Tuesday 8 September 2020

ያለ ኢየሱስ ስርየት የለም!

 Please read in PDF

  ጳጉሜ 3 ብዙዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚላተሙበትን ድርጊት የሚፈጽሙበት ቀን ነው፤ በሌላ ቋንቋ፣ “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?” (ዕብ. 10፥29) የሚለውን ቃል በግልጥ የሚቃወሙበት ቀን ነው፤ “በመልአኩ ሩፋኤል” ስም መጠበል ወይም መጠመቅ ከኀጢአት ያነጻል የሚል ከንቱ ልፍለፋ።

የእግዚአብሔር ቃል ኀጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌላ ለማንም አልሰጠም፤ ጸሐፍት ፈሪሳውያን እንኳ ይህን እውነት፣ “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” (ማር. 2፥7) በማለት ይመሰክራሉ እንጂ አያስተባብሉም። እንኳን በአዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን እንኳ ሥርየት በታወቁት በኹለቱ መላእክት ስም[በሚካኤልና በገብርኤል] ሲደረግ አንድም ቦታ አንመለከትም፤ ከምንም በላይ ደግሞ በአዲስ ኪዳን፣ “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” (ማቴ. 1፥21) ተብሎ የተነገረለት ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው።

እንኳን ባላታወቀ መልአክ ስም፣ በታወቁት መላእክት ስም እንኳ ስርየትና የኀጢአት ይቅርታ ካልተደረገ፣ “በሩፋኤል ስም መጠበል ይቅርታ ያሰጣል” የሚለው ትምህርት ከወዴት መጣ? ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የላካቸው እንዲህ በማለት ነው፤ “ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።” (ሉቃ. 24፥46-47)። ንስሐና የኀጢአት ሥርየት በኢየሱስ ስም ብቻ አይደለምን? ከዚህ የወጣው ወይም ያፈነገጠው ለወንጌል ባዳ፤ ለቅዱስ ቃሉም እንግዳ ነው።

ኀጢአትን በተመለከተ በቀደመው ሰው ላይ ሞትን የፈረደው አንዱ እግዚአብሔር ነው፤ አንዱ እግዚአብሔር በመላለሙ ላይ የፈረደውን የሞት ፍርድ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ሌላ ፈጽሞ መሻር ወይም ይቅር ማለት አይችልም። ሞት በአንዱ ከገባ ይቅርታና ሥርየትም በዚያው በአንዱ ፈንታ ቤዛ ኾኖ በፈቃዱ በሞተልን በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው።  “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።” (ሮሜ 5፥17) እዲል፤ አሜን።

እንኪያስ ከወንጌል ውጪ፣ ከቅዱስ ቃሉ ባፈነገጠ መንገድ ስለምን የክርስቶስን ሞትና ቤዛነት ታክፋፋላችሁ? ስለ ምንስ ትንቃላችሁ? እግዚአብሔር በውድ ልጁ እንዲያው ከታላቅ ጸጋው የተነሣ ያደረገውን ይህን ታላቅ የድኅነት መንገድ አለመፈለግ ራሱ እግዚአብሔርን አለመፈለግ ነው ነው፤ እግዚአብሔር በልጁ የሠራውንና ብቁ የኾነውን የስርየት መንገድ ትቶ፣ ሌላ መንገድ መፈለግና መከተል ከእግዚአብሔር ይልቅ ጻድቅና ቅዱስ ለመኾን የመቀማጠል ያህል ብርቱ ግብዝነት ነው።

ነገር ግን ደም ሳይፈስ ስርየት የለም እንደተባለው፤ ያለ ኢየሱስ ስርየት፤ ያለደሙም አንዳች ይቅርታ የለም፤ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፤ ይህን እውነት ለትውልዱ አብራ፤ ግለጥም፤ አሜን።

 


1 comment: