Monday 30 November 2020

ጽዮን፣ ታቦትን አይወክልም!

 Please read in PDF

መግቢያ

በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አሳታሚነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕሥራ ምዕት(አዲሱ ሚሊኒየም) ላይ “የራስዋን” አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ አሳትማለች። መጽሐፉ በተለምዶ “ሰማንያ አሐዱ” ተብሎ የሚጠራ ቢኾንም፣ ነገር ግን አያሌ ግልጽ ስህተቶችን በውስጡ እንደ ያዘ ወይም እንዲይዝ ታስቦበት የታተመ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በተለይም በግልጽ የተቀመጡና የታወቁ ሐረጋትን በመቀየር ድፍረት ያለበትን ስህተት ሠርቶአል። ከሠራቸው ስህተቶች አንዱም የእግዚአብሔርን ታቦት ለግል ዓላማቸው ከእግዚአብሔር ይልቅ ለማርያም[ለታቦተ ጽዮን] ለመስጠት በሚመች መንገድ ወደ ሴት ጾታ መለወጣቸው ነው።



የተለወጡ የታቦቱ ሐረጋትና ዓላማቸው!


የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ

“የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድሩበትን ቦታ ታገኝላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ትቀድማቸው ነበር።” (ዘ. 10፥33)

    የ1954 ዓ.ም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ

“የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው።”

“የእግዚአብሔርም የሕጉ ታቦት ትከተላቸው ነበር። … የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደችከተማዪቱንም ዞረችወደ ሰፈርም ተመልሳ በዚያ አደረች።” (ኢያ. 6፥8፡ 11)

“የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። … እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ።”

“ሕዝቡም ሁሉ አካትተው በተሻገሩ ጊዜ ታቦተ ሕጉ ተሻገረች” (ኢያ. 4፥11)

“ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ እያዩ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ ተሻገሩ።”

“በፊታችን እንድትሄድከጠላቶቻችንም እንድታድነንየእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ … የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባች ጊዜ …” (1ሳሙ. 4፥3፡ 5) …

በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ … የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ …” …

ለእግዚአብሔር ብቻ ተሰጥቶ የተጻፈውን ታቦት፣ ወደ ማርያም ወይም ጽዮን የመለወጣቸው ዓላማ፣ የማርያምን ወይም የታቦተ ጽዮንን የውሸትና የስርቆት ትርክት እውነት ለማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ታቦቱን የእግዚአብሔር ታቦት (1ሳሙ. 3፥3፤ 5፥10፤ 7፥1፤2ሳሙ. 6፥6)፣ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት (ዘኍ. 14፥44፤ ዘዳግ. 31፥25) የኪዳኑ ታቦት ወይም ጽላት (ዘኍ. 10፥33፤ ዕብ. 9፥4) በማለት ብቻ የሚጠራ ሲኾን፣ የታቦቱ አገልግሎት ዐሥርቱ ቃላት የተጻፉባቸው የኹለቱ ጽላት ማኖሪያ እና ከእስራኤል መሪዎች ጋር የእግዚአብሔር መገናኛ ኾኖ ነበር። ስለዚህም ታቦቱ የመሰጠቱ ዋነኛ ዓላማ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በአንድነት ለመገኘቱ የኪዳን ምልክት ኾኖ ብቻ ነበር፤ (ዘጸ. 25፥1-22፤ 40፥20)።

ታቦቱ በእግዚአብሔር ስም ስለ ተጠራም ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤ ዳጎን የተባለውን የፍልስጤማውያንን ጣኦት ሰባብሮ ጎማምዶታል (1ሳሙ. 4-6)፣ የታቦቱ መገኘት የእግዚአብሔር መገኘትን ይወክል ነበርና አያሌ ድልን አጊኝተዋል (ኢያ. 3)፣ የዮርዳኖስን ወንዝ ከፍሏል (ኢያ. 3፥17)፣ … ነገር ግን በታቦቱ የተሠራው ሥራ ኹሉ የተሠራው በብሉይ ኪዳን ብቻ ነው። ምክንያቱም ታቦቱ ለእስራኤል ልጆች የተሰጠው፣ እግዚአብሔር በመካከላቸው ለመገኘቱ ምልክትና ምሳሌ ወይም ጥላ ኾኖ ነበርና።

“የሙሴ ጽላት አለን” ለማለት የሚተረከውን እጅግ የተሳሳተ ትርክት እውን ለማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐረጋት እስከ መለወጥ መድረስ ግን እጅግ ታላቅ አለመታዘዝ ነው።

ማደሪያዎቹ እኛ ነን!

ቅዱሱ ድንኳን የተደኮነብን የክብሩ መገለጫዎች እኛ መኾናችንን ቅዱስ ቃሉ በግልጥ እንዲህ ይመሰክራል፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” (ዮሐ. 1፥14) እንግዲህ ይህን አምነን ከመቀበል በቀር ምን እንላለን? ምንስ ማብራሪያ ያሻዋል?! ይህን ያደረገ ጌታችን መንፈስ ቅዱስ ይባረክ፤ አሜን።

ኪዳኑ ኢየሱስ ነው!

በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር፣ አማኑኤል ኾኖልናል። ምክንያቱም ልጁ በደሙ ፍጹም ዕርቅን በእኛና በእግዚአብሔር መከከል አድርጎአልና፣ እናም እርሱ በእውነትና በመንፈስ ሊመለክ በመካከላችን አለና ሌላ ምልክት፣ ምሳሌ ወይም ቊሳዊ ጥላ አያስፈልገንም። አካሉ ሲመጣ ጥላው፣ የተመሰለለት ነገር ሲመጣ ምሳሌው፣ ዋናው ሲመጣ ምልክቱ ስፍራቸውን ሊለቁና ሊወገዱ ይገባቸዋልና፣ ታቦቱ በአካላዊ ቃል ሥጋ መልበስና በመንፈስ ቅዱስ በምልዓት ለቤተ ክርስቲያን መሰጠት ምክንያት ላያስፈልግ ከመካከላችን ተወግዶአል፤ እግዚአብሔር በልጁ እርሱን ብቻ ትኵር ብለን እንድናየው ኹሉንም ቊሳዊ ነገር[ታቦቱን፣ በሰው እጅ የተሠራ መቅደሱን፣ ጽላቱን፣ መሶበ ወርቁን፣ በትሩን፣ የነሐሱና የዕጣኑ መሠዊያን፣ መቅረዙን …]  ፈጽሞ አስወግዶአቸዋል።     

እግዚአብሔር በመካከላችን ሊገኝ ኪዳኑን ያጸናበት፣ በመካከላችሁ አለሁ፣ አልለያችኹም እኛን ያለበት ኪዳን ኢየሱስ እንጂ ቊሳዊው ታቦት አይደለም። “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ. 18፥20) እንዲል። በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ በመካከላችን ለመገኘት በስሙ መሰብሰብ ብቻ በቂ ነው። እንደ አይሁድ ጌታ በመቅደሱ ብቻ አለ አንልም፤ በመላለሙ ያለው ጌታ በመንፈስና በእውነት ሊመለክ አለ፤ ኪዳኑንም በልጁ ደም አጸና፤ አተመ። እንዲህ የወደደንና ያፈቀረን፣ ኪዳኑንም ፍጹም በማይታበል ኪዳን ያጸናልን ጌታ ይባረክ፤ አሜን።

ማጠቃለያ

እንግዲህ በብሉይ ኪዳን በሴት አንቀጽ የተጠራ ወይም ማርያምን የሚወክል ታቦት ለመኖሩ የሚመሰክር አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፤ እንዲያውም ታቦት በኢትዮጵያ የመጣበትን የሐሰትና የስርቆት ትርክት እውን ለማድረግ የቅዱሳት መጻሕፍት ሐረጋት መቆነጻጸል እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው፤ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ንስሐ ልትገባባቸው ከሚገባቸው ኀጢአቶች አንዱ ይህ ነው፤ ቊሳዊውን ታቦት ይዘናል በማለት የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነትና ኀይል መሳት አይገባምና፤ የኦሪቱ ኪዳን ታቦት እግዚአብሔር ክብሩን የሚገልጥበት ነው፤ የአዲሱ ኪዳን ታቦት ደግሞ እግዚአብሔር ሰውን በልጁ ደም ዋጅቶ ያደረበት ሕያው ማደሪያ አማኝ ነው፤ እናም ቊሳዊውን ታቦት አለን ከማለት መሲሑን በማመን የዘላለም ሕይወትን መያዝ ብልጫ ያለውና ታላቅ ማስተዋል ነው።

ጸጋ ይብዛላችሁ።

4 comments:

  1. ጥሩ መልእክት ነው፤መፅሐፍ ቅዱስን ለማሳሳት መሞከር በጣም አደገኛ ሀጥያት ነው፤ኦርቶዶክስ በአምልኮዋና በትምህርቷ መበላሸቷ ሳያንስ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ መድፈሯ ለሰይጣን እጅ እንደመስጠት ይቆጠራል።
    ስለ ታቦት በኦርቶዶክስ የሚነገረው በሙሉ ውሸት ነው፤ባዕድ አምልኮን የሚያስከነዳ ተረቶችን ያጨቀና የጨቀየ አስተምህሮዎችን የያዘ ነው፤ኦርቶዶክስ በቅርቡ ትታደሳለች!!

    ReplyDelete
  2. አንተን ያስጨነቀህ ታቦት በሴት አንቀፅ መጠራቱ ነው ወይስ ታቦት እስከ ጭራሹም አያስፈልግም እያልክ ነው ? በታቦት አምነህ በሴት አንቀፅ ለምን ይጠራል ብለህ ከተበሳጨህ ወደ ሙህራን ጠጋ ብለህ ጠይቅ ፤ አይ ታቦት አያስፈልግም ብለህ ካሰብክ እኛ በወንድ አንቀፅ ጠራነው ፣ በሴት አንቀፅ የሚያገባህ ነገር ዬለም ። እዛው በአዳራሽህ ጨፍር ።

    ReplyDelete
  3. Really blessed

    ReplyDelete
  4. I also have this kind of questions when i asked the abew they say nufake please tell us more and you have gut keep it up

    ReplyDelete