Thursday 13 August 2020

የመጽሐፍ ቅዱሱ - ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው መሲሕ (ሉቃ. 19፥41-44)

Please read in PDF

   ጌታችን ኢየሱስ ስለ ማልቀሱ የተነገረው እጅግ በጣም ውሱን ቦታ ብቻ ነው፤ ካለቀሰባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ያለቀሰው ልቅሶ ነበር። ያለቀሰው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ፣ ከተማይቱን ፊት ለፊት በመመልከት ነበር። ሚስቱን አብዝቶ የሚወድድ ጐልማሳ፣ ሚስቱ በተወችው ጊዜ በስብራት እንደሚያለቅስ እንዲሁ፣ ኢየሱስም የከተማዋ ኹለንተና ከሚታይበት ከደብረ ዘይት ተራራ ፊት ለፊት ተቀምጦ ለኢየሩሳሌም አለቀሰላት።

የመሲሑ ሙሾ ምክንያት

   ኢየሩሳሌም፣ በመጨረሻው የመሲሑ የዙፋን ችሎት ጲላጦስ ፊት ቀርቦ፣ ጲላጦስ “መሲሑን ምን ላድርገው?” ሲላት፣ “ስቀለው!” ብላ አሰምታ ጮኻ የዓመጽ ቃል ተናግራለች፤ (ማር. 15፥12-13)። ጲላጦስ፣ “ያደረገው ክፋት ምንድር ነው?” ብሎ ቢጠይቅም፣ ኢየሩሳሌም ግን ምላሽዋ ያው የተለመደው፣ “ስቀለው!” የሚል የዓመጽ ቃል ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ያውቃል፣ ከዚህ ባለፈ ደግሞ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው፣ በሙሉ ኀይላቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደሚገድሉትና በዚህም ምክንያት የሚያገኛቸውን ጽኑ ሰቆቃ ኢየሱስ አስቀድሞ አይቶአል፤ እነርሱ ግን ይህን ኹሉ ለማየት የተገለጠ ዓይን፤ የሚያስተውልም ልብ አልነበራቸውም።

    አያሌ ነቢያት ልክ እንደ ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ሙሾ አውጥተው አልቅሰውላታል፤ በተለይም ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም፣ “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!” (ኤር. 9፥1) በማለት፣ ጽኑ ሐዘን ማዘኑን ይነግረናል። ኤርምያስ አልቃሻ ብቻ አልነበረም፣ ደግሞም ኢየሩሳሌም የምትሠራው ሥራ እጅግ ያስቆጣውና ያስመርረውም ነበር፤ ልቅሶው፣ ሊመጣ ያለውን ጥፋት ኢየሩሳሌም ባለማየቷና ለማየትም ጨርሶ ባለመውደዷ ያለቀሰው ጽኑ ልቅሶ ነው። ለዚህም ሰቆቃ በሚል መጽሐፍ የታወቀ መጽሐፍን ጻፈ።

  የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታ ኢየሱስም ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው ልቅሶ፣ በሙሾ የታጀበ ነበር። የሙሾው ሥረ ምክንያት፣ “የመጐብኘትዋን ዘመን አላወቀችም” የሚል ነው፤ እግዚአብሔር አምላክ በመሲሑ በኩል ለኢየሩሳሌምን ወይም ለአይሁድ ቢገለጥም፣ እነርሱ ግን ሊቀበሉት ፈጽመው አልወደዱም፣ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።” (ዮሐ. 1፥11) እንዲል። ኢየሱስ ወደ እርሷ የመጣው፣ የሰላምዋ ቀን ዛሬ እንዲኾን ነበር፤ እርስዋ ግን ይህን ውድና ውብ ሰላም ለመቀበል አልታደለችም።

   ሉቃስ፣ የኢየሩሳሌም ልበ ደንዳናነትና አለመታዘዝ በንስሐና በመመለስ እንዲስተካከል እግዚአብሔር በልጁ በኩል፣ የሰጣት የሰላም ዕድልን ለመቀበልና ለማየት ከዓይንዋ ተሰውሮ ወይም ላለማየት ዓይንዋ ታውሮ ነበር ይለናል። ሽፋሽፍትዋ ሥር ያለው እውነት ከዓይንዋ መሰወሩ እጅግ ይደንቃል፤ ያሳዝናልም፤ አያሌ ተአምራትን ተመልክታለች፤ አስደናቂ ትምህርቶችን ሰምታለች፤ እንከን አልባ ሕይወቱን አይታለች፤ ሐዘንተኞቿን አጽናንቶ ሲመልስ ምስክርነት መስጠት ሲገባት ዋሽታበታለች፤ እናም የመጣላትን የሰላም ንጉሥ በዓመጽ ከመካከሏ ልታስወግድ መቸኮልዋ፣ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ነበር።

ያለ መስማት ፍጻሜ

    የተሰጣትን እንከን አልባ ሰላም ልትቀበል ባልወደደች መጠን፣ እግዚአብሔር የሰጣትን የንስሐ ዕድልና የእግዚአብሔርን ልጅ ራሱን በመካድ ላለመቀበል በራስዋ መፍረድዋ ፍጻሜዋን እጅግ አስፈሪና አስደንጋጭ ያደርገዋል። ኢየሩሳሌም ለመመለስ ምሳሌ የምትኾናት ከተማ ነበራት፤ ነነዌ። ነነዌ በመመለሷ እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎላታል፤ ኢየሩሳሌም ግን ግን ለመመለስ ፈጽማ አልወደደችም። ሰላምን እንቢ ያለች ከተማ፣ ሰይፍ ሳይበላት አይቀርም።

   ጌታችን ኢየሱስም የተናገረው ይህን ነው፣ ጠላት ኢየሩሳሌም በሰይፍ ይከብባል፤ በውስጥዋ ያለውን ኹሉ ያጠፋል፤ ሰፊው ምሕረቱ፣ የተትረፈረፈው ቸርነቱ፣ ፍጹም ታጋሽነቱ ኹሉ እንዲድኑና እንዲመለሱ፤ እንዳይጠፉም ነው እንጂ በዓመጻቸው እንዲበረቱ አይደለም፤ (ዮሐ. 3፥17፤ ሮሜ 2፥4፤ 1ጢሞ. 2፥4፤ 2ጴጥ. 3፥9)። አለመመለስ፣ ትእግሥቱን መናቅ፣ የቸርነቱን መቻል ማቃለል … በፍጻሜው ፍርድና ጥፋት ነው፤ ምክንያቱም የተሰጠንን ጊዜ በትክክል አለመጠቀም፣ ሰጪውን ራሱን መናቅ፤ የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ መካድ ነውና።

ወራት ሳይመጡብን እንመለስ!

   የኢየሱስ ዓይኖች ዛሬም ያነባሉ፤ የአብ ልቦች ዛሬም ይተክዛሉ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስሜት ዛሬም በሐዘን “የጠቆረ” ነው፤ ምክንያቱም የነነዌ ልብን ከመያዝ ይልቅ፣ በመለያየትና በመበላላት ተጠምደናልና። ከመመለስና በንስሐ መንገዳችንን ከማጥራት፣ የያዝነውን የክፋት መንገድ እግዚአብሔር ራሱ እንዲያጸድቅልን የፈለግን ይመስላል። በእውኑ በዚህ መንገዳችን ኢየሱስ የሚያዝን አይደለምን? ልቡ የሚሰበርስ አይደለምን? ዛሬም ኀጢአትን የሚጠላው ያ ስሜቱ፣ በእውኑ የተለወጠ ነውን? ከቶ አይደለም።

   የሰላማችን ጊዜ ከፊታችን ተሰውሮአል፤ የእግዚአብሔርን የፍቅር ጠባይ ናቅነው እንጂ፣ ወደን ለቃሎቹና ለፈቃዱ በመታዘዝ አልተገዛንለትም፤ የኢየሱስን እንባዎች ለማበስ፣ ትክክለኛ አማኝነታችንን በሕይወት ምስክርነት መግለጥ አለብን። የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ፣ ዛሬም ባለመመለሳችን ሃዘኑ ጥልቅ፤ እንባው ብዙ ነው፤ ከሰላማችን ጋር እንድንገናኝ፣ የጉብኝታችንን ጊዜ እንድናስተውል ይፈልጋል፤ ዓይናችን እንዳታይወር፣ ቅጥር ቀጥረው ከብበው የሚያስጨንቁን ኃይል እንዳያገኙ እንመለስ፤ ወራት ሳይመጡብን እጃችንን በመዘርጋት እርዳን እንበለው።

ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።


1 comment:

  1. you couldn't believe how much it touched my soul.

    ReplyDelete