Saturday, 26 December 2020

ውርርዱ በገብርኤል አልነበረም!

 Please read in PDF

መግቢያ

በመጽሐፎቻቸው ምዕራፍ ብዛት ዓበይት ነቢያት ተብለው ከሚጠሩት አንዱ፣ የነቢየ እግዚአብሔር የዳንኤል ትንቢት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ጸሐፊ ራሱ ለመኾኑ በራሱ በትንቢት መጽሐፉ ውስጥና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት አለ (9፥2፤ 10፥2፤ ማቴ. 24፥15ን ከዳን. 9፥27 እና 11፥31 ጋር ያስተያዩ)። የዳንኤል መጽሐፍ ዋና ሃሳብ ወይም ሊነግረን የወደደው እግዚአብሔራዊ መልእክት፣ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ጌትነትና ድል ነሺነቱን ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ጌታ ስለ ኾነ፣ “ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ የወደደውን ያሰለጥናል” (5፥21)።


በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ታሪኮች አንዱ፣ የሦስቱ ወጣቶች ታሪክ ነው፤ ታሪኩ በባቢሎን ምርኮ ዘመን ከእግዚአብሔር ውጭ ላለማምለክ በቆረጡና ለጣዖት እንዲሰግዱ አዋጅ ባሳወጀው ንጉሥ ናቡከደነጾር መካከል የተደረገውን ውርርድ የያዘ ነው። 

የታሪካዊ ዳራ ግጭት

በአጭር ቃል በኦርቶዶክስ ቀኖና ታኅሳስ 19 መልአኩ ገብርኤል ሦስቱን ወጣቶች እንዳዳነ ነው፤ ነገር ግን በድርሳነ ሚካኤል ዘታኅሳስም ሦስቱን ወጣቶች ያዳነው ሚካኤል ነው ይላል፤ (ድርሳነ ሚካኤል ዘታኅሳስ፤1990 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አክሱም ማተሚያ ቤት የታተመ፤ ገጽ 73-75)። ነገር ግን፦

1.   የክፍሉ ማዕከል የእምነት ፈተናውን ማለፋቸውንና በእግዚአብሔር ካላቸው እምነት የተነሣ ድል መንሣታቸውን ማሳየት እንጂ የመልአኩ “ትድግና፣ ማዳን” እንዲወራ አይደለም።

2.   በመጨረሻ ንጉሡ ንጉሣዊ አዋጅን በአዋጅ ሽሮ የተናገረው፣ “እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር …” ብሎ ፍርድ እንደሚያገኘውና በምድሪቱ ኹሉ እርሱ ብቻ እንዲመለክ አዘዘ፣ ስለዚህም የንጉሡም፤ የወጣቶቹም፤ የትንቢቱ ጸሐፊ ትኵረት መልአኩ አልነበረም፣

3.   የየትኛውም መልአክ ተአምራት ግቡ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲታመኑ፣ እንዲፈሩ፣ እንዲመልኩ … ብቻ እንጂ ሌላ ምንም ለማድረግ ቢሻ እንደ ሰይጣን ከመሻሩ አይቀርም።

ውርርዱ!

ውርርዱ፣ ለገብርኤል ወይም ለሌላ መልአክ ስለ መስገድና ስላለመስገድም አልነበረም፤ ውርርዱ ለናቡከደነጾር ምስል ስለ መስገድና ለእግዚአብሔር ብቻ ስለ መስገድ፣ ስለ ሦስቱ ወጣቶች እምነት ጽናት የተደረገ ብርቱ ውርርድ ነው። ናቡከደነጾር በአማልክቱ ታምኖ፣ ሦስቱ ወጣቶች እንዲሰግዱለት ለማስገደድ ያለውን ንጉሣዊ ቊጣና ቅጣት ኹሉ ተጠቀመ። ወጣቶቹ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነትና መደገፍን ፈጽሞ ባለመጣል ቆሙ። እስከ መጨረሻይቱ ሰዓት እምነታቸውና ምስክርነታቸው በእግዚአብሔርና በግርማዊነቱ ላይ ብቻ ነበር፤ እናም ግርማዊው ልዑል ያህዌ ኤሌሂም አዳናቸው፤ ታደጋቸው!

ከዚያ በኋላ ጣዖት አምላኪው ንጉሥ እንዲህ ብሎ መሰከረ፣ “መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ … በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።” አለ። እናም ንጉሡ ናቡከደነጾር ሦስቱን ወጣቶች እግዚአብሔር እንዳዳናቸው ፍጹም አመነ። የዕብራውያን ጸሐፊ እንደ መሰከረላቸውም በእርሱ ላይ ፍጹም በመደገፋቸው፣ “የእሳትን ኃይል አጠፉ፥” (ዕብ. 11፥34)። ጽኑዕ እምነታቸው በእሳት ተፈተነ፤ በባዕድ ምድር ያላሳፈሩትና ፍጹም የታመኑት ጌታ፣ እርሱም አላሳፈራቸውም።

ማጠቃለያ

ንጉሡ ውርርዱ ወጣቶቹ ለእርሱ እንዲሰግዱ ነው፤ ወጣቶቹ ደግሞ ለእግዚአብሔር እንጂ ለማንም ሊሰግዱ አልፈለጉም፤ ንጉሡ በፍጻሜው በወጣቶቹ አምላክ በእግዚአብሔር አመነ። ምን እንማርበታለን፣

1.   በኹኔታዎች ኹሉ በእግዚአብሔር ብቻ መታመን፣

2.   ቢያድነንም፤ ባያድነንም በእግዚአብሔር ጉዳይ በብርቱ መከራ ተከብበን ቢኾን እንኳ አለመደራደር፣ የሕይወት ክፍያም ከጠየቀን፣ ክፍያውን ያለ ድርድር መፈጸም፣

ሦስቱ ወጣቶች የተወራረዱት ለአምላካቸውና በአምላካቸው ስም ፍጹም በመታመን እንጂ ስለ መልአኩ አልነበረም፤ መልአኩ የታዘዘውን ብቻ ፈጸመ፤ ዛሬም ለተዋረዱና ለተጣሉ፣ መከራ ለገጠማቸው ኹሉ እርሱን በማስከበር ሕይወት ለሚኖሩ ልጆቹን የሚያድነው ታዳጊ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ አሜን።

3 comments:

  1. እግዚኣብሔር ዛሬም ቅሬታዎች አሉት ሰለአንተ እግዚኣብሔርን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ ጌታ አብዝቶ ይባርክህ

    ReplyDelete
  2. ዘመንህ ሁሉ ይባረክ

    ReplyDelete
  3. አንተ መንደሬ ሆዳም ፓስተር አረፍ እያልክ ሁሉም ላይ አትቀባጥር በሽታ

    ReplyDelete