዙልን፣ መቁረስን መልመድ ቅዱስ ፍሬ ነው፤ አለማድረግ ግን ከንፉግነት ያልፋል። ለሃይማኖት ቤተ ሰዎችም አለማሰብም ነው (ገላ. 6፥10፤ 1ጢሞ. 5፥8)፤ ከፍቅርም መውጣትና ፍቅርን ማጣትም ነው፤ (1ተሰ. 2፥8)።
      III.      የጨከኑ አያሌ አገልጋዮች፣ “ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው” (1ቆሮ. 9፥18) በማለት፣ አንዳች “ብድራት” ሳይጠብቁ እንደሚሰብኩ የታመነ ነው። ይኹንና፣ መዘንጋት የሌለብን እውነታ፣ “ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ ማዘዙን” (ቊ. 14) ማስተዋል አለብን። ነገር ግን ይህን ችላ ብንልና ለሚታዩና ለሃብታም አገልጋዮች ብቻ ብናጐበድድ፣ የጌታን ትእዛዝ በግልጥ እንሽራለን።
   እንኪያስ፣ አብያተ ክርስቲናያትና የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ከዚህ በታች ያሉ ጥያቄዎችን እንዲያሰላስሉት እሻለሁ፤ የመከሩ ሠራተኞች “የኾኑት”ና የሚመስሉት፣ ፋንነው፤ ኰርተውና ጠግበው ያሉት፣ እውነተኛ የመከሩ ሠራተኞች ግን የደበዘዙት ስለ ምን ይመስላችኋል? በእውኑ እንደ ቃሉ ሠራተኞችን እኩል ለመቀበል፣ ለማልበስ፣ በእርቦና በገበታ ለመመገብ ባለመውደድ አይደለምን? ለአንዱ ጨቁነን እየሠፈርን ለሌላው በቊንጠራ እንኳ ለመስጠት እየሳሳን አይደለምን? ለሚታዩትና የታወቁ ለተባሉት የምንሰጠውና በሰዎች ወይም በሃብታሙ አገልጋይ ፊት ለመታየትና ለመታወቅ፤ ለመወደድና ለመሞገስስ አይደለምን?
   ጌታ ግን እውነተኛ አገልጋዮቹንና የሚድኑትን ያውቃል፤ አንድ ቀን ኑሮአችንና ሥራችን ኹሉ በጌታ ፊት ይገለጣል፤ የዚያኔ እንዳናፍርና የምንመልሰው እንዳናጣ፣ የምትሰጡ ሆይ ለማን እንደምትሰጡ፤ የተቀበላችሁም ቆርሶ መስጠትን አስተውሉ፤ ልመዱም። የታመናችሁና ጨክናችሁ የምታገለግሉ እውነተኛ አገልጋዮች ሆይ፤ ጌታ በነገር ኹሉ ጸጋ ያትረፍርፍላችሁ፤ አሜን።
 “እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል።” (1ዮሐ. 3፥16)

No comments:

Post a Comment