Sunday, 26 July 2020

የልቤ ሙሾ! (ስለ ወገኖቼ፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ክፋት ማገንገን)

Please read in PDF
 
   በባሌ አጋርፋ(አምቤንቱ)፣ በሻሸመኔ፣ እንዲሁም “በትውልድ መንደሬ” በአርሲ ነጌሌ የተፈጸመውን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ዘግናኝ ተግባር ሰምቼ፣ አይቼ በሰውነቴ ተሸማቅቄአለሁ፤ ለረጅም ሰዓት አልቅሼአለሁ፤ በባሌ አጋርፋ(አምቤንቱ) በአካል ተገኝቼ የኾነውን ኹሉ አይቻለሁ፤ አቤቱ! ይህን ለምን አሳየኸኝ? የአዛውንቶችን ሰቆቃ ለምን አመለከትኸኝ? የማልችለውን ለምን አሸከምከኝ? ሆደ ባሻውን ለምን ድንጋጤንና ፍርሃትን የሚያጭር ነገር እጎበኘው ዘንድ ወደድክ? አንተ ለደካሞች አልተከላከልክላቸውም፤ እኔ ምን እንዳደርግ አመለከትኸኝ ይኾን?

   በአገሬ አፍሬአለሁ! አቀርቅሬ ተሸንፌ አልቅሻለሁ፤ ቅስሜ እስኪሰበር ቅስስ ብዬ ሄጃለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እስከ መቼ ሰይፍ የጨበጡ በማረድ ይበረታሉ? ጌታ ሆይ! “ምንም የማያውቁ” የአእምሮ ሕሙማን ሲታረዱ አይገድህምን? ሕፃናት ወንዶችና ሴቶች መደፈራቸው ሳያንስ፣ መታረዳቸውን አትመለከትምን? መልክህና አምሳልህ ያለበት ክቡር ሰው፣ ታርዶ የጅብና የአእዋፍ ምግብ መኾኑ አያስቈጣህምን? የሰው በእሳት መንደድ፣ የሰው ቁልቁል መሰቀል አይሰቅህምን? …

   ይህ ኹሉ ሲኾን እያየህ ለምን ዝም አልከን? እናት ልጄን፣ ሚስት ባሌን አስጥሉልኝ ሲሉ ለምን አልሰማህም? ለኀጢአተኛ ሰላም፣ ለአራጅ ለምን ቀና ኾነ? አቤቱ አንተ ጻድቅ ነህ፣ ለምን ፍትሕ ድል ነስቶ አይወጣም? የክፋት በትር ለምን ወፈረ? ለደካሞች የመጣኸው ጌታ፣ ደካሞች ሲቀጡ ምነው ሳትረዳቸው? ጌታ ሆይ፤ የሚንቀጠቀጡ ከንፈሮችን፣ የሚርገበገቡ ዓይኖችን፣ የሚብረከረኩ ጉልበቶችን … ተመልክቻለሁ፤ የሞትክለት ፍጡርህ ለምን እንዲህ ተጐሳቀለ?

  የፍጥረተ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ አንተ ብቻ ነህ፤ በምድር ያለው ኹሉም ነገር ይገድሃል፤ አንተ ሳታውቀው በምድራችን የሚከናወን አንዳች ነገር የለም፤ የምድር ጉንዳን እንኳ በፊትህ የተጠበቀችና የታሰበች ናት፤ ድኾችና የአእምሮ ሕሙማን በፊትህ ፈጽሞ የተዘነጉ አይደሉም፤ ታድያ በምድራችን ላይ እኒህ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ የአእምሮ ሕሙማን፣ “የዚህ ብሔር አባል ወይም ሃይማኖት ተከታይ ናቸውና” ተብለው ሲገደሉ ዝም አልክ? አይገድህምን?

ገዳዮች የደካሞችን ጣዕር ሲያበዙ፣ ኀጢአትን እንደ መጐናጸፊያ ሲጐናጸፉ ለምን ዝም ትላለህ? በደልና ግፍን፤ የሕግን ልልነት፣ የፍትህ ማጋደል፣ የሐቅ ጥመት፣ የእውነት መደፍጠጥ፣ የሐዘኔታ ልቡ መድማት፣ የርኅራኄ ጉበት መፍረስ፣ የመቀባበል አንጀቱ ሲቃጠል … ለምን አሳየኸኝ? ለምን አመለከትኸኝ? አባብዬ! ለምን አስደነገጥኸኝ? ለምን እንባዬን አፈስስ ዘንድ መጽናናትህን ወሰድክብኝ?

እኛን ለማዳን ገደድ አለህ? እኛን ለመታደግ ደንታ አለህ? የእናቶች አንጀት ሲቃጠል፣ የአባቶች የሲቃ እህታ፣ የወንድ ልጅ ብርታቱ ሲፈታ፣ የእህቶች መብከንከን፣ የሕፃናት የደረቀ ከንፈር ያባባሃል? በአንድ ሌሊት፣ ልጁ የተነጠቀችበትን አባት፣ ልጅዋን ድንገት በጨካኞች ያጣችውን እናት፣ በወንድሙ ፊት የታረበትን ወንድም፣ ሴት ልጁን በፊቱ የደፈሩበትን አባት እንዴት ታጽናናዋለህ? … ይህን ኹሉ ብመለክትም አንተ ጻድቅ፤ ርኁርኅ፣ አዛኝ፣ በሰማይም በምድርም አቻ የሌለህ አሳቢና መጋቢ ነህ።

ጌታ ሆይ! ዓለም ኾን ብሎ የረሳቸውንና ለዓመታት የፈረሱትን የመንና ሶርያን ሳስብ ኢትዮጲያንም እፈራለሁ፤ መንገዳችን ጠማማ፤ አረማመዳችን ክፉ ነው፤ መጋቢው አባታችን ሆይ፤ ዓይኖቼ ቢፈዙም እንኳ አንተን ከመጠበቅ አልታክትም! አንድ ቀን እንደምትመጣ፤ ኹሉን እንደምታስተካክል አምናለሁ፤ አራጅና ገዳዮች፤ ጥላቻ ቀላቢ ፖለቲከኞችና ሃይማኖተኞች በንስሐ፤ በልጅህ አምነው እስካልተመለሱ ድረስ በፊትህ አንዳች ሞገስና መልስ እንደሌላቸው አምናለሁ! አቤቱ ያህዌ ኤሎሂም ሆይ! ለተጠቁት ደስታህን አብዛላቸው፤ አሜን።

ወላጅ አዶናይ አባታችን ሆይ፤ ለክፉዎች “ልጆችህም” ባያምኑብህም ርኅራኄህ ይንጠብጠብላቸው፤ በምሕረትህ አስባቸው፤ እኛንም አጽናን፤ አጽናናን፤ አሜን።

6 comments:

  1. Keep it up bro!

    ReplyDelete
  2. Amazing ! No words for it !

    ReplyDelete
  3. I appreciate the way you are conveying idea and expressing the attitude of Bible

    ReplyDelete
  4. አሜን በምህረቱ ያስበን!!!!

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር ይመስገን ቃለ ህይወትን ያሰማልን መምህራችን

    ReplyDelete