Monday 30 June 2014

የጠፋው ልጅ ወንድሞች(ሉቃ.15፥28)


ከሌሎች ወንጌላት ይልቅ ጠፍቶ ስለመገኘት ሉቃስ ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጠናል፡፡“ጠፍቶ የተገኘው” ህጻኑ ኢየሱስ(ሉቃ.2፥46)፣ ጠፍቶ የተገኘው በግና ድሪም (ሉቃ.15፥3-11) ሉቃስ የዘገባቸው እውነትና ምሳሌዎች ናቸው፡፡በእርግጥ በኃጢአት ጠፍቶ ለበጎነት እንደመገኘት ያለ ፍጹም ሰማያዊ ደስታ የለም፡፡(ሉቃ.15፥10)
     የጠፋው ልጅ የአባቱን ሀብት ለመካፈል ሲነሳ ወደአባቱ ቤት ለመመለስ ፈጽሞ ያሰበ አይመስልም፡፡ከአባቱ ቁጥጥር ውጪ በመሆን ያሻውንና የወደደውን ሊያደርግ በመፈለግ ወጥቶ የሄደ ነው፡፡“ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ የሄደው ወደሩቅ ሀገር ነው፡፡”(ሉቃ.15፥13) በሄደበት ሀገር ግን ሀብቱን በተነ፡፡ እንዳይመለስም እጅግ ርቆ ሄደ፡፡ የኃጥዕ መንገድ ከእግዚአብሔር የተለየ ነውና ሩቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተለየው አዳም መልካም በሚመስለው መንገድ ሲጓዝ ፤በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ሩቅ ነበር፡፡(ዘፍ.3፥6) በተመሳሳይ መንገድ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ወደተርሴስ የሄደው ዋጋ ከፍሎ፤ከስሮ ፤ርቆም ነው፡፡(ዮና.1፥3)
     የጠፋው ልጅ ከመራቁ ባሻገር በረሃብ ምክንያት የሚጨነቅም ሆነ፡፡ የረሃቡን ጭንቀት ለማስታገስ “ … ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።”(ሉቃ.15፥15) ይላል፡፡ የጠፋው ልጅ የእሪያ እረኛ በመሆን ያደረገው ይህ ድርጊት በአይሁድ ልማድና  በኦሪት ህግ እጅግ ርኩሰት ነው፡፡(ዘሌ.11፥7) ይህ ብቻ አይደለም ለእንሰሳት የሚሰጠውን የእህል ገለባ (አሰር) ሊበላ እየተመኘ እንኳ ሊያገኝ ያልቻለ ነበር፡፡

     ኃጢአተኝነት ያወረደው ማንነት የእግዚአብሔር ትንሳኤ ካላገኘው ከእንሰሳ እንኳ የሚያንስበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ከባህርይ ውጪ የእንሰሳ ምግብን መመኘት እጅግ ይከብዳል፡፡ በእርግጥ ይህ የጠፋ ልጅ በጣም ያሳዝናል፡፡ የዚህ ልጅ መጥፋት እውነተኛው ስብራትና ህመም የሚሰማው ለወለደው አባቱ ነው፡፡ ምንም እንኳ አባቱ ነጻነቱን የጠበቀለት ቢሆንም ልጁ በተቅበዘበዘና በባዘነ ጊዜ ፍጹም የማዳን እጅን ዘርግቶለታል፡፡ ወላጅ አባት ስለልጁ ስብራት ማንም አያስረዳውም፡፡ የልጁን ነገር ያለቋንቋም ይገባዋልና፡፡
     ልጁ የጠፋበት አባት ዓይኖች ደጅ ደጅ ብቻ የሚያዩ አይደሉም፤ይልቁን መንፈሱ ይቅበዘበዛል እንጂ፡፡ የጠፋው ልጅ በሆነው ሁሉ ወደልቡ ተመለሰ፤አዘነ፤ተጸጸተ፤ተነስቶም ወደአባቱ በመሄድ “አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።”(ሉቃ.15፥18) በማለት ለራሱ ተናዘዘ፡፡ እውነተኛ ንስሐ ለራስ ከመናዘዝ ይጀምራል፡፡በራሱ ፈርዶ፤ጥፋተኝነቱን አምኖ መጥቷልና አባቱ በምንም ነገር ሊወቅሰው አልወደደም፡፡ጌታም ለእኛ ያለው ሀሳብ ይህ ነው፡፡ራሳችንን በንስሐ ወቅሰን በመጣን ጊዜ የፍቅርና የሥርየት ደሙ ለይቅርታ እንጂ የቁጣውና የትዝብቱ በትር አያገኘንም፡፡
     ስለተገኘው ልጅ ሙሉ ደስታ ሆነ፡፡ ተካፍሎ ከሄደው ሀብት ይልቅ አሁን በመመለሱ ያገኘው ተቀባይነትና ማዕረግ ፤የልጅነት ሥልጣኑም በለጠ፡፡ አባቱ ከበደል የተመለሰ ልጁን ሲያገኘው ከሞትና ከመጥፋት ህያው ሆኖ ስላገኘው ልዩ በዓል፤ትልቅ ግብዣ አደረገለት፡፡ አብ የጠፋን ልጆቹን በልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ባገኘን ጊዜ ዘላለማዊ ደስታና በዓል በእግዚአብሔር ገነት ሆኖዐል፡፡
      የጠፋው ልጅ በመገኘቱ፤ በተደረገው ደስታና በዓል በቤት የነበረው ታላቁ ልጅ ፍጹም ደስተኛ አልነበረም፡፡ “ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው።እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጠቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው።”(ሉቃ.15፥28-30)
    አይሁድ በቤተ ክርስቲያን መመስረት ደስተኞች አልነበሩም፡፡ የቀደሙት “ታላላቅ” የኋለኞቹ ታናናሾች በመምጣታቸው ፈጽሞ አልተደሰቱም ፤ይልቁን አብዝተው ተቆጡ እንጂ፡፡ ይህ ወንድም የተቆጣ ብቻ አይደለም ታናሽ ወንድሙን “ይህ ልጅህ… ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር የበላ” በማለት እንደወንድም በማያይ ጥላቻና በንቀትም የተናገረ ነው፡፡በእርግጥ ግን ሰው ሲመለስ ለምን ይሆን ብዙዎች እንዲህ የሚንጨረጨሩት? የጌታ መንግስት እኮ እንዲህ ያሉ ደካሞችና ኃጢአተኛ ሰዎች የሚጋፏትና የሚናጠቋት ናት?(ማቴ.11፥12) ዛሬም ይህ እውነት ፍንትው ብሎ አለ፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት በአገልግሎት የቀደሙትና በቤቱ ያሉቱ ሌሎች “ኋለኞች” ከአለምና ከጠፉበት ሲመጡ ብዙዎቹ ደስተኞች አይደሉም፡፡ በፌስ ቡክና በተለያዩ የመገናኛ ገጾች ከሚሰሩ አስነዋሪ ኃጢአተኞች አንዱ የደከሙት ሲመለሱና ፊታቸውን ወደጌታ ዘወር ሲያደርጉ የሚወርፉና የሚሳደቡ የስድብ አፎች መብዛቱ ነው፡፡
     ለምን እንደሚቆጡና እንደሚሳደቡ ሳስብ “እገረማለሁ!”፡፡ ቁጣቸውና ስድባቸው ደግሞ ከሩቅ ይሰማል፡፡ አባቱ ስለጠፋው ልጁ በዓል ሲያደርግ፤ታላቅ ወንድም መርዶ ይቀመጣል፡፡ ዘማውያን ፣ዘፋኞች ፣ዓለማውያንና አህዛብ በፍጹም ንስሐ ተመልሰው አንዱን ጌታ ብቻ መርጠው ተገልግለው ሊያገለግሉ ሲመጡ ጥቂት ያይደሉ የቤቱ “ቀደምት ነዋሪ ወንድሞች” ግን ጠፍተው የተገኙ ወገኖችን የቀደመ ነውር ያጠናሉ፤ያጠነጥናሉ፡፡ ስለዚህም አብዝተው ይቆጣሉ፡፡ “እኛ ከጥንት እዚህ ነበርን ፤እኒህ ከወዴት መጡ?” የሚል የቀኝ አይን ቅላት ጥያቄ ያሠማሉ፡፡ እግዚአብሔር በልጁ ደም አጥቦ የረሳውን ኃጢአት አስታውሶ እንደመቆጣትና የክስ ምክንያት እንደማድረግ ከባድ ነውርና ኃጢአት ፈጽሞ የለም፡፡
     እናንተ ታላላቅ የቤቱ ቀደምት አገልጋዮች! እንደእኔ ያለ ፍጹም ኃጢአተኛና ነውረኛ ከጠፋበት በመጣ ጊዜ ስለምን ትቆጣላችሁ? እኔ የአባታችሁ ልጅ ወንድማችሁ ነኝና ከጠፋሁበት በመገኘቴ ደስ ይበላችሁ እንጂ በአንዳች አትከፉ፤አባቴም እንዲህ ይላችኋልና፦
            “ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል፡፡”(ሉቃ.15፥31-32)
አሜን፡፡ እንዲህ ይሁንልን፡፡    


3 comments:

  1. Let there be light1 July 2014 at 05:49

    10Q brother
    .. ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን...

    ReplyDelete
  2. Let there be light1 July 2014 at 05:49

    የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና

    ReplyDelete
  3. እውነተኛ ንስሐ ለራስ ከመናዘዝ ይጀምራል፡፡በራሱ ፈርዶ፤ጥፋተኝነቱን አምኖ መጥቷልና አባቱ በምንም ነገር ሊወቅሰው አልወደደም፡፡ጌታም ለእኛ ያለው ሀሳብ ይህ ነው፡፡

    ReplyDelete