Monday 30 March 2020

የገነነ ምሕረት!

በምድራችን ላይ እጅግ አያሌ ተላላፊ በሽታዎች ተነስተዋል፤ እስካሁን ግን ከ1918 እስከ 1919 ዓመተ እግዚእ፣ የዓለማችንን 50 ሚሊየን ሕዝብ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ፤ እንደ ቅጠልም  ያረገፈ፤ በH1N1 Virus መነሻነት የተነሳውና “Spanish flu” በመባል እንደሚታወቀው መረርሽኝ ያህል የተነሣ የለም፡፡ በጊዜው የዓለማችን አንድ ሦስተኛው የሚያህለው ማለትም፣ 500 ሚሊየን ሕዝብ ገደማ በቫይረሱ ተጠቅቶ ነበር፤ ከዚህ ቁጥር ውስጥ ደግሞ 50 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ሞቶ ነበር፤ የዚያኔ በአሜሪካ ብቻ 675 ሺህ ሕዝብ ያህል አልቆባት ነበር፡፡


   ከዚህ ጊዜ ቀደም ብሎና ከዚህም በኋላ ይኸውም፣ ከ1815 እስከ 1975 ዓመተ እግዚእ ማለትም ዓለም በወረርሽኙ፣ በአንደኛውና በኹለተኛው የዓለም ጦርነት በረገፈበት ጊዜ፣ ወደ 5 ቢሊየን የሚጠጋ መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ በዓለማችን ላይ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አታሚ ማኅበራት ተሰራጭቶአል፡፡ እኒህን ነገሮችን ሳስብ ለዛሬው ለእኔ የሚቀርልኝ ብርቱ መልእክት፣ ሰው ምን ያህል እጅግ ዓመጸኛ የማይታዘዝ መኾኑንና እግዚአብሔር ግን እጅግ ገናና ምሕረት ያለው አምላክ መኾኑን ነው፤  ዛሬም እውነታው ይኸው ነው፤ እጅግ ባልታዘዝን መጠን በራሳችን ስተን እንጠፋለን፤ እግዚአብሔር ግን ስህተታችንን አልፎ እየሠራ፣ ኀጢአታችንን አልፎ እየመጣ … ዛሬም በቸርነቱ ጠብቆን አለን፤ እንኪያስ፦ “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራን ሳናውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት እንንቃለንን?” (ሮሜ 2፥4) ጌታ ሆይ፤ መመለስን ስጠን፤ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment