Wednesday 23 September 2020

የአሸናፊ ገብረ ማርያም(ቀሲስ) “ጐስአ ልብየ ቃለ ሰናየ” ማርያም ናትን?

 Please read in PDF

መግቢያ

  አሸናፊ ገብረ ማርያም(ቀሲስ) ጥቂት የማይባሉ መዝሙሮችን “ሠርቶ”፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ጀምሮ ተጠቅመንባቸዋል፤ ታንጸንባቸዋል፤ አምልከንባቸዋል። ለጌታ የሚሠራቸው መዝሙሮች እጅግ መሳጭና ትኵረትን ቀንብበው የሚይዙና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው ናቸው። በዚህ ረገድ ከማከብራቸውና ከምወዳቸው ዘማሪዎች መካከል አንዱ ነው።

ነገር ግን ለያህዌ የተነገረውን ቅዱስ ቃል ለውጦ፣ “ስላደረገችልኝ ለእመቤቴ ምን እከፍላታላሁ?” ያለውን አዝማሪ፣ “ትክክል አይደለም” ብለን፣ “ጐስአ ልብየ ቃለ ሰናየ”[ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ (መዝ. 45፥1)] ተብሎ ለመሲሑ የተነገረውን ቅዱስ ቃል አጥፎ፣ “ለማርያም መዘመር” ትክክል አይደለም አለማለት አባይ መዛኝነት ነው፤ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊም፤ አድሎአዊነትም ነው፤ (ምሳ. 11፥1)። ቃሉም በግልጥ፣ “እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር።” ብሎ የሚናገረው ለመላው የሰው ዘር[ለሚያምኑትም፤ ለሚያገለግሉትም] ነውና፤ (ምሳ. 30፥6)።

ተግዳሮት

    በዕድሜና በ“አገልግሎት ዘመን” የሚበልጡንንና “አያሌ ተከታይ ያላቸውን” አገልጋዮችን መውቀስና በአደባባይ የሠሩትን ነውርና ስህተት “ትክክል አይደላችሁም” ብሎ መናገርም ኾነ መጻፍ፣ ራስን በስለት ላይ የመቸከል ያህል ምላሹ ተቃውሞውና ጠንካራ ጥላቻ አለበት። የአገልጋዮቹም በእንዲህ አይነት ተከታዮች መከበብ በራሱ ያስፈራል። ብዙዎች ስህተት በአደባባይ የሚሠሩና ሌሎችን በስህተት መንገድ የሚመሩ አገልጋዮችን ነኹልለው መከተላቸው ሳያንስ፣ አመንነዋል ያሉት ወንጌል ስህተትንና የቃሉን ተቃራኒ ሐሰቶችን ኹሉ እንደሚጠየፍ አለማወቃቸው ድንዛዜአቸው ጽኑ መኾኑን ያሳያል።

  ከተገለጠ የስህተት ትምህርት ይልቅ ተመሳስለው የተሠሩና በጽድቅ እርሻ ላይ የተቀረቀሩትን ወይም የተዘሩትን የስህተት ትምህርቶችና ልምምዶችን መለየት፣ ብርቱ የጸሎት ትጋትና የቅዱስ ቃሉ መትሮ ሰያፊ ወይም ከፋይ እውቀት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በተለይም ለእግዚአብሔር የተነገሩ ቅዱስ ቃላትን እንደ ወረደ፣ ለቅዱሳን ሰዎች ወይም ኀይላት መስጠት፣ የእስራኤል ልጆች በአንድ ወቅት “ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የአምልኮ ዕቃዎችን” ከሠሩት የከፋ ስህተት በምንም አይተናነስም፤ (2ነገ. 23፥4)። በርግጥም ትላንት በድርሳናት፣ በገድላት፣ በመልክዐ መልክእ፣ በተአምራት ስም ተታልለን፣ ዛሬ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ ውጭ በተጠቀሱና በተተረጎሙ ጥቅሶች ቅዱሳንን ለማምለክ መቋመጥ የማሰናከያ ዓለት በትውልድ ፊት ማኖር ነው።

የአሸናፊ(ቀሲስ) “ጐስአ ልብየ…”

አሸናፊ በቍጥር ስምንቱ “በዘመረው የማርያም መዝሙር” እንዲህ ይላል፣

“ጐስአ ልብየ ቃለ ሰናየ

በአንቺ የተደረገው ይጨረሳል ወይ?

ስምኦን በመቅደስ ሲያገኝሽ

ልጅሽን ታቅፎ ባረከሽ

ለብዙዎች መውደቅ መነሣት

ድንጋይ ነው ማዕዘን ምልክት

ስለዚህ ነው ድንግል ብጽዕት መባልሽ

እኔም ተባረኩኝ ሳመሰግንሽ።

ያንን ቅዱስ ወንጌል ሲነግርሽ

ይኩነኒ ብለሽ ተቀበልሽ

ሆነልን ደስታ መጽናናት

ወደ ሰማይ ዐለም መጠራት…”

1.      መዝሙረኛው “ጐስአ ልብየ ቃለ ሰናየ”[ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ (መዝ. 45፥1)] ብሎ የዘመረው በኋላ ሊመጣ ላለው መሲሕ ነው፤ አሸናፊ(ቀሲስ) ግን ቃሉን ገልብጦ የተጠቀመው ለማርያም ነው። ይህ እጅግ ጸያፍ በቃሉ ላይ የመጨመር ድፍረት ነው። ቃሉ የተነገረው እግዚአብሔርን በንጉሣዊ ክብር ከማክበር አንጻር የተዘመረ ውብ ዝማሬ ነው፤ መዝሙረኛው በንጉሡ የልብ መልካምነት መደሰቱን፤ የንጉሡም ቃሎች በጸጋ የተዋቡና የሚያስደስቱ መኾናቸውን በደስታ ሲናገር እናስተውላለን።

   የዕብራውያን ጸሐፊ በምዕ. 1፥8-9 ላይ ከዚሁ ከመሲሑ መዝሙር በመጥቀስ[መዝ. 45፥6-7]፣ ለጌታ ኢየሱስ ዝማሬን አቅርቦአል፤ ስለዚህም መዝሙረኛው ሊመጣ ያለውን መሲሕ በማሰብ የዘመረለትን መዝሙር ወስዶ ለማርያም ማቅረብ በቃሉ ላይ ማመጽ ነው።

2.     ሌላው በግጥሞቹ ውስጥ አዝማች የኾነውና “ስለዚህ ነው ድንግል ብጽዕት መባልሽ” የሚለው ሐረግ፣ ረባሽ አምልኮ አስገባሪ ቃል ነው። ስምኦን አረጋዊ ስለ መሲሑ፣ “ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥” (ሉቃ. 2፥34-35) ብሎ የተናገረውን ቃል ጠቅሶ፣ በማሠሪያው ረባሹን ሐረግ ይጠቅሳል፤ በመጨረሻውም ማሠሪያም፣ “እኔም ተባረኩኝ ሳመሰግንሽ።” በማለት ሌላ ባዕድ ፍጡራዊ አምልኮ በማቅረብ ያሞጋግሳል።

   ግጥሞቹ፣ ስለ ልጁ ያወሩና ክብር ወሳጅዋና ባርካ ምስጋና ተቀባይዋ ማርያም እንድትኾን መደረጉ ታስቦበት እንጂ በቸልታ የተፈጸመ ተግባር አይደለም። ልጁ ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ኾኖ መሾሙ፣ ክብርን ለእርሱ ብቻ እንጂ ለማርያም እንድናቀርብ ወይም “ስለዚህ” ብለን ማርያምን እንድናመሰግን የሚያደርገን አንዳችም ምክንያት አይኖረውም። ወደ ሰማይ ዓለም ለመጠራታችን ምክንያታችንም፤ የጠራን ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ከማርያም ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም።

3.     ይህ ብቻ ሳይኾን የአሸናፊ(ቀሲስ) የማርያም “ዝማሬዎች” ሌሎችም እጅግ የሚያሳፍሩ አሉ። ነገር ግን ለማርያም የዝማሬ አምልኮ ማቅረብ በራሱ የተሳሳተና ከመጽሐፍ ቅዱስ ያፈነገጠ ነው፤ ይህ እየታወቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማስመሰልና ስለ ኢየሱስ እየዘመሩ ቆይተው፣ “ስለዚህም እናመሰግንሻለን” ማለት፣ የመገበውን መጋቢ ገፍቶ ያልመገበውን መጋቢ “ምግቤ፤ ምግቤ” እያሉ የማሞገስ ያህል የዕፍረት ሙገሳ ይኾናል።

   ከሰዎች ተወዳጅነትን ለማግኘት የእግዚአብሔርን ቃል መሸቀጥ አይገባም፤ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ተናግረን ቢጠሉን እጅግ መልካም ነው፤ ሰዎች እንዲወዱንና ዕርዳታቸው እንዳይነጥፍብን፣ አቦ አቦ እንዲሉን፣ ደጋፊነታቸውን እንዳናጣ … በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብንሸቅጥ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። እንዲህ ያለ ተግባር ፍርዱ ጽኑ፤ ኵነኔው አስፈሪ ነው። እናም አሸናፊ(ቀሲስ) ሆይ፤ እንዲህ ያሉ አያሌ ሥራዎችን ስትሠራ ዝም ያሉህ ባልንጀሮችህ ወደውህ አይመስለኝም፤ እኩያዎችህ ይህን ነግረውህ ለምን እንዳላስተዉህ አላውቅም፤ ግን መልካም አይደለምና በማርያም ስም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀስህ ቃሉ የማይለውንና የማይፈቅደውን አምልኮ ከማቅረብ ራቅ! ደግሜ እልሃለሁ፤ እውነትን ሰውተን በግብዝነት ፍቅር ከመዋደድ፣ እውነትን ተናግረን መላለሙ ቢጠላን እጅግ ይሻለናል!

ማጠቃለያ

   በማናቸውም መንገድ አምልኮ የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ዝማሬ ደግሞ አምልኮ ነው፤ ለእግዚአብሔር በቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ኾኖ፣ በማናቸውም መንገድ የሚቀርብ የቱም ነገር[ጸሎት፣ ስግደት፣ ዝማሬ፣ እልልታ፣ ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ሙገሳ …] አምልኮ ነውና። ስለዚህም ከእግዚአብሔር በቀር ለየትኛውም ፍጡር መዘመር እርሱ ጣዖት አምልኮ ነው። በሰማይም ሆነ በምድር ከእግዚአብሔር በቀር ለማንም ዝማሬ ማቅረብ አይገባም፤ እናም አምልኮአዊ ምንዝርና ወይም ሴሰኝነት እንድንፈጽም የምታደርጉ ወይም የምታለማምዱ አገልጋዮች ሆይ፤ እንዲህ ካለ ጸያፍ ተግባር ተጠበቁ፤ አንዱን ቅዱስ፣ ከጥንት የነበረውን ጻድቅ፣ ብቻውን አምልኮና ክብር የሚገባውን ቅድስት ሥላሴን ብቻ ባርኩ፤ ጸጋውን ያትረፍርፍልን፤ አሜን።

 


5 comments:

  1. አሸናፊ ሁሌም ያሳዝነኛል

    ReplyDelete
  2. ለምን ግን እንዲህ ያደርጋል? እውነት የሚመክረው አቶ ነው

    ReplyDelete
  3. ከሰዎች ተወዳጅነትን ለማግኘት የእግዚአብሔርን ቃል መሸቀጥ አይገባም፤ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ተናግረን ቢጠሉን እጅግ መልካም ነው፤

    ReplyDelete
  4. A rise and Shine spiritual message

    ReplyDelete
  5. ንገራቸው ግራ ገብትዋቸው ግራ የሚያጋቡትን

    ReplyDelete