Saturday 15 August 2020

ስለ ማርያም “ከሚሸቅጡ” ተጠበቁ!

Please read in PDF

   መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ብቻ መናገር አስተዋይነት፤ ያልተናገረውን ደግሞ አለመጨመር ፍጹም ታማኝነት ነው። እኛ ሰውን ደስ ለማሰኘት የተናገርነው “እውነት”፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ያልተናገረው ሐሰት ሊኾን የሚችልበት አንዳች ሚዛን የለም፤ የእውነት እውነተኛው ሚዛን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ከኾነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያልተናገረውና ያላለው ኹሉ ሐሰት፣ እርሱ የተናገረውና በእርሱ ያለው ብቻ እውነት ነው። ሚዛንን ስቶ ሚዛናዊ መኾን ፈጽሞ አይቻልምና።

የሸቃጮች ወቀሳ

   መጽሐፍ ቅዱስ፣ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።” (2ቆሮ. 2፥17) በማለት፣ ስለ ሐሰተኛ መምህራን ጠባይ በግልጥ ይናገራል፤ ሸቃጭነት የንግድ ቋንቋ ነው፣ አንድ ሰው ትርፍን ለማግኘት የሚጠቀምበት የጮሌነት ወይም የብልጣ ብልጥነት ተግባር። በአገራችን ልክ በቅቤ ውስጥ ሙዝ፣ በበርበሬ ውስጥ ቀይ አፈር እንደሚጨምሩ፣ ራስወዳድነታቸው ልክ አልባ የኾኑ ነጋድያን እንደሚያደርጉት ማለት ነው።

  በቆሮንቶስም፣ ሰርገው የገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎችም ያደረጉት እንዲህ ነበር፤ ቅንነት አልነበራቸውም፣ በራሳቸው የትምህርት አቀራረብ የሚመኩና አቀራረባቸውንም ሰው እንደሚወድደው አድርገው በማቅረብ፣ የአንዳንድ ተላላ አማንያንን ቤትና ማጀት፤ ኪስና ቦርሳ መበዝበዝ ተቀዳሚ ዓላማቸው ነበር። እኒህ ሰዎች ወንጌልን የሚሰብኩት፣ ለሕይወትና ለማዳን አይደለም፤ ይልቁን ለትርፋቸው፣ ለግል ክብራቸው፣ ለኑሮአቸው መደላደልና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ኾነው የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ነው።

   ሸቃጮች፣ እኛን ከሚወቅሱበት አንዱ፣ “ስለ ሣራ፣ ስለ ኤልሳቤጥ፣ … ሲነገር ደስ ይላችኋል፤ ስለ ማርያም ግን ሲነገር ይከፋችኋል፤ የምድራዊ መሪዎች ተቀዳሚ እመቤት እየተባሉ ማርያምን እመቤት ማለቱ ለምን አስከፋ?” የሚል በግብዝነት የታጀለ ወቀሳ ነው። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ድንግል የተነገረው ሲነገር አንዳችም ነገር አይከፋንም፤ ፊታችንም አይቀጭምም፤ ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ ከተነገረው በተቃራኒና ጨርሶ ያልተናገረውን ለድንግል ማርያም ሲነገር ስንሰማ፣ ያለ ማቅማማት አንቀበልም፤ ትክክል አይደለም ብለንም ደፍረን እንናገራለን። ለመኾኑ የምድራዊ መሪዎች “ተቀዳሚ እመቤት” ያሉት ሚስቶቻቸውን እንደ ኾነ ታውቁ ይኾን?! ማርያም “የኢየሱስ እናት” ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ከጠራት በላይ፣ እኛ መጽሐፉን እናውቅልሃለን አንልም፤ እርሷ “የኢየሱስ እናት” መባሏ በቂ ነው!

ድንግል ማርያምና ሌሎች ቅዱሳት አንስት

   ስለ ሌሎች ቅዱሳት አንስት ሲነገር፣ የተነገረውና የተጻፈው ብቻ ይነገራል፤ ስለ ድንግል ማርያም ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የሌሉ አያሌ ስህተቶችና ኑፋቄዎች ጭምር በብዙ ቤተ እምነቶችና በሸቃጭ አገልጋዮች ዘንድ አለ። ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ የሰው ልጅን ለማዳን አንድያ ልጁ ወደ ምድር ሊመጣ በወደደ ጊዜ፣ ከእርሷ እንደ ተወለደ በግልጥ ይናገራሉ። እግዚአብሔር ይህን ታላቅ ተግባር የፈጸመው በራሱ ፈቃድና ችሎታ እንጂ፣ በውርደት ከተማ በናዝሬት ከምትኖረው ከማርያም ጻድቅነት የተነሣ አልነበረም።

  ሌሎች ቅዱሳት አንስትን በተመለከተ ማንም ሲጨምርም ኾነ ሲቀንስ አንመለከትም። ማርያምን በተመለከተ ግን ኢየሱስን የሚጋርዱና አምልኮ የሚያጋሩ አያሌ ክህደትና ኑፋቄ ሲዘራ እንመለከታለን። ከዚህም የተነሣ፦

አዎን፤ ይህን እንቃወማለን!

   ስለ ድንግል ማርያም ያልተነገረውን፣ “ልክ አይደለም፤ አልተጻፈም” ማለታችን፣ ለአንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችውን ድንግል ማርያም የምንቃወም ይመስላቸዋል፤ እኛ የመጽሐፍ ቅዱሷን ማርያም፣ በተነገረላት መጠን እንናገራለን፤ እናስተምራለን፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ፣ ልዩና እንግዳ ትምህርት ያላትን ማርምን ግን ትምህርቶቿን የማንቀበለው፣ ከቅዱስ ቃሉ በአፍአ ስለ ኾነች ነው። ስለዚህም ድንግል ማርያምን በተመለከተ ከዚህ በታች ያለውን ጨርሶ አናስተምርም።

1.      በድንግል ማርያም ስም መማጸንን፦ እንድንድንበት የተሰጠን ስም አንድ ኢየሱስ ነው፤ ኢየሱስ፤ (ሐዋ. 4፥12)፣ እንድንለምንበትና እንድንማጸንበትም የተሰጠን ስምም ኢየሱስ የሚለው ብቻ ነው (ዮሐ. 14፥13-14)፤ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ከሚለው ስም ውጭ በማንም አንማጸንም፤ አንጸልይም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወልድ ስሙ ማንቱን ገላጭ ነውና። ስሙ በተጠራበት ኹሉ አምላካችን በዚያ አለ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ በተጠራበት በዚያ አለ፤ ምክንያቱም መንፈስ የኾነ አምላክ ነውና፤ (ዮሐ. 4፥24)።

  በድንግል ማርያም ስም የማንማጸንበት ምክንያት፣ እርሷ ስሟ በተጠራበት ኹሉ የምትገኝ አይደለችም፤ ስሟ በተጠራበት ኹሉ ለመገኘት እርሷ አምላክ መኾን ያስፈልጋታል፤ ነገር ግን እርሷ አምላክ አይደለችም፤ እግዚአብሔር እኛን መስማት የሚችለው በተወደደውና መስቀል ላይ መሥዋዕት ኾኖ እርሱን ባረካውና ደስ ባሰኘው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

2.     ከሙታን መካከል ተነሥታለች የሚለውን፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከሙታን መካከል የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ኾነና(1ቆሮ. 15፥20፡ 23፤ ራእ. 1፥4) ሥጋ ለባሽ ኹሉ፤ ድንግል ማርያምንም ጨምሮ ግን የክርስቶስን ኹለተኛ መምጣትና በኹለተኛ መምጣቱም የሚደረገውን ከሞት መነሣት እንደሚጠብቅ፣ ያለ ጥርጥር በግልጥ ይናገራል፤ ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ አማኞች ድንግል ማርያም ከሙታን መካከል “እንደ ልጅዋ ተነሣች” ብለው ያምናሉ፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱሳት አባቶች ትምህርት አንዳችም ማስረጃ የለም። ደግሞም የክርቲያን ሃይማኖት የተመሠረተው፣ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ብቻ ነው።[1]

