Sunday, 8 March 2020

በእኔ የተናገርክ … ተባረክ!

Please read in PDF

አገልግሎትን በክብር መጨረስ መታደል ነው። ያለ መንፈስ ቅዱስ ዕርዳታም፣ ማንም አገልግሎቱን በክብር መጨረስ አይቻለውም። ሩጫውን ስለ ጨረሱ ቅዱሳን ስናስብ፣ ልባችን ታላቅ ሐሴት ያደርጋል፤ በመደነቅም ይሞላል፤ ኹላችን እንዲህ ብንኾን፣ በሕይወት ዘመናችን እንደ እነርሱ ባለ ትጋት ጸንተን፣ እርግጠኞች ኾነን፣ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤” ማለት ብንችል እንዴት በታደልን?! … አዎን! ለዚህ ተጠርተናል!!!


እግዚአብሔር አልተለወጠም፤ አዲስ ጠባዩንም በእኛ አይጀምርም፤ ትላንት ከአባቶቻችን ጋር የሠራው ያው እግዚአብሔር፣ ዛሬም ባልተለወጠ ማንነቱ አለ፤ እነርሱን አስጀምሮ እንዲጨርሱ ከረዳ፣ ለእኛም በስሙ አምነን በመታዘዝ ለምንከተለው፣ ፈጽሞ የታመነና የማይለወጥ ነው። ብዙ ጊዜ ባለመታመን፣ በጥርጣሬ፣ በመዛል … ተከትለነው እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን ፈጽሞ አልጣለንም፤ ሩጫውን እንድንሮጥ ጸጋ አበዛልን፤ ምሕረት አገነነልን፤ ዕድሜ ሰጥቶ፣ ጤንነት አሟልቶ ካሰብነውና ከለመድነው፣ ከወደድነውና እንዲኾን ከሻትነው በላይ አለልክ ጠበቀን ታደገን፤ አዎን እርሱ አይለወጥም!
በእነዚህ ስምንት ዓመታት በብዙ ድካም ውስጥ ባልፍም፣ ብበድለውም፣ በብዙ ዝለትና ውድቀት ብንኮታኮትም … ማስተዋሉ የማይመረመረው፣ የማይደክመውና የማይታክተው፤ የዘላለምና የምድር ዳርቻ ፈጣሪ በፍጹም በመታዘብ አልፎኝ አልሄደም። ብዙ ጊዜ ለሰዎች ከመናገሬ በፊት፣ እኔን ፊት ለፊት ተናገረኝ፣ በፍቅር ወቀሳው ወቀሰኝ፤ አብረውኝ እንዲኖሩ የፈቀድኩትንና ልለያቸው የማልችላቸው የመሰለኝን እልፍ ስንፍናዎቼን እያጠራ፣ እየገረዘ፣ እየሠራ፣ እንያነጸ፣ እያበረታ … ከበላዬ አንከባለለልኝ፤ ሳይታዘብ፣ ሳይጠየፍ፣ ሳይሰለች … እጅግ ደካማ በኾንኩ በእኔ፣ ምሕረትና ይቅርታውን አብዝቶ፣ በልጁ ወዶኝ፣ ከኃጢአት ረግረግ አውጥቶኝ … ሊናገርብኝ እንደ ዕቃው ስለ ተጠቀመኝ ጌታዬን እጅግ አድርጌ እባርከዋለሁ፤ አባባ ከፍ በልልኝ፤ በእኔ የተናገርክ ተባረክ፤ አሜን።
ስምንቱ የጡመራ መድረክ አገልግሎቴ፣ ከእግዚአብሔር በታች አብረውኝ በብዙ ያገለገሉ ውድ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ፤ ጌታ እነርሱን ስለሰጠኝ እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ፤ ውድ ወንድሜ ደሬ (እኔን እንደ አንተ ደፍሮ ማን ይቆጣኛል?! ይወቅሰኛል?! ተወዳጅ ወንድም!)፣ ወንድሜ ሙሌ (ትዳርህን አዶናይ ይባርከው! ይኸው “አገልግሎቱን ጀምር” ብለኸኝ እዚህ ደርሶአል፤ ጌታ ባንተ በኩል ተናግሮኝ መከሩ እዚህ ደርሶአል፤ ተባረክልኝ!)፣ ወንድሜ አዲስ (“ስለዚህ ነገር ጽፈሃል?፣ በእገሌ የተላለፈውን ተመልክተሃል?” … እያልክ የምትኮረኩረኝ … ጌታ ኢየሱስ ኅሊናህን ይባርከው)፣ ወንድሜ ቢኒ (ጽሑፉ ለብዙዎች እንዲደርስ በተጋኸው ትጋትህ … አዶናይ ዘመንህን ይባርከው፤ የእጅህን ሥራ ያከናውንልህ)፣ ተወዳጅ እህቴ ሰብሊ (ሎጎዎችን የምታሰማምሪልኝ … አዶናይ ውብ ልጆችሽንና እጅሽን ይባርክልሽ፤ ያህዌ ደስታሽን ያብዛልሽ)፣ በጸሎት፣ በዐሳብ፣ በማንበብ፣ አስተያየት በመስጠት፣ በመተቸት፣ በማበረታታት፣ “በጥላቻም ይኹን”በተለያየ መንገድ … ከጐኔ ለነበራችሁ ኹሉ ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛላችሁ፤ አሜን።
ደግሞ እግዚአብሔር ሌላ የአገልግሎት ዘመን ስለ ጨመረልን ክብሩን እርሱ ብቻ ይውሰድ፤ ተወዳጆች ሆይ! ጌታ በነገር ኹሉ እንዲያጸናኝ በጸሎታችሁ እርዱኝ፤ እስከ ኢየሱስ ቀን በቅዱስ አገልግሎት እጸናና፣ የኢየሱስን ወንጌል የሰው ፊት አይቼ ሳላዳላ መናገርና መመስከር እንድችል በምልጃችሁ አስቡኝ፤ ጸልዩልኝ። የክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ከኹላችን ጋር ይኹን፤ አሜን።

12 comments:

  1. አቤኒ የረዳህ ይባረክ

    ReplyDelete
  2. ደግሞ እግዚአብሔር ሌላ የአገልግሎት ዘመን ስለ ጨመረልን ክብሩን እርሱ ብቻ ይውሰድ፤ amen

    ReplyDelete
  3. ዘመንህ ይባረክ ወንድም አቤኒ፡፡ በብሎግህ ብዙ ተምረናልና ተግተህ ቀጥልበት

    ReplyDelete
  4. የረዳህ ጌታ ይባረክ

    ReplyDelete
  5. የረዳህ ጌታ ይባረክ

    ReplyDelete
  6. የረዳህ ጌታ ይባረክ

    ReplyDelete
  7. zemenih befitu yilemlm tebark aben

    ReplyDelete
  8. tsega yibzalih wendme

    ReplyDelete
  9. tasaznaleh betam....kante gn yehn altbkm nbr manh

    ReplyDelete
  10. tasaznaleh betam....kante gn yehn altbkm nbr manh

    ReplyDelete
  11. ፓስተር አቤኔዘር ተክሉ እንዳትኾን ብቻ?!
    የአቤኔዘር ተክሉ የሚል ገጽ(page) አለና የተወገዘና መናፍቅ ነውና ክርስቲያኖች ተጠንቀቁት!
    ከጉዳዩ ስሙ አስደነገጠኝኮ ሰዎች።
    ይህ ሰው ኦርቶዶክስ እየመሰለ የሚቀስት የነጭ ፓስተሮች ዕቃ ነውና ከተኩላው ራቁ ንቁ።

    ReplyDelete
  12. ጅል ቢጤ ነህ

    ReplyDelete