Monday 2 March 2020

ቅድስት - ኢየሱስ ከሰንበት ይበልጣል!

Please read in PDF

  “ሰንበት” የሚለው ቃል፣ በዕብራይስጥ ትርጉሙ ማቆም ወይም መተው ማለት ነው።[1] “ሰንበት … የዕለት ስም ሰባት፣ ሰባተኛ ቀን፤ ሰባተኛ ዓመት ማረፊያ ዕረፍት…”[2] ማለት ነው። በቀደመው ኪዳን ትእዛዝ መሠረት፣ “ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ …” (ዘጸ. 20፥10) እንዲል፣ ማናቸውም የኪዳኑ አማኝ፣ የዘወትር ሥራውን ትቶ ወይም በማረፍ በኹለንተናዊ መልኩ እግዚአብሔር አምላኩን በአምልኮ ለማክበር የሚጠቀምበት ቀን ነው፤ የሰንበት ቀን ለዕረፍትነት ወይም ለአምልኮ መሰጠቱ ከሕጉ በፊት መኾኑን አለመዘንጋት፣ ለኹሉ የሰው ዘር መሰጠቱን እንድናስተውል ያደርገናል

   ከዚህም ባሻገር ሰንበትን፦
1.      እግዚአብሔር አምላክ ባርኮታል፤ ቅዱስ እንዲኾንም በእግዚአብሔር ተለይቶአል፣
2.     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰንበትን ወይም የዕረፍት ቀንን መርህነት አልሻረም፤ ነገር ግን አይሁድ ሰንበትን ያከብሩ የነበሩበትን ግብዛዊ መንገድና አመለካከት ፈጽሞ አልተቀበለውም፤ እጅግ ነቅፎታል፤ (ሉቃ. 13፥10፤ 14፥1)። ምክንያቱም የአይሁድ ሰንበት አከባበር፣ በሰንበት የተራበ ሰው መብላትን እንኳ የሚከለክል ነበርና፤ (ማር. 2፥23-24)።
  በተያያዘ መንገድ የዕረፍት ቀን ቅዱስ ዓላማ፣ በክርስቶስ ለሚያምኑ አማኞችም እጅግ ታላቅ ፋይዳ አለው፤ በብሉይ ኪዳን የቀን መባረክ መሠረቱ፣ ኹለንተናዊ በኾነ መንገድ ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው፤ በዝንባሌአቸው፣ በንግግራቸው፣ በሥራቸው ኹሉ፣ በአምልኮአቸው፣ በኑሮአቸው ጭምር ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበትና ለእግዚአብሔር መለየታቸውንም ጭምር የሚመሰክሩበት ቀናቸው ነው። ይህን የሚያደርጉት ሰንበት የኪዳኑ ምልክትና ለእግዚአብሔር የመለየታቸው ማሳያ ጭምር መኾኑን ለማመልከት ነው።
  ልክ እንዲኹ፣ ክርስቲያኖችም የአምልኮ ቀናቸውን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በማድረግ ለእግዚአብሔር ለይተውታል፤ የለዩበትም መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተጠቅሶአል፣ “ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ …”፣ “እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።” (ሐዋ. 20፥7፤ 1ቆሮ. 16፥2) እንዲል፣ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን አማኞች፣ የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን ማለትም እሁድን ለአምልኮ፣ የጌታን እራት ለመቁረስ፣ ለምስጋናና ሌሎችንም ለመርዳት፣ ትንሣኤውንም ለማክበር ለይተውታል። በቤተ ክርስቲያንም ታሪክ ቀኑ ለአምልኮ መለየቱንም እናስተውላለን።
3.     በሰንበት እስራኤል ኹሉ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚሰጥበት ቀን ነበር፤ (ዘጸ. 20፥8-10፤ ዘዳግ. 5፥14፤ የእግዚአብሔር መኾናቸውንም ምስክርነት የሚሰጡበት ቀን ነው፤ ቀኑ ከውድቀት በፊት እንደ መሰጠቱ፣ በረከትነቱ ለመላው የሰው ዘር የተሰጠ መኾኑን እናስተውላለን።
   በአዲስ ኪዳን ላይ ይህ ዐሳብ እጅግ ተብራርቶ እናገኘዋለን፤ በግልጥ ቃልም እንዲህ ይላል፣ “ስለ ሰባተኛውም ቀን  በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና። ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ይላል።” (ዕብ. 4፥4-5 ዐመት)። እግዚአብሔር ከሥራው በሰባተኛው ቀን “ዐርፎአል”፣ የተጠራነውና የተጋበዝነው የዚህ ታላቅና ቅዱስ ዕረፍት ተካፋዮች እንኾን ዘንድ ነው፤ እስራኤልን  “ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ሲል፣ ዕረፍቱ የራሱ የእግዚአብሔር መኾኑን እናስተውላለን እንጂ፣ ቀኑ በራሱ ዕረፍት መኾኑን አይነግረንም።
   እስራኤል ባለማመን ምክንያት ወደ ዕረፍቱ አልገቡም፤ አለማመን ከዕረፍቱ ያጎድላል። አለማመን ለመታዘዝ አለመፍቀድና ፍጹም የኾነ እንቢታን፣ ዓመጻን አመልካች ነው። ልክ ያኔ እስራኤል በምድረ በዳው ለመታዘዝ እንቢ በማለት፣ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት እንዳልወደደች እንዲኹ፣ ዛሬም አለመታዘዝ በክርስቶስ ኢየሱስ ከተሰጠን ዕረፍትና ፍጹም አርነት ያጎድለናል። ለሚያምኑ አማኞች በቀኑ ውስጥ ዕረፍት አለ ብንል እንኳ፣ ዕረፍቱ የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ወይም የቀኑ ወይም የሌላ አካል አይደለም፤ የራሱ የእግዚአብሔር ዕረፍት ብቻ እንጂ።
   በቀደመው ኪዳን ታዛዥ የነበሩትን፣ ኢያሱ ወደ ዕረፍታቸው ርስት አደረሳቸው፤ ነገር ግን ይህ ዕረፍት በቂና የመጨረሻ አልነበረም፣ ጥላ ነውና አካሉ ዘንድ አያደርስም፤ “ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።” እንዲል ለእነርሱ የቀረላቸው፤ ለእኛም የቀረልን ዕረፍት አለ፤ ከኢያሱ የሚበልጠው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ዕረፍታችን፣ በዕረፍቱም የሚያሳርፈንም ነውና፤ በቀደመው ኪዳንም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “እግዚአብሔርም፦ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው።” (ዘጸ. 33፥14)። አዎን በቀደመውም ኪዳን አሳራፊው ያህዌ ኤሎሂም ነው፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የአብ አንድያ ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!
   ባለማመን ላላረፉትና ለሚቅበዘበዙት ዛሬም እግዚአብሔር፣ “ዛሬ ብሎ እንደገና አንድ ቀን በመቅጠር” የንስሐ በር ለመላው የሰው ልጅ አዘጋጅቶአል፤ ድምጹን እየሰሙ አለመስማት አለመታደል ነው፤ የመዳን ቀን ዛሬ ነው፤ ዛሬ ተብሎ የተቀጠርልን ቀን አኹን ነው፤ (2ቆሮ. 6፥2) ይህን ዕድል አለመጠቀም ራስን ማቅበዝበዝ፤ ዕረፍት መንሳት ነው፤ ኀጢአት ያላረካችሁ፣ ዛሬም እንኳ ለኀጢአት በቀጠሮ ላይ ያላችሁ፣ በምድረ በዳው ዓለም ላይ ባለማመን የምትቅበዘበዙ ሆይ! ተወዳጁን ኢየሱስ በማመን ተመለሱና እረፉ! ኢየሱስ እርሱ ሰንበት ከሚባለው ቀን ይበልጣል፤ ያሳርፋልም!
  “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል።
   እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴ. 11፥28)
አሜን።



[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 74 በግሪክም በተመሳሳይ ትርጕም “ሳባቶን - ዕረፍት፣ ሥራን መተው” ማለት ነው።
[2] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ ገጽ 874

1 comment:

  1. ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ የተወደድህ ወንድማችን

    ReplyDelete