Please read in PDF
የዓቢይ ጾም አራተኛው ሳምንት ስያሜው መጻጉዕ ነው፤ ትርጉሙ በ ቁሙ ጐባጣ ማለት ነው። የስያሜው ታሪክ በቀጥታ የተያያዘው በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.
5 ላይ ያለውን ታማሚ ሰውን ማዕከል ያደረገ ነው። ታማሚው ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል ሕመምተኛ የነበረ ሰው ነው። ሕመሙ ምን
እንደ ኾነ አልተጠቀሰም፤ ነገር ግን ጽኑ ሕመም መኾኑ አይካድም። በኢየሩሳሌም፣ በበጐች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች
የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ ወይም ቤተዛታ ተብላ በምትጠራው የመጠመቂያ ስፍራ፣ ይህ መጻጉዕ ሰው ለሠላሳ ስምንት ዓመታት
ያህል ፈውስን ሲጠብቅ ኖሮአል።
ፈውሱንም
ይጠብቅ የነበረበት መንገድ እጅግ አታካችና የሰውን ዕርዳታ የሚያሻው ነበር፤ ይኸውም “የመጠመቂያውን ውኃ ዐልፎ ዐልፎ መልአኩ መጥቶ
ሲመታው ወይም ሲያናውጠው”፣ ከኹሉ ቀድሞ የሚገባው ሰው፣ ከሕመሙ ኹሉ ይድን፣ ይፈወስም ነበር። ይህን ለማድረግ ደግሞ ይህ ሰው፣
አንዳችም የሚረዳው ሰው አልነበረውም ነበር፤ ሰው በማጣቱ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ውኃው ሲናወጥ፣ ሰው ቀድሞት ይገባ ነበርና፣ ለዓመታት
ሕይወቱ እንዲህ ቀጥሎ ነበር።
ኹሉን
የሚተካ፣ ልብን የሚጠግን፣ በፈረሰው ቅጥር በኩል የሚቆመው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለዚህ መጻጉዕ ደረሰለት፤ ነገር ግን ሰውየው
በውኃውና በመንቀሳቀሱ ላይ እንጂ በኢየሱስ ላይ ምንም ዓይነት እምነት አልነበረውም። ወላጆቹ እንኳ ወደ ተዉት ሰው ጌታ ኢየሱስ
መጣ፤ ምናልባት በበሽታው ምክንያት ኹሉም ሰዎች ሸሽተውት ጥለውት ተለይተውታል፤ ጊዜው በረዘመ ቊጥር እርሱም ሕይወት ሳይታክተውና
ሳይመርረው አይቀርም፤ ሕይወት ድንግዝግዝና ጠቋራ በኾነችበት ወቅት ብርሃን ኢየሱስ ወደዚህ ሰው ተጠጋጋ።
ጌታ
ኢየሱስን አለማመን አልጋረደውም፤ የሰውየው አለማመን ኢየሱስ የሚሠራውን ሥራ ከመሥራት አላገደውም። ብንክደው እንኳ የታመነና ራሱን
መካድ የማይቻለው እውነተኛው ጌታ፣ እርሱን ወደማያውቀውና ፈጽሞ ወደማያምነው ሰው በቀጥታ መጣ። መጥቶም፦ “ኢየሱስ ይህን
ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? አለው።” ሊያድን የመጣውና፣ የጠየቀው
ተወዳጁ ጌታ ነው፤ ምሕረት ይፈስና የፈውስ ጥያቄውም ይቀርብ የነበረው ከኢየሱስ ብቻ ነበር። ሰውየው ፈዋሹ ውኃው እንጂ ኢየሱስ
እንደ ኾነ አያምንም፤ ኢየሱስ ወደ ሰውየው መጣ እንጂ ሰውየው ወደ እርሱ የመጣውን ኢየሱስን ፈጽሞ አላስተዋለውም፤ አላወቀውምም።
እንዲያውም
ሰውየው ያልተፈወሰበትንና ረጅም ዓመታትን ያስቈጠረበትን ምክንያት፣ ለኢየሱስ ማስረዳት ጀመረ፤ ኢየሱስ ይህን ኹሉ ምክንያት አልፎ፣
ከመሥራት ያገደው ነገር አልነበረም። የሰው አለማመን እግዚአብሔርን ወደ ሰው ከመምጣት አያግደውም። አዳም ያልታዘዘውን አድርጎ በእግዚአብሔር
ላይ ባመጸ ጊዜ፣ እግዚአብሔር በገነነ ምሕረት፣ “ወዴት ነህ?” እያለ ፍለጋ እንደ መጣ አንዘነጋም። የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት
ከሰው ልጅ አለማመን እጅግ ይልቃል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አልፎ የሚሠራበት ጊዜ ብዙ ነው። የእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ የመብዛትና
የመትረፍረፉ አንዱ ምክንያት፣ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” እንዲል፣
ኹሉ እንዲድኑለት እንጂ ክፋታችንን ተባብሮ አይደለም።
እግዚአብሔር በፍቅሩ መላለሙን ወዶአል፤ በክርስቶስም የመሠረተውና የገነባውም
አካል ትልቅና ኹሉን መቀበልና መሸከም የሚቻለው ነውና፣ ይህንም መጻጉዕ ከእርሱ አንዳች ሳይጠብቅ፣ ሊያድነውና ሊፈውሰው ወድዶ ወደ
እርሱ መጣ። ኢየሱስ ከብዙ በሽተኞችና ሕመምተኞች ይህን ሰው ብቻ መርጦ መምጣቱ፣ በራሱ እጅግ ያስደንቃል! እርሱ እንደ ወደደና
እንደ ፈቀደ የሚሠራ፣ አማካሪና ጥበበኛ የሌለው ልዑል እግዚአብሔር ነው። እናም ይህን መጻጉዕ ሊቀበለውና ሊፈውሰው፣ ሊያድነውም
መጣ።
መጻጉዕ ሰውዬ፣ የመፍትሔዎች ዳርቻ ጌታ ኢየሱስ በፊቱ ቆሞ፣ እርሱ ግን ዓይኖቹን
ከችግሮቹና ልቡንም “ሰው የለኝም” ከሚል ሮሮና ምሬት ሊነቅል አልቻለም። ዓይኖቹን አንዲትም ሰዓት እንኳ በኢየሱስ ላይ ሊጥል ባይወድም፣
ኢየሱስ ግን ትቶት ወይም አልፎት አልሄደም፤ ይልቁን ችግሮቹ ላይ እንደ ካስማ ተተክሎ አልነቀል ያለውን፣ እምነት አልባውንና ስለ
ነበረበት ችግሩ አንዳች ጸሎት ያላቀረበውን ሰው፣ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ
ሄደ።” ይህ እንዴት ኾነ? ሳያምንበት፣ አድነኝ ብሎ አንዳች ጸሎት ሳያቀርብ፣ እርሱን ለመቀበልና ለማወቅ ፍጹም ፈቃደኛ ባልኾነበት
… ይህ እንዴት ኾነ? ጌታ ኢየሱስ ሉዓላዊና መጋቢ አምላክ ነው።
እግዚአብሔር አብ፣ በጌታ ኢየሱስ ያረገው ሕያውና ዘላለማዊ እውነት ይህ
ነው፤ አንዳች ፍላጎትና እርባና የሌለንን ሊቀበልና ሊያድን ወድዶ፣ ከእኛ አንዳች መልካም ነገር ሳይኖር እግዚአብሔር በአንድ ልጁ
ፍቅሩን መግለጡ እጅግ ያስደንቃል! እግዚአብሔር አብ እጅግ የተወደደ አባት ነው፤ ለፍጥረቱ በመሳሳቱና በመራራቱ ብቻ አንድያ ልጁን
ለውርደትና ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ይደንቃል፤ ይህ የሚገባን ነንን?! አዎን! ለማይገባን ኹላችን እንዲሁ በሚወድድ ፍቅሩ ወደደን፤
አዎን! በልጁ ያልተወደደ ማንም የለም፤ እናንተ ኃጢአተኞች ኹላችሁ በአንድያው ልጅ ፍጹም ተወዳችኋል፤ ተፈቅራችኋልም!
እጅግ ከዚህ የላቀውና የሚያስፈራው ነገር ግን የሰውየው መዳን፣ ሳያምን፣
አንዳች ጸሎት ሳያቀርብ መፈወሱ ሳይኾን፣ የተፈወሰው ሰው የፈወሰውን ፈጽሞ አለማወቁና እንደ ተፈወሰ ፈጽሞ አለማወቁ ነው። እንዴት
የፈወሰውን ፈዋሽ አላወቀም? እንዴት ለምን ፈወስከኝ አላለም? እንግዲህ ከፈወስከኝ፣ እንዴት ምን ላድርግልህ አላለም? እንዴት ለዓመታት
ከነበረበት ሰቆቃ ነጻ ያወጣውን ሰውና ፈዋሽ ሳያውቅ ቀረ? ለዓመታት ለመፈወስ “ሰው የለኝም” ያለው ሰው፣ ሲፈወስ “ሰው አገኘኹ”
እንዴት አላለም? ችግርና ችጋር ያወራ አንደበት እንዴት ፈውስና ደህና መኾንን ማውራትና ጮኾ መናገር ተሳነው?! መዝሙረኛው ለዚህ
መልስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ታላቅ ነው! ሐሳብህስ ምን ያህል ጥልቅ ነው! ደነዝ ሰው ይህን አያውቅም፤
ነኁላላም አያስተውለውም።” እንዲል፣ ይህ ሰው በእውነት አንዳች ሊያስተውል አልቻለም።
አካላዊ ሰውነቱ ቢፈወስም፣ ልቡ ግን ጨለማና ድቅድቅ ነበረ፤ ተቀብሎ አንዳች
እንዳልተቀበለ የኾነ ሰው ነው፤ ምናለ አካላዊ ሰውነቱ ሳይፈወስ ቀርቶ፣ ልቡ በበራለት? ምናለ ኹሉን ነገር አጥቶ፣ ኢየሱስ ብቻ
በተገኘለት? ምናለ በሥጋው ከስሮ በነፍሱ ወይም በዘላለም ሕይወት ባተረፈ? አዎን! ዛሬ ላይ ምድራችን እንዲህ ባሉ በብዙ ሰዎች
ተከብባለች፤ እያዩ በማያስተውሉ፣ እየሰሙ በማያደምጡ፣ በሥጋ ጤንነት ተንበሽብሸው በነፍሳቸው ግን ሞግገው በከሱ፣ … ልበ መጻጉዕነት፣
ከአካላዊ መጻጉዕነት እጅግ ይከፋል፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ጐባጣነት አንገት ያስደፋንን በምሕረትና በፈውስህ ቀና ብሎ መሄድን ስጠን፤
አሜን።
No comments:
Post a Comment