  “ከሰውም ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፥ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማነው? ብሎ እንደ ተናገረ። ራሱን ማዳን ያልተቻለው ሌላውን ማዳን እንደ ምን ይችላል? አንድ ራሱን ሊያድን ያልቻለስ ዓለምን ሁሉ ሊያድን እንደ ምን ይችላል? ኃጢአት በሰው አድሮ ይኖር ነበርና፤ ሞትም ይከተለው ነበርና።”[2]

3.     አምልኮአዊ ተግባራት ሊቀርቡ አይገባም፦ ዝማሬ፣ ምስጋና፣ ጸሎት፣ ስብከት፣ ውዳሴ፣ ቅዳሴ… ከአምልኮ ተርታ የሚደመሩ ናቸውና ለእግዚአብሔር ለየትኛውም ሰው የሚቀርቡ አይደሉም።[3] በብዙዎች ዘንድ እኒህ ነገሮች ለድንግል ማርያም ይቀርባሉ፣ “ስለ ድንግል ማርያም አንሰብክም፤ ስብከታችን የተሰቀለውና አንዱ የመዳናችን ምክንያት፤ ደግሞም መድኀኒታችን ኢየሱስ ብቻ ነው”፣ ስንላቸው እጅግ ይከፋቸዋል፤ ምክንያቱም መሠረታቸውን የመሠረቱት ቃሉ በማይለው፤ በማይናገረው ድቡሽት ላይ መሥርተዋልና።

   ለክርስቶስ ምስጋና አቅርበን፤ “አትለይምና” ብለን፣ ቀጥለን ማርያምን አንባርክም፤ ይህ አለመታዘዝ ብቻ ሳይኾን፣ ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር ደባልቆ የማምለክ ባዕድና እንግዳ መንገድ ነው። እንኪያስ ቃሉን ተናገሩ እንጂ ቃሉን እጅ ጠምዝዛችሁ በግድ አታናግሩት

ማጠቃለያ

   ስለ ሌሎች ቅዱሳት አንስት ስንናገር ደስ የሚለንን ያህል፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱሷ ማርያምም ስንናገር ደስ ይለናል፤ ቃሉ ከተናገረው አናልፍም፤ በተናገረውም ላይ አንጨምርም። በሸቃጮችና በእኛ መካከል ያለው ትልቁ ገደል ይህ ነው። የክርስቶስ አገልጋዮች አይሸቅጡም፣ የሚናገሩትን የሚናገሩት በእውነትና በቅንነት ብቻ ነው፤ ቅንነት ቀጥተኝነት ነው፤ ቀጥተኝነት ኦርቶዶክሳዊነት ነው፤ ኦርቶዶክሳዊነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን ብቻ መናገርና መመስከር ነው፤ ቅዱስ ቃሉንም የምንናገረው ሰው እንደሚሰማን እያሰብን ሳይኾን፣ እግዚአብሔር እንደሚሰማንና ደስ እንደሚሰኝብን ኾነን ብቻ ነው፤ እንዲህ ስናደርግ ከእግዚአብሔር የኾነ ብቻ እንዲሰማን እናውቃለን፤ (ዮሐ. 8፥47)።

ጸጋና ሠላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

 



[1] አበራ በቀለ(አባ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት  ገጽ 152

[2] ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ፤ ምዕራፍ 42 ክፍል 8 ቍጥር  7-8 ገጽ 145

[3] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 145

7 comments:

  1. ለወንድማችን የሕይወትን ቃል ያሰማልን እርስቱን መንግስቱን ያውርስልን እድሜ እና ጤና ይስጥልን!

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን የሰማነውን በልባች ሰሌዳ ላይ ይፃፍልን

    ReplyDelete
  3. ምዕመናን እነደዚህ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን መምህራንን አያሳጣን::

    ReplyDelete
  4. ግሩም: ድንቅ: ነው: ነገር: ግን: አንተን: በሩቁ: ነው::

    ReplyDelete
  5. God bless you for sharing the orthodoxy doctrine.

    ReplyDelete
  6. God bless you for sharing the orthodoxy doctrine.

    ReplyDelete