ከአገልግሎት በፊት ርስ በርስ መዋደድ ይቀድማል። ኢየሱስን ከመስበክ በፊት ሕይወቱንና ትምህርቱን በሚገባ
ማሰላሰል ብርቱ ማስተዋል ነው። ኢየሱስን እየሰበኩ ትህትናቸው የታይታ፣ ክርስቶስን በድንቅ ንግግር እየናኙ ኅብረት የሚጠየፉ፣ መዝሙረኛው፣
“አፉ ከቅቤ ይልቅ የለዘበ ነው፤ በልቡ ግን ጦርነት አለ፤ ቃሉ ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነው፤ ይሁን እንጂ የተመዘዘ ሰይፍ ነው።”
(መዝ. 55፥21) እንደሚለው፣ ልባቸውና አፋቸው የተጣላባት ግብዝ አገልጋዮችና አማኞችን እንደ ማየት ቅስም እንክት የሚያደርግ
ነገር ያለ አይመስለኝም።
በአንድና ወጥነት ባለው ሕይወት አለመኖር ወይም አስመሳይነት ከአመንዝራነት ሕይወት ጋር ይመሳሰላል።
ጠቢቡ፣ “የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤ አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤ በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመርራለች፤ ሁለት
አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች።” (ምሳ. 5፥3-4) እንዲል፣ አመንዝራ ሴት ወይም ወንድ ይህን የሚያደርጉት አጥምዶ ለማሳት
ነው፤ ስለዚህም የለየለት የግብዝነትን መንገድ ይመርጣሉ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኹለት መልክ ስላላቸው ሰዎች፣ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥”
(ማቴ. 12፥39) ብሎ ሲናገር፣ አመንዝራ ሴት በአንድ ሰው እንደማትረካ ወይም ወንዱም በአንዲቱ ሴት እንደማይረካ እንዲኹ፣ በኢየሱስ
ትምህርትና ሕይወት የማይረካና የማያርፍ ትውልድ መልከ ብዙና ጥርቅም ፍላጎቱን ለማርካት አእላፍ መልክ፤ ገልበጥባጣ ጠባይ አለው።
ክፉ ሰውም በአንድ ክፋቱ መች ይረካና?!
የዘመንዋ ቤተክርስቲያን እንዲህ ባሉ
አገልጋዮች መሞላትዋ ያስፈራል። የሚያደርጉትን ነገር በትክክል ያውቁታል፤ የግብዝነቱን መንገድ በሚገባ ተለማምደውታል፤ ነገር ግን
የሚያደርጉትን ኹሉ የሚያደርጉት በስውር እጅና ቶሎ ሊደረስበት በማይችል “የጥበብ መንገድ” ነው። ስታገኛቸው እንከን አታገኝባቸው
ይኾናል፤ መንገዳቸው ግን ኩልል ያለና የጠራ የግብዝነት ነው።
የቢዖር ልጅ በለዓም፣ እስራኤል ኹሉ ቅንን መንገድ ትተው በሰጢም ከማመንዘራቸው በፊት አሳች ምክር
ከጀርባ መምከሩን ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ይሁዳ ባይነግሩን ማን ያስተውላል?! ምንም እንኳ ምዋርተኛም በለዓም፣ “በመንፈስ ቅዱስ
ትእዛዝ” ለእስራኤል፣ “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር
ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል።” ብሎ ትንቢት የተናገረ ቢኾንም፣ መንገዱ የስህተት ጎዳናው የዓመጻ
ነበር። እንደ ምዋርተኛው በለዓም የውድቀትህን ቀን አድብተው የሚጠብቁ ግብዞችና አስመሳዮች መኖራቸውን አትዘንጋ! ምዋርተኛው በለዓለም
የቱንም ያህል ትንቢት ቢያመጣም፣ ልበ ጠማማ፤ አስመሳይ ምክር ማምጣቱ እሙን ነው።
የአገልግሎት ስኬት ፍቅርን አይተካም፤ ርስ በርስነትን ገፍቶ “ሩጫን መጨረስ” የክርስትና ግቡ አይደለም።
የክርስቶስ መንገድ፤ የጽዮን ጉዞ የሚጨረሰው ርስ በርስ ተያይዞ እንጂ፣ በማስመሰልና በግብዝነት ካባ የራስን አገልግሎት አስጠብቆ፤
የሌላውን ገፍቶ አይደለም።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።
No comments:
Post a Comment