ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ብዙ አመንትቻለኹ፤ ለተሐድሶ አገልግሎት ከማይመቹ አካሄዶች መካከል የነትዝታውን የሚመስል አስከፊ መንገድ የለም፤ እነ ትዝታው ከ“አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል” ውስጥ ራሳቸውን አዳብለዋል፤ ይኹንና ካውንስሉ በውስጡ፣ የክርስቶስን ርቱዕ ትምህርት፣ ሕይወትና ሥራ የማይቀበሉ ያሉትን ያህል፣ እነ ትዝታውም እውነተኛ የወንጌላውያን አማኞች እንዳልኾኑ የሚያሳዩ አያሌ ምልክቶች አሉ።
ከዚህ የሚከፋውና እጅግ አስቀያሚው መንገድ ደግሞ እነትዝታው “በወንጌላውያን ታዛ ተጠልለው”
ራሳቸውን “ኦርቶዶክሳዊ ሐዳስያን ነን” ማለታቸውና ራሳቸውን ኦርቶዶክሳዊ ሐዳሲ አድርገው የሚቈጥሩ ሰዎች በዚያ ኮንሰርት ላይ
ራሳቸውን “ክነው” መገኘታቸው ነው።
በግሌ ስለ ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ በቅርበት የምረዳቸው አያሌ ነገሮች አሉ፤ በኮንሰርቱ አንድም ቀን
ስለ ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ በቅንነት ያልመከሩ ሰዎችና ተቋማት “እንደ ኦርቶዶክስ ተሐድሶ” ራሳቸውን ወክለው አይቻለኹ። በጋሻው
ደሳለኝ ከጃፒና ከሲጄ ቴቪ ባለቤት ተምሮ ሲያበቃ፣ ራሱን “ሐዳሲ” ነኝ ማለቱ ያሳዝነኛል፤ ዘርፌ ከነጩፋና እስራኤል ዳንሳ
“pulpit” ላይ ሳትወርድ፣ እንደ “ኦርቶዶክስ ሐዳሲ” ራስዋን መቊጠርዋን ላየ፣ “ሐዳሲነት ገደል ይግባ” ቢል
አይፈረድበትም!
ኦርቶዶክሳዊ ሐዳሲነት ቅይጥነት አይደለም፤ ኦርቶደክሳዊ ሐዳሲነት ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞችና አገልጋዮች
ርኅራኄና ሃዘኔታ በጎደለው ቃል መዘርጠጥና ማዋረድ ጨርሶ አይደለም፤ ኦርቶዶክሳዊ ሐዳሲነት ታዋቂነት፣ ዝናን ጥቅምንና
ታይታዊነትን ማሳደድ አይደለም፤ በትዝታው ሳሙኤል ኮንሰርት ላይ ይህን ቅይጣዊነት በሚገባ አስተውያለኹ። ሚናቸውን ያልለዩና
ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶነትን ሊወክሉ የማይችሉ ግን “ራሳቸውን ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ ነን” የሚሉ፣ አያሌዎች የኮንሰርቱ ፊተኛውን
ወንበር ሞልተውት ታይተዋል፤ “ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ” በነርሱ ተወክሎ ከኾነ (ፈጽሞ አይወከልም እንጂ) እኔ ጨርሶ “ኦርቶዶክሳዊ
ተሐድሶ ነኝ” ብዬ ራሴን አልጠራውም!
ቀድሞ እንደምለው ትዝታውና ዘርፌ ዛሬም የሚያተርፉበት የአገልግሎት መስመራቸውና የማይጸጸቱበት
የአገልግሎት መንገዳቸው፣ የቀደመውና ብዙዎችን በመዝሙር ወንጌል የደረሱበት አገልግሎታቸው ነው። ይህን ስል “ኦርቶዶክስ ይኹኑ”
እያልኹ እንዳልኾነ እያወቁ አስመስለው የሚያጣምሙ ግን ጥቂት አይደሉም፤ ይኹንና ልናገር የፈለግኹት ግልጥና ለትርጒም ያልተጋለጠ
ነው። ጸያፍ ቃልና “አገለግለዋለኹ” ለሚሉት ሕዝብ የንቀትና የጥላቻ ጥግ በቃልና በድርጊት እያሳዩ የሚሰበክ፤ የሚኖርም ወንጌላዊነት
አለ ብዬ አላምንም!
ለኦርቶዶክስ የምናሳየው ተሐድሶ፣ ርቱዕ የኾነውን የክርስቶስን ሕይወት፣ ሥራና ትምህርት ባልተሸቀጠ
ዐውድ ውስጥ ነው። ዐውዱ ከብሽሽቅ የጸዳ፣ ከጥላቻ የራቀ፣ የሰከነ ጠባይን የተላበሰ፣ ከሐሰተኞች “pulpit” የራቀና የነጠረውን
የወንጌልን እውነት ሰብኮ ከመኖር የሚቀዳ ነው።
በትዝታው ኮንሰርት ላይ ከተመለከትኹት ተነስቼ፣ የወንጌል ማኅበራት ኅብረት ግልጽ መስመር ማበጀት አለበት
ብዬ አስባለሁ፤ አልያ ግን ኦርቶዶክስ ተሐድሶ “በማይወክሉትና ቁመናውን በትክክል በማይገልጡት ተላላዎች” ተወክሎ መሰደቡና መተቸቱን
በከንቱ ጌጥ እንዳያደርገው ያስፈራኛል።
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እውነተኛና ትክክለኛ ከክርስቶስ ትምህርት፣ ሕይወትና ሥራ የተቀዳ ኦርቶዶክሳዊ
ተሐድሶ በዐውዳቸውና በርቱዕ መንገድ እንዲመጣ ከሚመኙ አንዱ ነኝ! ጌታ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይራራላት፤ መንፈስ ቅዱስ በእውነተኛ
ወቀሳው ያግኛት፤ አሜን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24)
አሜን።
Sijemir ante nek sile christos le orthodox yemitastemrat endew difretachu eko yigermal sima joro kalek malet new orthodox minim yemitades neger yelatim eshi wedefitim aynoratim ezaw erasachun chalu orthodox hulem mulu nech eshi
ReplyDelete