Sunday, 27 July 2025

ከኦርቶዶክስ የወጡና ወደ ኦርቶዶክስ የሚመለሱ!

Please read in PDF

 በዚህ ባለንበት "የክርስትና ዐውድ" ሰዎች "ወንጌል ተረዳን" ሲሉ፣ ከአንድ ኅብረት ወደ ሌላ ኅብረት "ቀለል ባለ መንገድ ሲሸጋገሩ" ማየት የተለመደ ኾኖአል። ርግብ ቤቷ ጨርሶ እስካልፈረሰና ጫጩቶቿን እስካልገደሉባት ድረስ ስላባረሯት፣ ስለመቷት ... ብቻ ከጎጆዋ አትወጣም ተብሎ በሚነገረው የኦርቶዶክስ ማኅበረ ሰብ ውስጥ የኖረውም ኾነ፣ ከኅብረት መውጣት "የዓሳ ከባሕር የመውጣት ያህል" ከባድ ነው በሚለው የወንጌላውያን ማኅበረ ሰብ ሰዎች ይወጣሉ፤ ይፈልሳሉም።




ለእኔ የዘወትር ጥያቄዬ፣ ከወር ባነሠ ዕድሜ ውስጥ ከኦርቶዶክስ ወይም ከወንጌላውያን ዐውደ ምሕረት ላይ "ያገለግል የነበረ ሰው"፣ ድንገት "ወጣኹ፣ የተለየ ብርሃን አገኘኹ ... " ሲልና ሲያገለግል ማየት፣ እንዴት? የሚል ጥያቄ በውስጤ ያጭራል። ሰው የማሰላሰያ ጊዜ የለውም ወይ? እንዴት በአንዴ ይገላበጣል፤ የቀደመውን አያምነውም ነበር? የጥያቄና የመልሱ ጊዜ እንዴት እንዲህ ይፈጥናል? መቼም ስለ "ያልተገለበጠ ቂጣ" የተነገረውን የኤፍሬምን ጠባይ አንዘነጋም።

ያልተገለበጠ ቂጣ ሲታይ የበሰለ ይመስላል፤ ነገር ግን በጋለ ምድጃ ወይም ምጣድ የተጋገረ ስለ ኾነ ሥሩ ያረረ ነገር ግን ውስጡ ያልበሰለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከማረሩ የተነሳ የበሰለ ሊመስል ይችላል፤ ግን አልተገላበጠምና ጥሬ ነው፤ ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር መደባለቁ፤ የአሕዛብን አማልክትና ጣዖታት ለማምለክ ምክንያት ኾኖታል፤ ሆሴዕ በትንቢቱ እንደ ተናገረው፣ የፀጉር መሸበቱ እንኳ በሽምግልና ወግ ያገኘው ሳይኾን፣ ሳያስተውል በሕይወት እንዳረጀና ፍጹም እንደ ደከመ የሚያመለክት ነው፡፡

ልክ እንዲኹ፣ ከኦርቶዶክስ ወደ ወንጌላውያን ከወንጌላውያንም ወደ ኦርቶዶክስ የሚመጡት አብዛኛዎቹ ያልተገላበጡ ቂጣዎች ናቸው፤ ሲታዩ ማለትም ሲናገሩና ነገሮችን ሲያብራሩ የበሰሉ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በፍጹም ጤናማዎችና እውነተኛ ምሳሌነት ያላቸው አይደሉም፡፡

አንዳንዶች እንዲያውም መምጣታቸውና መሄዳቸው ሳይታወቅ፣ በአገልግሎት ዐውደ ምሕረት ነው የሚታወቁትና ራሳቸውን የሚገልጡት፡፡ ይህ “የወንጌሉን አትሮንስ” የመናቅ ያህል ከባድ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ሰዎች እምነታቸውንና የእምነት አቋማቸውን መቀየራቸው “የግል ውሳኔያቸው” ቢኾንም፣ ዓውደ ምሕረቱና አትሮንሱ ግን የግል ስላይደለ፣ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ባይ ነኝ!

በተለይ በዚህ ዘመን ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋርና “ካልተገላበጠ” ማንነት ጋር የሚመጡትን ሰዎች መለየት፣ እምነታቸውን “የለወጡበትን” ዐላማ ትክክለኛ መሻታቸውን መረዳት፣ አስቀድሞ ወደ አትሮንስና ዓውደ ምሕረት ከማውጣት በትክክል ማስተማር፣ በሕይወት ልምምዳቸውም ጤናሞች እንዲኾኑ መርዳትና መመገብ ያስፈልጋል፡፡ ከኦርቶዶክስ “ጨርሰውና ጨክነው” የማይመጡና ወደ ኦርቶዶክስ በትክክል ሳያምኑ፣ ሳይማሩ፣ ሳይመረምሩና ሳይኖሩ የሚመለሱ በርግጥ እጅግ ያሳዝናሉ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment