Monday 23 March 2020

ስለ ተላላፊ በሽታ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

Please read in PDF
መግቢያ
   ጌታችን ኢየሱስ መድኀኒት አስፈላጊነቱ ለበሽተኞች መኾኑን ተናገረ (ማቴ. 9፥12)፤ ስለዚህም ሰዎች ከበሽታ ለመዳን መድኀኒትን መጠቀማቸውን እናስተውላለን፤ “በጥንት ዘመን ሰዎች በመድኃኒት ሲያምኑ በነፍስ ሊበረቱ ይችላሉ። ጥቅሙ ከእምነት እንጂ ከመድኃኒት አልነበረም። ዛሬ ግን ብዙ ጊዜ በመድኃኒት ቢያምኑም ባያምኑም መድኃኒቱ ፍቱን ነውና ይሠራል”። ከፊት ዘመን ይልቅ በዛሬ ዘመን ሰዎች በመድኃኒት አብዝተው የሚታመኑ ይመስላል፤ ለዚህም ይመስላል በምድራችን ላይ እጅግ ዝቅተኛ ከሚባሉት እስከ ቅንጡ መታከሚያ ቤቶች የተበራከቱት። ነገር ግን ይህ ኹሌ ስሙርና የመጨረሻ መፍትሔ ኾኖ አይታይም።


   ምድራችንን እንደምንመለከተው፣ ተላላፊ በሽታ ማቅ አስታጥቆአታል፣ ስጋትና ፍርሃት ዳርቻዋን ከብቦታል። በአጭር ጊዜ እንቈጣጠረዋለን ያሉት ሃያላን መሪዎች፣ በተላላፊው በሽታ የተያዙ ዜጎቻቸውን ካልተያዙት እንኳ በቅጡ መለየት ተስኖአቸው፣  በጭንቀትና በፍርሃት መግለጫ በመስጠት ሲራኰቱ እያየናቸው ነው። በእርግጥ ትምክህትና ኵራት፣ ሃያልነትና የሥልጣኔ ገናናነት ማንንም እንዳልታደገ፣ እነሆ እኛም ከቃለ እግዚአብሔር በተጨማሪ በዓይኖቻችን አስተውለናል።
ተላላፊ በሽታ
   ተላላፊ በሽታ ብዙውን ጊዜ በሕዝቡ መካከል ሊከሰትና ከአንዱ ወደ ሌላው በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ በመተላለፍ ሕዝቡን ሊጎዳ ይላል፤ ስለዚህም ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው ከሕዝቡ መካከል እንዲለይና (ዘሌ. 13፥1-8) ጽዳቱን እንዲጠብቅ ይደረጋል፤ (ዘሌ. 11፥39-40፤ 13፥47-58፤ 14፥33-53፤ 15፥1-33፤ ዘዳ. 23፥13) ከዚያም ከበሽታው ይፈወሳል። ጌታ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር በሕዝቡ መካከል ሊነሳ እንደሚችል በማሰብ፣ ብርቱ ማስጠንቀቂያን “ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው ወይም ይዝጋበት” በማለት በተደጋጋሚ ተናግሮአል።

   ተላላፊ በሽታዎች በልብስ፣ በአጎዛ፣ በድሩ ወይም በማጉ፣ በበፍታው ሊተላለፍ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ልብሱ እንዲታጠብ ወይም እንዲቃጠል ወይም በበሽታ የተጠቃው ክፍል ተቀድዶ መልሶ እንዲታጠብ በማድረግ ማጽዳት እንደሚገባ ቅዱስ መጽሐፍ በሚገባ ያስቀምጣል። ለእነዚህና ለሌሎችም በሽታዎች የተለያዩ የሕክምና ተግባራት ይደረጉ እንደ ነበር ከሰፊው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች መረዳት እንችላለን፤ ቍስሉን ማፍረጥ፣ በዘይት ማለዘብ፣ የበለስ ጥፍጥፍ መለጠፍ፣ ወይን ጠጅ መጠጣት(ዛሬ አምቦ ውኃ ይኾንን?) … እና ሌሎችንም በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን፤ (ኢሳ. 1፥6፤ 38፥21፤ ሉቃ. 10፥34፤ 1ጢሞ. 5፥23)።

  አንዳንድ በሽታዎች ባለመታዘዝ ምክንያት ሊመጡ ይችላሉ፤ (ዘሌ. 26፥14-16፤ ዘዳ. 28፥22፤ ኤር. 24፥10)፤ ማርያም፣ ግያዝ፣ በርያሱስ በግል ኀጢአታቸው ምክንያት በበሽታ ተያዙ፤ ሁል ጊዜ ግን በሽታ በኀጢአት ምክንያት ሊመጣ እንደሚችል ፍጹም ስህተት ነው። አንዳንዴ ሰይጣ በቁስል እንዲመታ ሊፈቀድለት ይችላልና፣ ለዚህም ኢዮብን መዘንጋት አይገባም።
ስለ በሽታዎች የቅዱሳት መጻሕፍት ዐሳብ

   ቅዱሳት መጻሕፍትና ጸሐፊዎች ስለ ፈውስና መድኃኒት ዋና ዐሳባቸው፣ እግዚአብሔር ፈዋሽና አዳኝ እንደ ኾነ አጽንተው በመናገር ነው። “ … እኔ ፈዋሽህ አግዚአብሔር ነኝና”፣ “አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር”፣ “እርሱ ሰብሮናልና፣ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናልና፣ እርሱም ይጠግነናል” (ዘጸ. 15፥26፤ ኤር. 30፥17፤ ሆሴ. 6፥1)። ለዚህም ማሳያ እግዚአብሔር ብዙዎችን ፈውሶአል፤ በብሉይ ኪዳን ማርያምና ንዕማን ከለምጽ መፈወሳቸው ምስክር ናቸው። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አያሌ በሽተኞችን በመፈወስ የምትመጣውን ፍጽምት መንግሥት ጣዕም ቅምሻውን አሳይቶናል።

   የትኛውንም በሽታ እግዚአብሔር ይፈውሳል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው፣ እርሱም የማያውቀው አንዳች ነገር የለውም፤ ሰዎች በገዛ ስህተታቸውና በተላላነታቸው ያመጡትን በሽታ መፍትሔና መድኃኒት እግዚአብሔር አለው። ዛሬ በምድራችን ላይ እንደምናየው ያለውን በሽታና ጥፋት፣ ሰዎች እግዚአብሔር በሰጣቸው ጥበብ መርምረው እስኪደርሱበት ድረስ እንኳ፣ በሉዓላዊነቱ ጣልቃ ገብቶ ገደብ ሊያበጅለት የሚቻለውና ችሎታ ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

  ይሁንና በግልጥ እንዲህ ትልቁንም፤ ትንሹንም የሚያዳርስ ወረርሽኝ ሲመጣ በሕጉ መጽሐፍ ያሉትን ማስጠንቀቂያዎችን መስማትና የኢየሱስን ርኅራኄ ማሳየት ይገባናል፤ ይኸውም፦

·        ከታመሙት መራቅና ራስን መጠበቅ። በሽታውን ወደ ሌሎች ከማስተላለፍ መጠበቅ የምንችለው፣ እኛም በሽታው ካለባቸው ሰዎች ራሳችንን መጠበቅ ስንችል ነው። ይህ ሰውን አለማፍቀር አይደለም፤ ይልቁን በቸለተኝነት ሌሎች ብዙዎችን መበደል ነውና፣

·        ንጽህናችንን መጠበቅ፤ ልኩ በሕጉ መጽሐፍ ላይ እንደ ተጠቀሰው የሚታጠበውን ማጠብ፣ የሚቀደደውን መቅደድ፣ የሚቃጠለውን ማቃጠል ይገባናል። በዚህም የበሽታውን ስርጭት እንገድበዋለን

·        ለታማሚዎች መጸለይ፣ መማለድ፣ አስፈላጊውንና የባለሙያዎችን ምክር በመቀበልና በመተግበር፣ ወንጌልን መመስከርና የኢየሱስን ርኅራኄ ልናሳይ ይገባናል።
ማጠቃለያ

   መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሉዓላዊ አምላክና ኹሉን በተቈጣጣሪነቱ፤ በመግቦቱም የሚመራ መኾኑን ይነግረናል፤ ስለዚህም በምድራችን ላይ የሚኾነውን ኹሉ ያውቃል፤ ደግሞም በሽታንም ኾነ የትኛውንም ጉድለት ሊመላና ፍጹም መፍትሔ ሊያበጅለት የሚቻለው ራሱ ብቻ መኾኑንም ጭምር ይነግረናል። እኛም ይህን ማመንና መታመን ይገባናል። ስለዚህም ባለሙያዎቹ የሚነግሩንን እያደረግን፣ ርኅራኄና ፍቅርን ሳንተው፣ ልንማልድ፣ ልንጸልይ ይገባናል። የእስራኤል ቅዱስ ለምድራችን መልካሚቱን እጁን ይላክላት፤ አሜን።
  ጸጋና ሠላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment