የሰዱቃውያንን ጠባይ ያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፦
1-
የመሲሑ ክርስቶስን
መምጣት የማይቀበሉና የማያምኑ፣
2-
የሙሴን
ሕግ ብቻ እንጂ የመዝሙራትንና የትንቢትን መጻሕፍት የማይቀበሉ፣
3-
ትንሣኤ
ሙታንን፣ መላእክትንና መንፈስ ቅዱስን የማይቀበሉና መኖሩንም የማያምኑ(ማቴ. 22÷23-33)፣
4- ባለጠጐችና በጊዜው በጣም የተሻለውን ቅንጡ ኑሮ የሚኖሩ፣ የካህናት ቡድን የኾኑ፣
5-
በጊዜው
ከነበሩ ሮማውያንና ቄሳሮች በኹሉ ነገራቸው በአንድ በመስማማት ይኖሩ የነበሩና፣
6-
ጌታ ይግባኝ
በሌለው የአይሁድ የሲንሐንድርየም ሸንጎ ፊት በቀረበ ጊዜም የፈረዱበትና አብዛኛውንም የፍርድ ወንበር ጨብጠውም የነበሩት እነርሱ
እንደ ኾኑም ታሪክ ጠቅሰው ይነግሩናል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን በግልጥ በአደባባይ
ይፈጽም በነበረበት ወራት ሰዱቃውያን ከፈሪሳውያንና ከጸሐፍት ባልተናነሰ መልኩ ይከሱትና ያሳጡት በብዙ ነገርም ሰኰናውን እየነከሱ
ይተናኰሉትም እንደ ነበር ታላቁ የሕይወት መዝገብ ይነግረናል።
የሙሴን ሕግ እንደሚቀበሉ ቢናገሩም በምንም አይነት መልኩ ግን ሕይወትና
ኑሯቸው ከጨበጡት መጽሐፍና ከሚናገሩለት እውነት ጋር የማይዛመድና የማይጣጣም ነበር። ሙሴን በታሪክ ቢያውቁትም በሥራቸው አይተባበሩም።
የሙሴን ትንቢትና ምሳሌውን ቢናገሩትም የትንቢቱንና የምሳሌውን ፍጻሜ ግን ማወቅና መቀበልም አይሹም። ትንሣኤ ሙታንና ፍርድ እንደ
ሌለ ስለ ካዱም ለኃጢአታቸው ድንበር፣ ለነውራቸው ዳርቻ፣ ለግፋቸውም ማብቂያ፣ ለክፋታቸውም የማያልቅ ቀጠሮ የያዙ ናቸው።
ያማረ ቤታቸውንና ኑሯቸውን እንጂ የሕዝቡ መዋረድና መጎስቆል፣ የደመቁ
ካባና ቀሚሳቸውን እንጂ የሕዝቡ መታረዝና በነፍስ መራቆት፣ ስለሚቀበሉት አስራትና በኵራት እንጂ የሕዝቡ እርር ኩምትር ድብን ብሎ
በፍትሕና በእውነት እጦት መክሰል፣ ስለ መልካቸው ቅላትና ወዘና እንጂ የሕዝቡ ሁለት መልክ፣ ምሬትና ብሶት፣ የላመና የጣመ እየበሉ
የሕዝቡ የኅሊና መሻገትና የመንፈሱ መድረቅ፣ ለሕይወትና ለቅድስና የተፈጠረው የሰው ፍጡር ከስብዕና እንኳ ወርዶ ለማይረባ አዕምሮ
ተላልፎ መሰጠቱ … ምንም ደንታ ምንም ስሜት የማይሰጣቸው ነበሩ። ስለዚህ በዘመኑ አለልክ ፍርድ ሚዛን ስቷል፣ መንፈሳዊ ሕይወት
ሞቷል፣ ኃጢአት እንደ ነውር መቈጠሩ ተትቷል፣ መቅደሱ ጭምር ለደራ ንግድ ተላልፎ ተሰጥቷል።
የዚህ ሁሉ ዳርቻው፣ የሰቆቃው ሁሉ ማብቂያው የሰቀቀን ድንበሩ፣ የመርገም
ጨርቁ ጽድቅ፣ የነውረኝነቱ ኦሜጋው፣ የመንፈሳዊው ጕስቁልና ፍጻሜውና … የመለምለምና የማፍራት ጅማሬና አልፋ የመሲሑ ክርስቶስ መምጣትና
መገለጥ ነበር። ነገር ግን የእርሱን መምጣትም ሆነ ተገልጦ ሕዝቡን በመጽናናት፣ በእረፍትና በሕይወት እንደሚመራ አያምኑም። የእኛ
እውቀት፣ ጥበብና ባዕለጠግነት የክርስቶስን መገለጥ ፈጽሞ ሊተካ አይችልም። ያለን ነገር ክርስቶስን መግለጥና ለሌላቸውም ሕይወቱን
እንዲጠሙና ለማየት እንዲናፍቁ ማድረግ ካልቻለ ያለን ነገር ከሰዱቃዊነት ሀብት አይዘልም። ብዙ አማኝ ነን የሚሉ ክርስቲያኖችም ሰው
የተከተላቸውንና የደገፋቸውን ሰባክያን፣ ዘማርያን፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ አጥማቅያን፣ ዲያቆናት፣ መሪዎች፣ መጋብያን፣ ወንጌላውያን
በወረት ፍቅር የመከተልና አብሮ መጓዝ እንጂ ከክርስቶስ ጋር ባይገናኙም ግድ የላቸውም። ሰዱቃውያን ድጋፍ እስካገኙ ድረስ ሕዝቡ
ከክርስቶስ ጋር ባይገናኝም የሚያስጨንቃቸው አይደሉም።
በክርስቶስ የትንሣኤ ሙታን ትምህርት የክርስትና ዋናና የተመሰረተበትም
የተስፋ ትምህርት ነው። በቤተክርስቲያን ቀኖና ይህን ትምህርት የሚክዱና የማይቀበሉ ቍጥራቸውም ከመናፍቃን ይቈጠራል። የመጀመርያዎቹ
የቤተክርስቲያን መናፍቃን የሚባሉት ግኖስቲካውያን የትንሣኤ ሙታንን ትምህርት አያምኑም፤ አይቀበሉምም። ይህ ማለት ሰው ዛሬ በሚሰሠራው
ክፋቱ በሙታን ትንሣኤ እንደሚቀጣ አያምኑም ማለት ነው። ሰው ለሚሠራው መልካም ሥራ ሽልማትና የክብር ትንሳሣኤ፣ ለኃጢአቱ ደግሞ
ቅጣትና የውርደት ትንሣኤ አለኝ ብሎ ካላመነ በተለይ ለሚሠራው ክፋትና ኃጢአት ድንበር የለውም ማለት ነው። ምክንያቱም ሽልማትም
ውርደትም በትንሣኤ ሙታን ትምህርት ውስጥ የሚካተት ነውና። ቤተክርስቲያን የዛሬው መከራዋንና ሐዘንዋን ታግሣ አጸፋ ከመመለስ ተከልክላ
በቅድስና ራስዋን ለክርስቶስ አሳልፋ የሰጠችው አክባሪዬ፣ ሞገሴ ዳግም በሙታን ትንሳሣኤ መጥቶ ያከብረኛል ብላ ነው።
ኃጥአን ፍርድ እንደ ሌለ ስለሚያምኑ አመጻቸውን እስከ ሰማይ ጥግ እንደ
ጽዋ ይመሉታል። ቤተክርስቲያን በግልጥ ኃጢአትን መገሰጽና መጥላት ካልቻለች የሚገጥማት የመጀመርያው ነገር የቅድስና ካባዋን አውልቃ
ከኃጥአን ጋር በመመቻመች ለመኖር ራስዋን ታዘጋጃለች። ጉበኛና ሴሰኛ መሪዎችንና ባዕለ ሥልጣናትን ለመገሰጽና ለመውቀስ የቤተክርስቲያን
መሪዎች ንጹህና ከዚህ ክስና ነቀፌታ የራቁ መሆን አለባቸው። በዚህ ነውር የተያዘች ቤተክርስቲያን ግን መቼውንም ጊዜ ከነዚህ መሪዎች
ጋር ተደላድላ ትኖራለች እንጂ እንደ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ አንገቷን እስከ መሰየፍ አትጨክንም።
ሰዱቃውያን በፈቃዳቸው ከሮማውያን ጋር ይተባበሩ ስለ ነበር ሕጉን ጨብጠው
አለ ሕግ እንደሚኖሩ አሕዛብ ነበሩ። ሕጉ በእጃቸው ሞቷል። ያተሩፉበት ዘንድ የተሰጣቸውም መክሊት ቀብረውታል። ይህ ደግሞ ብርቱ
ቅጣትና ተግሳጽ አለበት። ለክርስቶስ በሕይወት ካልመሰከርንለትና እስከ ሞትም በመታገሥ መክሊትን ካላተረፍን ወንጌሉ፣ የተሰጠን
የሕይወትና የእውነት መክሊት ይቀበራል ፍሬ አልባም ይሆናል።
ጌታ ሆይ ቤተክርስቲያንህን ከዚህ መንፈስ ከልክል።አሜን።
(2009 ዓ.ም ተጻፈ፤ ሐረር)
No comments:
Post a Comment