Wednesday, 18 March 2020

ተጽናኑ፤ አጽናኑም!

Please read in PDF

   አዲስ ኪዳን በአጭር ቃል፣ ከሥጋ ሕመምና ሞት፤ ከበሽታም ይልቅ ከእግዚአብሔር አባትነት መለየትና መነጠልን የዘላለም ሞትና ፍርድ እንደሚያስከትል ያስተምራል። የሥጋ ሕመምና ሞት በአዲስ ኪዳን ትምህርት፣ ጊዜያዊና ሰው የመኾናችን ውጤት መኾኑን ብቻ የሚያመለክትም ነው። ከዚህ ባሻገር ሰዎች ባለመታዘዝ በጸኑ ልክ፣ ለኀጢአት፣ ለዓመጻና ለማይረባ አእምሮ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።




   በብሉይ ኪዳን ደግሞ፣ ነቢዩ እንዲህ ይላል፦ “…ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሠፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።” (ኢሳ. 1፥5-6) በዚህ ዓውድ መሠረት  የኀጢአት ኹኔታ በበሽታ ምሳሌነት ተገልጦ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ራሱን ከሕዝቡ ጋር ቈጥሮ፣ “የእስራኤል ቅዱስ” ተብሎ ተጠርቶ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ በሕጉና በኪዳኑ ጸንተው ከመኖር ይልቅ፣ በኀጢአት በመጽናታቸው ምክንያት ቅዱስ መኾንን ሳይፈልጉ ቀሩ።

   መቀደስን ላልፈለጉት ሕዝብ፣ እግዚአብሔር መልእክቱን ማስተላለፍ የፈለገው በቀጥታ ነው፤ በሽታ መላ ሰውነትን እንደሚመርዝና እንደሚያበላሽ እንዲሁ፣ ኀጢአትም ኹለንተናን የመበከልና የማርከስ ባሕርይ አለው፤ እስራኤል ይህ ኹሉ ኾኖ እንኳ፣ ልቧን ለመለወጥ አለመፍቀዷ እጅግ የሚያስደንቅ ነው፤ ልክ ጌታ ኢየሱስ በናዝሬት ሰዎች አለማመን እንደ ተደነቀው።

  እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ሰዶምና ገሞራ ያላጠፋውና በብዙ ምሕረትና መግቦት የታደጋት ወይም እንደ ሠራችው ኀጢአትዋ መጠን ያገኛነት የሚገባት መለኮታዊ ቅጣት ሳያገኛት የቀረው፣ በቸርነቱ ጥላ ስለጋረዳትና ስለታደጋት ብቻ ነው። እንጂ እንደ ሥራዋና ክፋትዋ የሰዶምና የገሞራ ዕጣ ለእስራኤል የሚገባ ነበር። ምክንያቱም እስራኤል የነበረችበት ኹኔታ፣  መከሩ ካለፈ በኋላ በከፍታ ቦታ በዱባ ተክል ውስጥ እንደሚገኝ ጎጆ ወይም ሰው ትቶት እንደ ሄደ የዕርሻ ማሣ ትመስል ነበርና።

   የእስራኤል ኀጢአት የሰዶምና የገሞራን ኀጢአት ይመስላል፤ ይህም ለእስራኤል እጅግ አስደንጋጭና አስፈሪ መልእክትን ያዘለ ነው፤ በእርግጥም ሰው እግዚአብሔርን ሲተው፣ ኹለ ነገሩ በምድር ካለ ኀጢአተኛ የሚለይበት አንዳች ነገር የለውም። ይህን በእውነተኛ ንስሐ በመመለስ ዕርቅና ስምም በማድረግ ምሕረትና ይቅርታውን ማግኘት እንጂ፣ በግብዝነት ራስን እውነተኛ አድርጎ ማቅረብ፣ ነገሩን ይልቅና ይብስ ያባብሰዋል፤ ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ያለውን ነገር በግልጥ ተናግሮአል።

   በአንድ ወቅት አይሁድ መጥተው በአንድ ወቅት በአደጋ ስለሞቱ ሰዎች ጠየቁት፤ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።” በማለት ተናገራቸው፤ ለሰሊሆምም አደጋ ምላሹ ተመሳሳይ ነበር። በሌላው ዓለም ላይ ክፉው ነገር የበረታው፣ እኛ ዘንድ ደግሞ እንደ ሌላው ዓለም ብርቱው ጥፋት ያላገኘን፣ የተሻልን ስለኾን አይደለም፤ ያህዌ ኤሎሂም እንዲያው ምሕረቱን ስላገነነልንና ይልቁን ፈጥነን ፊታችንን በንስሐና በይቅርታ ወደ እርሱ እንድንመልስ እንጂ። ሁልጊዜ የእግዚአብሔር የቸርነት ብዛት ንስሐ እንድንገባና እንድንመለስ ነውና።

   በልጁ የማያምን መላው ዓለም ኀጢአተኛ ነው፤ ስለዚህም የሰዎች ልጆች ኹሉ ኀጢአተኞች በመኾናቸው፣ በልጁ በማመን ንስሐ ባይገቡና በልጁ ባያምኑ፣ ፈጽመው ሊያመልጡት የማይችሉት ፍርድ አላቸው፤ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ባናምን ግን ፈጽሞ የማናመልጠው የዘላለም ፍርድና ቊጣ አለ። እስራኤል ከሰዶምና ከገሞራ፣ አይሁድም በገሊላ ደማቸው ከመሥዋዕታቸው ጋር ከተደባለቁትና በሰሊሆም ግንብ ተንዶ ከገደላቸው ሰዎች ተሽለው እንዳይደለ፣ ደግሜ እላለሁ፦ እኛም አገር እጅግ ክፉው ነገር ያልኾነብን በመሻላችን አይደለም፤ ይልቅ ከግብዝነት በእውነትና በንስሐ ወጥተን በልጁ መዳንና ዕረፍት አምነን ንስሐ እንድንገባ እንጂ።

  በዓለም ላይ በአንድ ቀን ውስጥ፣ ሰውን በመግደል የታወቁ በሽታዎች ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ ቢሰጣቸው፣ Tuberculosis(የሳምባ በሽታ), Hepatitis B(የጉበት በሽታ), Pneumonia(የሳምባ ምች), HIV/AIDS, Malaria(የወባ በሽታ) ሲኾኑ፣ የገዳይነት መጠናቸው በቅደም ተከተላቸው ሲቀመጥ፣ በቀን 3014፣  2430፣ 2216፣ 2110፣ 2002 የሚያህሉ ሰዎችን በመግደል ቊጥሮችን ሲይዙ፣ በዚህ የቁጥር አሃዝ መጠን የCOVID-19(#Coronavirus)ን የቀን ገዳይነት መጠኑን ስንመለከት፣ በደረጃው እስከ15ኛ ካሉት ውስጥ የሌለ መኾኑን እናስተውላለን።[1]

  ስለዚህም ዓለም በቀን በሌሎች በሽታዎች ከኮሮና በበለጠ የሚሞቱባት መኾኑን የዘነጋን ይመስላል፤ እንደ ወረርሽኝ በፍጥነት የሚስፋፋው ያስደነግጠናል፣ ቀስ እያለ ብዙውን የሚገድለው ግን ምንም አይመስለንም ወይም አያሳስበንም፤ አያስጨንቀንም። ቀስ እያለ ወገናችንን ለሚፈጀው፣ ጸሎትም ምልጃም የለንም፤ እንዲህ ዓለምን በወረርሽኙ ለሚያስጨንቀው በሽታ ግን የምንሸበርና የምንደነግጥ፣ የምንርበደበድ መኾናችን ምን ያህል ከማስተዋልና ከእምነት የተዘናጋን፣ በተላላነት የተታለልን መኾናችንን ያሳያል። በእርግጥ ሙሉ ለሙሉ ባልተዋጀው አለም እንደ መኖራችን፣ እንደ ሰው የሚያስፈራንና የሚያስደነግጠን ነገር ይኖራል፤ ነገር ግን እንደማያምኑ፤ ተስፋ እንደሌላቸው አሕዛብ በመርበትበት፤ በፍርሃት ተውጠን የምንኖር አይደለንም። እንዲህ ተጽናኑ፤ አጽናኑም!

  እግዚአብሔር የትኛውንም ክፋት፣ በሽታ፣ የሰዎችን ዓመጽ፣ የመንግሥታትን አምባገነንነት፣ ጥልፍልፉን የሴረኞች ተግባር … በሉዓላዊ አምላክነቱ ፍጹም ይቈጣጠራል፤ ይይዛልም፤ እርሱ ሳያውቀው የሚከናወን የቱም ተግባርና አድራጐት በምድር ላይ ፈጽሞ የለም፤ ሰዎች ባይታዘዙትም፣ ምድር በፊቱ ፍጹም ያልታመነች ብትኾንም፣ እግዚአብሔር ግን የኀጢአትንና የዓመጽን ተግባር እንኳ ገደቡን እንዳያልፍ ፈጽሞ ይቈጣጠረዋል። ታድያ ባለመታዘዝ ለምን እንቀሰፋለን? ለምንስ በመገበዝና በመታለል ራሳችንን እናስታለን? … አምኖ ተዘልሎ እንደሚኖር ሰው በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ደግሞም ጭንቀታችን ሰዎች እንዲድኑና ከስጋት እንዲያርፉም ጭምር እንጂ እጅን በመታጠብ፣ ማስክ በማድረግ፣ ባለመጨባበጥ፣ በመራራቅ ከሥጋዊ በሽታ እንዲፈወሱ ብቻ መኾን የለበትም፤ ለታመሙ በምልጃ መጸለይ፣ ወንጌል መመስከር፣ ሕይወትና ዕረፍት ወደ ኾነው ወደ ልጁ መንግሥት እንዲፈልሱ ልንተጋ ይገባናል፤ እንዲህ በማድረግ ሰዎች ከሚበልጠው ጥፋት እንዲድኑ ማድረግ፣ መንፈሳዊ የፍቅር ግዴታችን መኾኑን አንዘንጋ! ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።



[1] https://informationisbeautiful.net/visualizations/covid-19-coronavirus-infographic-datapack/?fbclid=IwAR1iDauPFLB9dH_IioSZzWttr9ecfjXEVHnyW16dMlCWLoWQR286AvjoINY

2 comments:

  1. አሜን ይጠብቀን

    ReplyDelete
  2. What a rich understanding of the word and passion to teach! You are blessed and a blessing to the generation!!!

    ReplyDelete