Please read in PDF
ያለንበት የዓቢይ ጾም ሳምንት በማኅሌታይ ያሬድ ስያሜ፣ “ምኩራብ” ተብሎአል፤ ምኩራብ አይሁድ በምርኮ ወደ ባቢሎን
በተወሰዱ ወራት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብና የሕጉን ቃሎች ለማሰብ፣ በየጥቂት አባወራ በመሰባሰብ የጀመሩት ነው። ወደ
አገራቸው ሲመለሱም ይኸንኑ በመቀጠል፣ ከዋናውና መሥዋዕት ከሚቀርብበት መቅደስ ባሻገር፣ በየመንደራቸው አቅራቢያ ምኩራብ
በመሥራት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና ማንበብን በዚያ ጀመሩ። እንግዲህ ማኅሌታይ ያሬድ፣ ምኩራብን ለዓቢይ ጾም ሦስተኛው
ሳምንት ሲሰይም፣ በሳምንቱ ውስጥ ከሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ደግሞ፣ ዮሐ. 2፥12-22ን በመመደብ ነው። ክፍሉም
በቀጥታ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ጋር በማያያዝ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ስለ መኾኑ የታመነ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ
ከቅፍርናሆም ቀጥታ ጉዞውን ያደረገው ወደ ኢየሩሳሌም ነው፤ የመጣበት ሰዓት ደግሞ የአይሁድ የፋሲካ በዓል መቃረቢያ
ላይ ነው። በበዓሉ መቃረቢያ ስለ ኾነም፣ በመቅደሱ ዙሪያ ብዙ ግርግርና የሰዎች ብዛት ይታያል። ጌታ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ
ሲመጣ፣ በቤተ መቅደስ የማይሸቀጥ፣ የማይሸጥ፣ የማይለወጥ፣ የማይለዋወጥ … ነገር አልነበረም፤ እናም የቤቱ ጌታና አባወራ ቤቱን
ለማጥራት፣ ሻጭና ገንዘብ መንዛሪ ለዋጮችን በጅራፍ ገርፎ በማውጣትና የመንዛሪዎችን ገንዘብ በመበተን አባረረ።
ለቤቱ
በመቅናትም፣ “ቤቱ ላልተሰጠበት ዐላማ አታውሉ!” ብሎ ኹሉንም አስወጣቸው። ፍቅር የኾነው ጌታ ንዴት ሳይኖርበት ተቈጣ፣
በቅንአትም ተቃጠለ፤ በሥልጣናዊ ቃሉ፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” በማለትም ጨምሮ
አሰምቶ ተናገረ። ለእግዚአብሔር ያለው ይህ ታላቅ ቅንአቱም እስከ ሞት አደረሰው፤ በነፍስ ያሳርፈን ዘንድ፣ እርሱ በታላቅ ቅንአት
በፍቅር በሥጋው ሞተ። አይሁድ ለዚህ አድራጐቱ ተአምራዊ ምልክትን፣ “ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት
ታሳየናለህ?” በማለት ጠየቁ።
ጌታ ኢየሱስ ግን “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ”
ብሎ፣ “ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ” ተናገረ። ለአይሁድ ይህ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር አልተዋጠላቸውም፤ አልተቀበሉትምም። እነርሱ
የሚያወሩለት መቅደስና ጌታ ኢየሱስ የሚያወራው መቅደስ ፈጽመው አይገናኙም ነበር። እነርሱ ስለሚፈርሰውና ከድንጋይ ስለ ተሠራው ቤተ
መቅደስ ሲያወሩ፣ እርሱ ግን ስለ ሕያውና ፈጽሞ ስለማይሞተው ሕያው ቤተ መቅደስነቱ ተናገራቸው። ይህን ለማስተዋል የቤተ መቅደሶቹን
ይዘት ማየቱ በጥቂቱ ይጠቅመናል።
ፊተኛው መቅደስ
ፊተኛው መቅደስ የተሰጠው ከእግዚአብሔር በሰሎሞን አማካይነት ነው። ያ መቅደስ
ግርማውና ክብሩ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፤ ሰሎሞን አባቱ ዳዊት ባከማቸው ሃብት፣ መቅደሱን የሠራው እጅግ አንቆጥቁጦ፤ አስውቦ ነበር።
እግዚአብሔር ራሱ በዚህ መቅደስ ተገኝቶ ሰሎሞንን በተደጋጋሚ በጨለማ ውስጥ ኾኖ ተናግሮት ነበር። ይህ መቅደስ ለአይሁድ ብቻ ያይደለ፣
ከአይሁድ ውጭና የኪዳኑ አካል ያልኾነም ሰው መጥቶ በዚያ ቢጸልይ እግዚአብሔር እንደሚሰማው ቃል የገባበት መቅደስ ነበር።
የመሰጠቱ ዋነኛ ዓላማም፣ እግዚአብሔር አምላክ ክብሩን በዚያ መቅደስ ውስጥ
በመግለጥ፣ በሕዝቡ መካከል ለመኖር ነበር። ሥፍራው የያህዌ ዋነኛ መታወቂያ፤ የአምልኮ ማዕከል፤ የእግዚአብሔር መገለጥ የሚታይበትም
ቅዱስ ስፍራ ነበር። በእርግጥ መቅደሱ የአይሁድ ብቸኛ ተስፋና የአምልኮአቸው ማዕከል ነበር፤ ነገር ግን ኀጢአትን ስለ ሠሩ እጅግ
ውብና ማራኪው ቤተ መቅደስ በናቡከደነጾር ፈርሶ ፍጹም ምድረ በዳ ኾነ።
ኹለተኛው ቤተ መቅደስ
ፊተኛው ቤተ መቅደስ ከፈረሰና እስራኤል ለሰባ ዓመታት ያህል በባቢሎን ምርኮ
ከተገዙ በኋላ፣ በእነ ዘሩባቤል መሪነት ኹለተኛው ቤተ መቅደስ ተገነባ። ምንም እንኳ ግንባታው እጅግ የተለያየ ቢሆንም፣ የኹለተኛው
ቤተ መቅደስ ዓላማም ከፊተኛው ቤተ መቅደስ የተለየ አይደለም። ከዚህም ባለፈ ታላቁ ሄሮድስ በአይሁድ ዘንድ ድጋፍና ተወዳጅነት ለማግኘት
ሲል፣ መቅደሱን ለአርባ ስድስት ዓመታት ያህል በሚማርክ መልኩ አድሶትና አስፋፍቶት ነበር። ነገር ግን ይህም መቅደስ በ70 ዓ.ም
እስከ ዛሬ ድረስ ዳግም መሠራት እስከማይችል ድረስ ፈጽሞ ፈረሰ፤ ፈራረሰ፤ ወደመ።
እግዚአብሔር አንድን መቅደስ ለእስራኤል የሰጣቸው፣ ክብሩንና ራሱን ለእነርሱ
ሊገልጥና ለዘወትርም በዚያ እንደሚገኝ ኪዳን በመግባት ነበር። እስራኤል
መቅደሱ ብቻ ስላለ የምትወድቅ አልመሰላትም፤ እግዚአብሔር መቅደሱን የሚያፈርስ አልመሰላቸውም፤ እነርሱ በኀጢአት እየባሱና እየበረቱ
በሄዱ መጠን፣ የእግዚአብሔር ክብር ከእነርሱ እንደሚነሳ አላስተዋሉም። እግዚአብሔር ግን በኀጢአት ለጸናችውና አንድያ ልጁን በሞት
አሳልፋ በመስጠት፣ ባለማመን ለጸናችው እስራኤል መቅደሱን በማፍረስ የኹለተኛው ቤተ መቅደስም ታሪክ በመፍረስና በመጥፋት ተጠናቀቀ።
ሦስተኛው ቤተ መቅደስ
እንግዲህ ኹለቱ መቅደሶች በሚያሳዝን መልኩ በመፍረስና በመውደም ታሪካቸው
ተዘግቶአል፤ መካከለኝነታቸውም አብሮ በአንድነት አብቅቶለታል፤ ከእንግዲህ በሰው እጅ በተሠራ መቅደስ አማካይነት እግዚአብሔር ክብሩን
አይገልጥም፤ አይሁድ አርባ ስድስት ዓመት የፈጀ መቅደስ አለን ቢሉም፣ ጌታ ኢየሱስ ግን መቅደሳቸው እንደሚፈርስና የራሱ መቅደስነት
ግን በሕያው ትንሣኤ ለዘላለም ኗሪ መኾኑን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። … እርሱ ግን ስለ
ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል።
ፊተኞቹ ኹለቱ መቅደሶች፣ ለቀደመው ኪዳን መካከለኛ ወይም የአምልኮ ማዕከል
ነበሩ፤ ማንም በዚያ ሄዶ ቢጸልይ እግዚአብሔር ይሰማ፣ ዓይኖቹም በመቅደሱ ወደሚጸለየው ሰው ጸሎት ይመለከቱ ነበር፤ በመቅደሱ በእውነትና
እንደ ሕጉ ሥርዓት በመገኘት ለለመነ ኹሉ መልስ ነበረው፤ አኹን ግን የምንሰማበትና የምንታይበት አንድ፣ የማይፈርስ፣ ዘላለማዊ የኾነ
መካከለኛና የአምልኮ ማዕከል አለን፤ እርሱም በአይሁድ እጅ የተገደለ፣ ነገር ግን ከሙታን መካከል በመነሣት ሕያው ቤተ መቅደስ የኾነ
ነው።
እርሱን በማመን በስሙ የትም ኾነን፣ በማናቸውም የሕይወት ዘይቤ ውስጥ አልፈን፣
ብንለምነውና ብንማጸነው የሚሰማንና የሚመለከተን አንድ ሕያው መቅደስ አለን፤ በነዚያኛዎቹ መቅደሶች የእግዚአብሔር ክብር ሞልቶ እንደ
ታየ እንዲሁ፣ በሦስተኛውና በመጨረሻው መቅደስ የእግዚአብሔር ጸጋና እውነት ተመልቶ አየነው፤ ቅዱስ ቃሉም፦ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና
እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” እንዲል።
እነሆ የገባንበትና የምንሰማበት ቤተ መቅደስና የአምልኮ ማዕከል አለን፤ እርሱም
ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። መቅደሱ የክብሩ መገለጫ ነው፤ የክብሩ ምልአት በመቅደሱ አለ፤ እንዲሁ የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ
የኾነው፣ አማናዊው መቅደስ ክርስቶስ አለን፤ እርሱ ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አያድርም፤ ራሱ በሠራው መቅደስ፣ ሕያውና ቅዱስ ሰውነት
ያድራል እንጂ። መቅደሱ ሕያዋን ድንጋዮችና እልፍ መንፈሳዊ ቤቶች አሉት፤ “እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ
ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።”
እንዲል።
ክርስቶስን በማመን
የምትከተሉ ኹሉ ሆይ! ሦስተኛውን መቅደስ ክርስቶስ ኢየሱስን አክብሩት፤ ውደዱት፣ አምልኩት፣ የአምልኮአችሁ ማዕከል እርሱ ብቻ ይኹን፤
ከእርሱ በቀር የምትሰሙበትና የምትደመጡበት መቅደስ እንዳላችሁ አታስቡ፤ ወደ ክብሩና መንግሥቱ የገባንበትና ገብተንም ያረፍንበት
አንድ፤ ቅዱስና ሕያው ቤተ መቅደስ አለን፤ እርሱ አይሞትም፣ ሞትን ውጦአልና፤ ጠላቶቹን ኹሉ ድል ነሥቶ በክብር በሰማያት በግርማው
ቀኝ አለ፤ ክብርና ኀይል፣ ባለጠግነትም ድል ለነሣው ቤተ መቅደስ ለክርስቶስ ኢየሱስ ይኹን፤ አሜን።
መልካም አተያይ።ቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDeletetebarek
ReplyDeleteበውነት ደስ ብሎኛል ተባርክልኝ
ReplyDelete