Saturday 28 March 2020

ስለ ኮሮና የእግዚአብሔር ልብ ምን ይላል?!


 
   እግዚአብሔር ይህችን ምድር በእሳት ትኩሳት ሊያሳልፋት ቀጠሮ የያዘላት እንጂ ዘላለማዊና ቋሚ፣ ደስታዋም የማይከስም ኾና የተሠራች አይደለችም፤ ምድርና ሥጋ በእርጅና ይያዛሉ፤ ያረጃሉ፣ ይጃጃሉ፣ ይገረጅፋሉ፣ እንደ ብራናም ተጠቅልለው ያልፋሉ፤ እንደ አበባ ይረግፋሉ፣ እንደ ቅጠል ይጠወልጋሉ፣ እንደ ሣር ደርቀው ይጠፋሉ (1ጴጥ. 124) የእግዚአብሔር ቃል ግን አይሻርም፤ ደግሞም ለዘላለም ጸንቶ ኗሪ ነው፤ (1ጴጥ. 125 ዮሐ. 1035) ከቅዱስ ቃሉ የሚመዘዙት ፍርዱ ደግሞ እውነትና ቅንነት የከበባቸው፣ እጅግም ጣፋጭ ናቸው፤ (መዝ. 199-10)





  እንዲህ ባለው፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሕይወቱን የመሠረተ አማኝ ደግሞ፣ ጌታ ኢየሱስ እንደ ተናገረ፣ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።” (ማቴ. 724) እግዚአብሔርን የሰማና ደግሞም በመታዘዝ የታመነበት ሰው፣ እርሱ በረከትና ሕይወት ይከተሉታል፤እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።” (ኢሳ. 3316) ይህ የተነገረው፣ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔርዘንድ ነው፤ (ኢሳ. 2829) እርሱ ጌታችን በኃይሉ ታላቅ፣ በጥበቡም ስፍር የሌለው ነው፤ (መዝ. 1475)

  እግዚአብሔር ስለ ኮሮናም ይኹን ስለ የትኛውም የዓለም ንውጽውጽታ የማያረገርግና የማይረግብ፣ የማያወላውልና ጽኑ ሉዓላዊ ጌታ ነው፤የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝ. 3311) አዎን! “የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።” (2ሳሙ. 2221) ቃሎቹ እውነት፣ ምክሩ ፍጹምና ቅን የኾነው ጌታ፣ አደራረጉ ቅዱስ፤ ፍጻሜውም ጣፋጭና እጅግ የተወደደ ነው። የኢየሱስ ቃሎች የሚበሉ፣ ከማርና ከወለላ የሚጣፍጡ፣ ሐሤትና የልብ ደስታ የሚሰጡ፣ ደግሞምመንፈስና ሕይወትምናቸው፤ (መዝ. 1910 ዮሐ. 663 ኤር. 1516)

   ምክሮቹና አደራረጉ ጣፋጭና የልብ ሐሴትን የሚመሉት የእግዚአብሔር ቃሎች፣እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ።” (ሮሜ 1122) ይላል። ሉዓላዊው ጌታ ቸርነቱን ስንዘነጋ ጭካኔውን ይገልጥብናል፤ ጭካኔውን ብንዘነጋ ደግሞ ገደብ የለሽ ፍቅሩን በእኛ ላይ በመግለጥ ይታወቃል። በዚህም መራርነትንና ጣፋጭነትን በእኛ በመግለጥ ይታወቃል። መግቦቱ በዚህ እንዴት ተካካይ እንደ ኾነም እናስተውላለን።

   እውነተኛ መጋቢና መምህር ነውና፣ ከምሬት በኋላ እንዴት ማጣፈጥ እንደሚቻለው ያውቃል፤ ኑኃሚን የተናገረችውን አስተውሉ፣ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ ሃሳቡም ለተጠሩት የትኛውም ነገር ለበጎ ነውና፣ ምሬትንና ደስታን፣ ማጣትና ማግኘትን፣ በሕይወታችን የሚተግብረው እርሱ ነው፤ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።” (2ቆሮ. 69-10) ይህንእንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ” (ኤፌ. 111) እርሱ ነውና፤ ምክንያቱም እርሱ፣ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።ይላልና (ማቴ. 1029)




    አዎን! ያለ እርሱ ፈቃድ በእኛ ላይ የሚኾን ምንም ነገር የለም፤ ጣፋጭነትም ቢኾን ምሬት፣ ደስታም ቢኾን ሐዘን፣ ስብራትም ኾነ ፈውስያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚከናወን ነገር የለም። የፈቃዱ ማዕከል ደግሞ ክርስቶስ ብቻ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም፤ ሰይጣንም፣ ተፈጥሮም፣ በኃጢአት የተመላውም ዓለም፣ መሪዎችና ኃያላንም በዚህ ጉዳይ ሉዓላውያን አይደሉም። እንደ ፈቃዱና እንደ ዐሳቡ የሚሠራውና የሚያደርግ፣ የሚመራና የሚመግብ እግዚአብሔር ብቻ እንደ ኾነ፣ በልጁ ያመንን ኹላችን እናስተውላለን። አምነንው ተከትለነዋልና ደግሞም ምሪቱን በእውነት ይሰጠናል።

 
እርሱ ፍጥረተ ዓለሙን ወይም መላውን ተፈጥሮ ኹሉ ማዘዝ ይቻለዋልና፤ (ማቴ. 826) ደግሞ እግዚአብሔር የትኛውንም በጎ ይኹን ክፉ ነገር፣ የዕቅዱ ማስፈጸሚያ አድርጎ ሊጠቀመው እንደሚችል እናስተውላለን፤ እግዚአብሔር የአይሁድንና የጲላጦስን ክፋትና ጭካኔ ለራሱ ዓላማ፣ እንዴት እንዳደረገው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ሐዋ. 427) አዎ! ኹሉን ተግባር ለራሱ ዕቅድ ማስፈጸሚያ እንደሚጠቀመው እናስተውላለን፤ እግዚአብሔር ናቡከደነጾርንም፣ የአሦርንም ቂሮስ እንዴት እንደ ተጠቀመበት አስተውሉ፤ (2ዜና. 3622 ዕዝ. 11 ኤር. 259 276) ኮሮናንም እንዲሁ። እርሱ ኹሉንም በዓላማ ያደርገዋል፤ ሥራው እውነተኛ ነውና፤ (ዘዳ. 324)

  “
አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት…” ምን እንላለን? (ፊልጵ. 38) እርሱ ሳይሳሳት ኹሉን ያደርጋል፤ ደግሞም ርኅራኄው ከቶ አያልቅም፤ ርኅራኄውና ምሕረቱ ከሕይወት እጅግ ይሻላል፤ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ፦ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፦ እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች።” (ሰቆ. 321-24) አሜን ተስፋችን ሆይ እንታመንብሃለን።

(
መነሻ የጽሑፍ ዐሳብ ጆን ፓይፐር)

1 comment: