ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ ስላለበት ኹኔታ ፍርሃት አለኝ!
ከጥቂት ዓመታት በፊት በእጅ ስልኬ ላይ አንዲት እህት ደወለች፤ አነሳሁት። ሰቅጣጭ ልቅሶና መራራርነት ከድምጿ ይነበባል። እናም ሕይወቷን መጥላቷን፣ ራሷንም ልታጠፋ መዘጋጀቷንና የመጨረሻ የመፍትሔ ዕድሏን ለመሞከር መደወሏን ነገረችኝ። ከብዙ ተማህጽኖና ምክር በኋላ ላገኛት ወስኜ አገኘኋት። ሳገኛት መርዝና ገመድ አዘጋጅታ ራስዋን ለማጥፋት ወስና የተዘጋጀች መኾኑን አስተዋልኩ። በጌታ ብርታት ክፉ ተግባርዋን እንድትተው ካደረግሁ በኋላ ታሪኳን መስማት ጀመርኩ።
የአያሌ ወንድሞችን፣ አባቶችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን ሰቆቃና ስብራት ሰምቻለሁ፤
እንደዚህች እህት ግን የማንም ሰቆቃ ሐዘን ብርቱ አይኾንም። ከስምንት ዓመቷ ጀምሮ በአባቷ በተደጋጋሚ ስትደፈር፣ እናት እያወቀች
ዝም ከማለቷ ባሻገር፣ የሚደርስባትን ስትናገር ትገርፋት ነበር። እናም በ11 ዓመቷ ከወላጆችዋ ቤተሰብ ብን ብላ ጠፋች፤ አልተመለሰችም።
አኹን ዕድሜዋ ሃያ ሦስት ነው፤ ላለፉት አሥርት ዓመታት ከኖረችባቸው አምስት ገዳማት በሦስቱ አያሌ የዝሙትና ሰዶማዊ ትንኮሳና ጥቃቶችን
አሳልፋለች። በመጨረሻ ግን በደረሰባት ጥቃት ተመርራ ራስዋን ለማጥፋት ወስና ባለችባት ቅጽበት ተገናኘን።
እንዲህ ዓይነት የሰዶማዊነትና የመደፈር ዘግናኝና ሰቅጣጭ በርካታ ታሪኮች
በመካከላችን አሉ፤ አንዳንዶች እንዲህ ያሉ ጸያፍ ታሪኮችን በአደባባይ የሚያቀርቡት፣ አሉታዊ በኾነ መንገድ እንዲስፋፋ ማስታወቂያ
ለመሥራት እንጂ መንፈሳዊና ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጠው በማሰብ አይደለም። ለዚህም የቅርብ ጊዜ ትዝታችንን ማንሳቱ ብቻ በቂ ነው።
ከኮቪድ 19 በፊት ሲፈጸም ምንም ያልተባለውን ሰዶማዊነት፣ ኮቪድ 19ን ታክኮ[አባትነትን በደፈናው በማዋረድና በማንቋሸሽ] የተሰማው
የአንድ ሳምንት ድምጽ የነገሩን አሉታዊ ማስታወቂያነት ከመሥራት ውጪ የውኃ ሽታ ኾኖ መቅረቱን ማሳያ ነው።
በዚህ ረገድ ባለፈው ማክሰኞ፣ ግብረ ሰዶማዊነትን ከማስፋፋት አንጻር ፖፕ
ፍራንሲስ የተናገሩት ንግግር እንደ ተራ ነገር የሚታይ አይደለም። ሰውየውና እርሱ የሚመራት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአለም አብያተ
ክርስቲያናት ማኅበር አባል ናቸው። በበጀትና በአባላት ብዛትም የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። ኅብረቱን ከጀርባ ኾነው ከሚዘውሩት መካከልም ቀዳሚውን ስፍራ የያዙ ናቸው።
በዚህ ኅብረት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት አባልና ተባባሪ
ናቸው። እንዲያውም ኢትዮጵያ ከመሥራቾቹ አንዷ ናት።
ፖፑ፣ ግብረ ሰዶማዊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥዩፍና ርኩስ መኾኑን ጠፍቶአቸው
የተናገሩትን አልተናገሩም፤ አስበውና በዒላማ ተናገሩ እንጂ። ሰዶማውያን በምድር ላይ ያሉ ታላላቅ የሚዲያ ሰዎችን፣ የፊልም ከያንያንን፣
ሃብታሞችን፣ ታዋቂ የተባሉ ሰዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ በተለያዩ ማኅበረ ሰቦች የሚታመኑ ቅዱሳት ስፍራዎችን፣ … ኾን ብለው
በማጥመድ የታወቁ ናቸው። ለዚህም ተግባራቸው ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ገፍ ገንዘብ በማቅረብና ርካሽ የኾኑ የማጥመጃ መንገዶችን
በመጠቀም ነው። ፖፑ የዚህ ርካሽ ሰለባ የኾኑ ናቸው ብዬ በጽኑ እፈራለሁ።
የእኛስ ቤት?
እውነት ለመናገር ፖፑ ይህን ለመናገር በአንድ ጀንበር እዚህ ደረጃ አልደረሱም፤
አያሌ መንገዶችን አሳብረው መጥተዋል። የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎቻችን ፖፑንና ካቶሊካዊቷን ቤተ እምነት ኮነንን እንጂ ቤታችንን አልተመለከትንም፤
በርግጥ የፖፑን እብደት አለመገሰጽ በራሱ የከፋና ሌላ ዕብደት ነው። ግን በእውኑ የእኛስ መንገድና ቤት የጠራ ነውን?
በአዲስ አበባ የምናውቃቸው ውብ ጉባኤያት ግብረ ሰዶማዊ በኾኑ አገልጋዮች
ስለ መበተናቸው ብዙዎች እማኞች አለን፤ እኒህ አገልጋዮችን የሚያሰለጥኑ ወይም ወደዚህ ነውርና ዓመጽ እንዲገቡ የሚያደርጉ አንዳንድ
የገዳም አስተዳዳሪዎችና የአድባራት አለቆች፣ በቤተ ክህነት ታላላቅ ስፍራዎች ላይ የተቀመጡ፣ መጋቢዎች፣ ፓስተሮች፣ ሰባክያን …
ስለ መኖራቸው ከሹክሹክታ ያለፈ ድምጽ አለ። እንደምንሰማው በሩቅ ያለ ሳይኾን ከብብታችን፣ ከዓይናችን ሽፋሽፍት ሥር ያለ ዓመጽ
መኾኑን አብዛኛዎቻችን ያስተዋልን አይመስልም።
የቫቲካን ተጽዕኖ
በአብያተ ክርስቲያናት!
ቫቲካን፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውስጥ ተጽዕኖ በመፍጠርና አሉታዊ
የኾኑ ውሳኔዎችን አስገዳጅ በኾነ መልኩ በማስፈጸም በታሪክ ፊት ዛሬም ድረስ ተወቃሽ ናት። ይኸው ባህርይዋ ዛሬም አብሮአት ያለ
ይመስላል። እናም ሰዶማዊነትን በመደገፍ እንዲህ ባለ መልኩ ስትቀርብ፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት “አይደለም፤ አንቀበልም፤ አይኹን!”
ለማለት ምን ያህል ዝግጁዎች ናቸው? የኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰዶማዊነትን በዝምታ እንድትደግፍ
ተጠይቃ “እምቢ” በማለትዋ ከውጪ የሚደረግላት ድጋፍ መቆሙን ሰምቻለሁ።
ነገር ግን ኹሉም አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ አቋም በወጥነት ለመያዛቸው
ምን ዋስትና አለ? ነገሩን በፖፑና በሚመሩአት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ላይ ጣት በመቀሰር ማለፍ የሚቻል አይደለም። ይልቅ በገንዘብና
በተለያዩ መደለያዎች የሚቀርቡትን ቫቲካናዊ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋምና ለመቃወም፤ አሻፈረኝ ለማለት ትውልድንና ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ
በቅዱስ ቃሉ ማስታጠቅ፤ ተግቶ መጸለይ ይገባል።
እንዲህ ያለ አቋም በመንግሥት ረገድ የተለየ ተአምር ካልተከሰተ በቀር ይኖራል
ብዬ አልጠብቅም። ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ የመንግሥት በትረ ሥልጣን የጨበጡ ታላላቅ ባለሥልጣናት “በመብት ሰበብ” ሰዶማዊነትን
ሲደግፉ አይተናልና። ከመንግሥት ባሻገር ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና የወንጌላውያን አማኞች ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም ከፈለጉ፣ አንዳንድ ገዳማትንና ጳጳሳትን፣ የአድባራት
አስተዳዳሪዎችን፣ መጋቢዎችን አገልጋዮችን መፈተሽና ማጥራት ይገባቸዋል።
ማጠቃለያ
ቤተ ክርስቲያን ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ በገዛ ልጆችዋ የምትፈተንበት
ዘመን ላይ ናት። ቄሳራዊ ፖለቲካ “በልጆችዋ” ይዘወራል፣ ሰዶማዊነትን “ጳጳሳቱ” በድጋፍ ያጅቡታል፣ ለእግዚአብሔር መንግሥትና ለመንጋው
ግድ የለሽ የኾኑ አገልጋዮች ዙርያዋን ከብበዋል፤ … እናም ከየትኛውም ዘመን ይልቅ ብርቱ ፈተና ተጋርጦባታል። ፊቷንም፤ አቅሟን
ኹሉ ወደ ተሰቀለው መሲሕ፣ ወደ ቅዱስ ቃሎቹ፣ ወደ መሪው መንፈስ ቅዱስ፣ የፍቅር አባት ወደ ኾነው አብ በመመለስ ለኀጢአተኞች የመዳኑን
ወንጌል በመመስከር ካልተጋች በቀር፣ በገዛ ልጆችዋ መዋረዷ አይቀሬ ነው።
ቤተ ክርስቲያን ዓለምን ለሚወቅሰው መንፈስ ቅዱስ መታዘዝና መሸነፍ
አለባት። ኀጢአትን በግልጥ መጠየፍና መቃወምን ገንዘብ ማድረግ፣ ለሳቱ ኀጢአተኞች መማለድ ይገባታል፤ ይህን ባታደርግ ግን ጌታ በየትኛውም
ዘመን ቅሪትና የራሱ ትውልዶች አሉት፤ እርሱ ምድሪቱን ያለ ምስክር ከቶ እንዳይተው እናምናለንና። ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ
ይብዛላችሁ፤ አሜን።
Yasazenael
ReplyDeleteAmen
ReplyDeleteamen
Amen
Zemanh Yebarkiiiiiiiiii We LOve U More&more