Friday 22 May 2020

ከ"ምኞት" ወይም ከ"ጉምዠታ" ወንጌል ተጠንቀቁ!


የብልጽግና ወንጌል መምህራን ብዙዎችን ካታለሉበት መንገድ አንዱ፣ ሥጋዊ አምሮትንና መሻትን ባልሞተው አዳም ውስጥ በማስገባት እና በመቀርቀር ነው። ይህ መንገድ ደግሞ ከዚህ ቀደም ሰይጣን ራሱ ያደረገውና ብክለትን ወደ ሰው ያስገባበት ጥበቡ ነው። በኢየሱስ ላይ ዓይኖቹ ትክ ያላሉ ኹሉ፣ በዚህ ጥበብ መታለሉ አይቀርም።


የመጀመሪያዪቱ ሴት ምክረ ሰይጣንን ሰምታ፣ የትእዛዙን ዛፍ በተመለከተች ጊዜ፣ ቅዱስ ቃሉ፦ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” (ዘፍ. 36) ይላል።

ሰይጣን በመጎምጀት ያስገባው ዐሳብ፣ "እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምት ሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍ. 34-5 ዐመት) የሚል፣ እግዚአብሔርን የመኾን ከንቱ ምኞት ነበር።

ሰይጣን ለራሱ መኾን ያልቻለውን እግዚአብሔርነት፣ ሰዎች እንዲኾኑ መጎምጀትን አስጎመጀ። ሴቲቱ ከቃሎቹ ጣፋጭነት የተነሣ፣ ምራቋ ተዝረበረበ፤ ውስጥ መሻቷ ተንቀለቀለ። ወንዱ ደግሞ በፍጹም መሻት ራሱን ከጥፋቱ ዶለ። ሰው በከንቱ ጉምዠታ እንደ እግዚአብሔር ሊጌትይ ሲቋምጥ፣ ውድ ልጅነቱን የእግዚአብሔርን የፍቅር ትእዛዝ በመሻሩ አጣ።

አምላክ የመኾን ዐሳብ ከጥንትም የዲያብሎስ ነው፤ እርሱ ከመጀመሪያው አሳች ነውና (ዮሐ. 844) በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተነግሮአል፣ "በልብህም እንዲህ አልህ፤ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤ በተራራው መሰብሰቢያ፣ በተቀደሰውም ተራራ ከፍታ ላይ በዙፋኔ እቀመጣለሁ፤ ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።” (ኢሳ. 1413-14) ይህ ክፍል በጊዜው ለባቢሎን ንጉሥ የተነገረ ቢኾንም፣ አደራረጉና አወዳደቁ ከሰይጣን ጋር ተመሳሳይ ይመስላል። ጌታ ኢየሱስም፣ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።” (ሉቃ. 1018) እንዳለው።

ራሱን እንደ ልዑል ከፍ አድርጎ፣ ከደመናት በላይ ዙፋኑን ሊዘረጋ በልቡ ያሰበው የአጥቢያ ኮከብ(ሉሲፈር) ማደሪያው ጥልቅ፤ መጣያው ሲኦል ኾነ። አይንኮታኮቱ ተንኮታኮተ፤ የአምላክነት ዐሳቡ ተኮማትሮ ተጨራመተ።

ሰይጣን በዋሾነትና በማታለል፤ ቅይጥ ዐሳብ(እውነትና ሐሰት ቀላቅሎ) በማቅረብ የሚተካከለው የለም። በዚህ ዋሾ ብቻ ሳይኾን፣ ተንኮለኛም ነው። ቃለ እግዚአብሔር ሲጠቅስ፣ አመሳስሎ ለመለየት በሚያዳግት ዓይነት ተንኮለኝነት ነው።

አምላካዊ ክብር ስለሚሻም፣ የትኛውንም ለአምላክ የሚሰጠውን አምልኮ ለመቀበል ይክለፈለፋል። በማያስደንቅና ታላቅ ነገር ባልኾነ መንገድ፣ ተከታዮቹም ፍጹም ይመስሉታል። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።” (2ቆሮ. 1115)

የሰይጣን ሎሌዎች የኾኑት የብልጽግና ወንጌል መምህራን፣ "ቁርጥ፤ እግዚአብሔርን ነን! ትናንሽ አማልክት ነን! የእግዚአብሔር ዘረመል(DNA) አለን!... ይህንም ያወቅነው ዓይናችን በርቶልን ነው" ቢሉም፣ ውድቀታቸው ከመጀመሪያዎቹ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ራቁትነት።

እናም፤ ከክፉ መጎምጀት ተጠበቁ፤ ክርስቶስ የተናገረን እርሱ በቂያችን፤ የዘላለም ሕይወትም ነው። ሰይጣን ሊያራቁተን፣ አገልጋዮቹ ሊገፍፉን ይሮጣሉ፤ ነቅታችሁ ልብሳችሁን ጠብቁ፣እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” (ራእ. 1615)

ኢየሱስ ሆይ፤ ሳናድፍ፤ ልብሳችን ሳይገፈፍ፤ ማራን አታ፤ እባክህ ቶሎ !!! አሜን።

2 comments: