Wednesday 26 February 2020

ቤተ ክርስቲያንንም ለ“መደመር”?፤ ተዉ!

Please read in PDF

   በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነገሥታት “በዶግማና በቀኖና” አንድ ያልነበሩትን “አብያተ ክርስቲያናት”፣ አንድ ለማድረግ እጅግ መጣራቸውን እናስተውላለን።


   “ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላ ለሚቀጥሉት ፩፻፶ ዓመታትያህል የነገሡ የቊስጥንጥንያ ነገሥታት ቤተ ክርስቲያንን ለማዋሐድ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ ከ፬፻፸፬-፬፻፺፩ ዓ/ም የነገሠው ዘይኑን(ዚኖን)፣ ከ፬፻፺፩-፭፻፲፰ዓ/ም የነገሠው እናስታሲዮስ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ የሚለውን የተዋሕዶ እምነት ተቀብለው ቤተ ክርስቲያን በሰላም የምትመራበትን መንገድ ለመፈለግ ተነሳሰተው ነበር። ለዚህም በጎ ፈቃድ መሰናክሉ የኬልቄዶን ጉባኤ ውሳኔና የልዮን ጦማር መኾኑን በመገንዘብ የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ አባ አጋግዮስ(አካኪዮስ) እና ንጉሡ ዘይኑን ተስማምተው ይህን ለመሰረዝና ቤተ ክርስቲያንንም ወደ ጥንታዊ የተዋሕዶ እምነቷ ለመመለስ ከአንጾኪያና ከእስክንድርያው ፓትርያርኮች ጋር ውይይት ጀመሩ።”[1]

   ከጥንት ጀምሮ፣ ነገሥታት ኅይላቸውን ለማደርጀትና ሰፊውን የግዛት ክፍል ያለ ኮሽታ ጠቅልለው ለመግዛት ካላቸው ብርቱ ጉጉት የተነሣ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማዋሐድ ወይም “ለመደመር” ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ ነበር፤ በእርግጥም በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ውጥረት የቅርብ ዘመን ትዝታ አይደለም፣ ይልቁን ከጥንት የጀመረ እንጂ። ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “የእግዚአብሔር ከተማ” በተባለ መጽሐፉ፣ “በእግዚአብሔርና በሰው ከተማ መካከል ከፍ ያለ ውጥረት እንዳለ” ተናግሮአል። አዎን! ውጥረቱ ጨርሶ የሚቈረጠውና የሚያበቃው በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ብቻ ነው።
   እንግዲህ ከሰሞኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓቢይ ለኹለተኛ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን “አንድ የማድረግ” ተግባራቸውን ለማከናወን ዐሳብ ማቅረባቸውን ሰምተናል። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን “ማስታረቃቸውን” ከዚህ በፊት አይተናል፤ ዳሩ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ያልረገጡ ጳጳሳት መኖራቸውና ዕርቁም “ስሙርና ኅሩይ” መኾኑ ለብዙዎች ግር ቢያሰኝም። ይህ እንዲህ እነዳለ ነው ታዲያ ጠቅላዩ በድጋሚ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት “አንድ እንዲኾኑ” ዐሳብ ያቀረቡት።
   እናም በዚህ ጉዳይ ላይ መናገርን ወደድኹ፤ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት ቀጥተኛ አይደለም፤ ቀጥተኛ ስላልኾነም መንግሥት ለሚሠራው ሥራዎች ኹሉ ቀኝ እጇን አትሰጥም። ከመንግሥት ጋር በአንድ አገርና አብረው የሚኖሩ ቢኾኑም፣ “ቤተ ክርስቲያን መራሔ እሴቷ ከመንግሥት ፍጹም የተለየ በመኾኑ ጉርብትናው ሰላማዊ አይደለም”[2]፤ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን ደግሞ የቄሣርና የእግዚአብሔር መንግሥት አንድ አይደሉም፤ ቀጥተኛ ኅብረትም የላቸውም።
   የቄሣራዊነት ጠባይ ማጥመድና መሰለል፤ ሸማቂነትም ነው (ማር. 12፥14፤ ሉቃ. 20፥20) ፈሪሳውያንና ሄሮድስ ኢየሱስን “መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን (ማር. 12፥14)፤ ብለው የድለላና የሽንገላ ንግግር በመጠቀም፣ “ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ?” በማለት የሽመቃ ጥያቄን አቅርበውለታል። ኢየሱስ ግን የተሰወረውን ገላጭ፤ ኹሉን አዋቂ ነውና፣ ከሮማውያን ጋር በማጣላት ለፍርድ ሊያቀርቡት ቋምጠው የነበሩበትን የተንኮል ጥያቄአቸውን አወቀ።
  ቄሣር “ጠቃሚ” ነው፤ መንድ ይገነባል፣ የልማት አውታሮች ይዘረጋል፣ ፍትህ ያሰፍናል፤ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ይሠራል፤ ለዚህ ሥራው ግብርን መክፈል የእግዚአብሔር ባላንጣ መኾን አይደለም፤ ነገር ግን ቄሣር ኹል ጊዜ ቄሣር ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር ይልቅ እንድንሰማው ከወደደ፣ እንቃወመዋለን እንጂ አንታዘዘውም፤ “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤”፣ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።” እንዲል፤ (ሐዋ. 4፥19፤ 5፥29)።
   የቄሣር ምስል ያለበት የሮማውያን ገንዘብ የቄሣር ብቻ ስለ መኾኑ፣ የምስሉ በገንዘቡ ላይ መኖር በቂ ምስክር ነው፤ ስለዚህም የቄሣር ለቄሣር ሊሰጥ ይገባዋል፤ የራሱ ነውና። ቄሣር የራሱ ምስል ያኖረበትን ገንዘብ ማስተዳደር፣ መቈጣጠር፣ ማዘዝ፣ መናዘዝ … መብቱ ነው፤ ሰዎች አገራችን ለሚሏት፣ ሥልጣናችን ለሚሉት፣ ተወልደንበታል ለሚሉት ብሔራቸውና ዘራቸው የሚዋደቁት “ቄሣራዊ ምልክታቸውን” በዚያ ስላኖሩ ወይም እንዳላቸው ስላመኑ ነው።
  ቤተ ክርስቲያን ግን፣ የሰማይ አምላክ ፈቃድ ፈጻሚ ናት፤ ኹለንተናዋም በእርሱ ለእርሱ ከእርሱ ነውና። ራሱንም አሳልፎ የሰጠላት የእግዚብሔር አንድያ ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን ስንል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚለው ስም ያመኑና የዳኑ አማኞችን ነው፤ አስቀድሞም ቢኾን ሰው የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፤ የእግዚአብሔር “ጽሕፈት” መልክና አምሳል በሰው ልጅ ላይ ታትሞአል፤ (ዘፍ. 1፥27)፤ ስለዚህ ሰዎች ኹሉ የእግዚአብሔር ገንዘቦች ብቻ ናቸው፤ ሰዎች የእግዚአብሔር ገንዘቦች ከኾኑ ቤተ ክርስቲያንማ እንዴት አትልቅ፤ አትበልጥ?!
  ስለዚህም ቤተ ክርስቲያንን ሊያዝዝና ሊናዝዝ የሚገባውና ሥልጣንም ያለው፣ የሞተላት ጌታዋና ራስዋ የኾነው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ በመንፈሱ አንድ ሊያደርጋትም የሚቻለው እርሱ ብቻ ነው፤ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ. 4፥3) የተባልነውም ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ብቻ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ራሷ እንኳ የመንፈስ አንድነቷን በራስዋ መጠበቅ አትችልም።
   እናም ክቡር ጠቅላዩ ሆይ! እባክዎ፣ አብያተ ክርስቲያናት መካከል እየገቡ “አንድ ኹኑ” የሚሉትን ዐሳብዎን ተዉት! ምክንያቱም እንድ እንዲኾኑ የሚጋብዙትና እየጋበዙ ያሉት፣ የለየላቸውን መናፍቃንና እውነተኛ የኢየሱስ አማኝ ደቀ መዛሙርትን ነውና፤ በቴሌቪዥን መታየታቸውና ብዙ ሕዝብን ማስከተላቸው፣ በራሱ የክርስትና ፍሬም የአማኝነት መለኪያም አይደለም። ስለዚህም እባክዎን ጠቅላዩ ሆይ! ቤተ ክርስቲያን አባትና አጽናኝ፣ ራስና ጌታ አላትና እጅዎን በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አይስደዱ፣ አይሰድሩ!
   በገዛ መንገዳቸው ሔደው በክርስቶስ ላይ የሚቀማጠሉና በራሳቸው ጌቶችና አለቆች የኾኑትን “ስመ ገናናና ስግብግብ ሃብታም ስሑት መምህራንንና አገልጋዮችን”፣ ከእውነተኞች ጋር አንድ ኹኑ ብለው አይጋብዙ! ቤተ ክርስቲያን እንደሚዋሃዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምትዋሃድ አይደለችምና፣ እባክዎን በቄሣራዊነትዎ ጸንተው፣ ከቤተ ክርስቲያን ላይ እጅዎንም ዐሳብዎንም ይሰብስቡ!
   እውነተኛ እረኞችና አገልጋዮች ሆይ!
  “እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።” (1ጴጥ. 5፥1-4)
ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት፤ ከቶ ለማይጠፉትም ይኹን፤ አሜን፤



[1] አባ ጎርጎርዮስ(ሊቀ ጳጳስ)፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ 1978 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 161-62
[2] ሚኒሊክ አስፋው፤ ክርስቲያዊ ሥነ ምግባር፤ 2004 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ራእይ አሳታሚ ሕትመት ፋር ኢስት ትሬዲንግ፤ ገጽ 95

1 comment: