Wednesday 25 March 2020

ለሚበልጠው ብልጥግና ትጉ!

Please read in PDF
   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ለጤናማ ብልጥግና ትጉ፣ ለጤናማ ብልጥግና መትጋት ይገባናል” የሚሉ አባባሎች፣ በመካከላችን አሰምተው ሲነገሩ እየሰማን ነው። አባባሉ ጤናማ ቢመስልም፣ በውስጡ ግን ስውር መደላድል የለውም ማለት፣ እጅግ ተላላነት ሊኾን ይችላል። “የብልጥግና ወንጌል” መምህራንና ደቀ መዛሙርት ዋና ቅኝታቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስን በመታከክ ለብ ያሉ መልእክቶች ማቅረብና ማስተላለፍ እንደ ኾነ መዘንጋት አይገባንምና።  ለብ ያለ ነገር ደግሞ ለፍጥረታዊው ሰው እጅግ ከመለድለዱም ባሻገር፣ ቀላልና ሰፊ ኹሉም ለመጓዝ የሚያመቸው መንገድ ነው።


  መቼም ስለ ማናቸውም ነገር ስናወራና ስንወያይ መሠረታችንና መነሻችን፣ ስለምናወራውና ስለምንወያየው ነገር “ጌታችን ኢየሱስ ምን አለ? በዚህ ዙርያስ ኑሮውና ልምምዱስ ምን ነበር?፣ የቤተ ክርስቲያን አእማድ ነቢያትና ደቀ መዛሙርትስ ምን አሉ? ኑሮውና ልምምዳቸውስ ምን ነበር? ኦርቶዶክሳዊው የሐዋርያውያን አበው ሕይወትና ልምምድስ ምን ይላል? ትምህርታቸውስ ምንድር ነው?” የሚል መኾኑን መዘንጋት የለብንም።  ከእነርሱ ያልተቀዳ የትኛውም አስተምኅሮ፣ አምልኮአዊ ልምምድና ሌሎችንም ተግባራት፣ የጊዜ ቆይታቸው ምንም ረጅም ቢኾን እንኳ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።

ብልጥግና ምንድር ነው?

  ብልጥግና ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ሀብት የሚነገር ቃል ነው፤ በውስጡ ንብረትንና የገንዘብ ብዛትን ወይም ሥጋዊና መንፈሳዊ ችሎታን፣ ብቃትን ኹሉ ሊያካትት ይችላል፤ “አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ።”፣ “በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።” (ዘፍ. 13፥2፤ ኢያሱ 22፥8) እንዲል፣ በሥጋዊ ትርጉሙ ካየነው ብእላዊ ወይም ቍሳዊ ሀብትን አመልካች ነው።

   ስለ መንፈሳዊ ብልጥግና ደግሞ “በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በእርሱ በልጽጋችኋል፤ ስለ ክርስቶስ የመሰከርንላችሁም በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል።” (1ቆሮ. 1፥4-6 ዐመት)፣ “እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ …” እንዲል ስለ መንፈሳዊ ብልጥግና በትኵረት ይናገራል፤ (2ቆሮ. 8፥7 ዐመት)።

   መጽሐፍ ቅዱስ ትልቁ ትኵረቱ ብእላዊ ብልጥግና አይደለም፤ መንፈሳዊና ዘላለማዊውን ብልጥና እጅግ መፈለግ እንዳለብን ጮኾ ይናገራል እንጂ።  ጌታ ኢየሱስ በግልጥ ቃል የተከተሉትን ሕዝቦች ኹሉ ያይደለ፣ አምነው የተከለቱትን ደቀ መዛሙርት እንዲህ አላቸው፤

   ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?
እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። (ማቴ. 6፥25-33)
   ምድራዊ ብልጥግና በእግዚአብሔር ልግስና ለሁሉ የሚሰጥ ነው፤ በዚህ ኀላፊ ዓለም ላይ እግዚአብሔር ኀላፊውን ነገርና ብልጥግናን ለኀጥአንም ለጻድቃንም ሰጥቶአል፤ ይልቁን አማኝ ኾኖ የእግዚአብሔር በረከት በኾነው በምድር በረከት የተባረከ ቢኖር፣ እርሱ ለሌሎች ቢያካፍልና ቢሰጥ መንፈሳዊ በረከትን ያገኛል፤ “አንዱ በለጋስነት ይሰጣል፤ ሆኖም ይበልጥ ያገኛል፤ ሌላው ያለ መጠን ይሰስታል፤ ግን ይደኸያል። ”፣ “እንግዲህ፣ በዚህ ዓለም ሀብት ካላታመናችሁ፣ እውነተኛውንማ ሀብት ማን አደራ ብሎ ይሰጣችኋል?” (ምሳ. 11፥24፤ ሉቃ. 16፥11)።  ሀብታም የተሰጠውን እንዳልተቀበለ ቢረሳና በሀብቱ መመካትና መኩራት ቢጀምር ግን ብርቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል

በመጠን ኑሩና ለሚበልጠው ትጉ!

   እንዲያውም ባለጠግነት ማሰናከያ ሊኾን ስለሚችል፣ መጠነኛ ሀብት እጅግ መልካም እንደ ኾነ መጽሐፍ ቅዱስ አበክሮ ይናገራል፤ አማኞች ባላቸው ሀብት ብቻ መደሰት እንጂ፣ ሀብትን መመኘት እንደ ሌለባቸውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” (1ጢሞ. 6፥7-9፤ ዕብ. 13፥5)

  በተለይ ደግሞ አማንያንን በማታለልና ቤተ ክርስቲያንን መሥርተው ሕዝብን የሚመዘብሩ አገልጋዮች፣ በመጨረሻው ከኀጢአተኞች ጋር በአንድነት ይፈረድባቸዋል።  ዛሬ እግዚአብሔርን የማይፈሩ አያሌ ኀጢአተኞች ሀብታሞች እንደ ኾኑ እናስተውላለን፤ እንደ ኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናትም ለሌላው ቆርሰው የማይሰጡና የመዘበሩትንና የሰበሰቡትን ብርና ወርቅ በባንክ አጠራቅመው፣ ወለዱን የሚበሉና ሀብትን በማከማቸት የታበዩ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉም እናውቃለን። ነገር ግን ለሚበልጠውና ከእናንተ ፈጽሞ ስለማይወሰደው ብልጥግና ስለኾነው፣ መንፈሳዊ ሃብት ትጉ፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።


No comments:

Post a Comment