አስቀድመን እንደ ተናገርነው፣ “ኒው ኤጅ ሙቭመንት”[1] አዲስ “እምነት” እንደሚመስል ስያሜው ቢናገርም፣ ነገር ግን
ትምህርቱ፣ ከኖስቲዝም፣ ከክርስትና ከሂንዱና ከሌሎችም ቤተ እምነቶች የተቀዳና የተለቃቀመ ትምህርት ነው።[2] ከክርስትና በቀዳው አመለካከቱ ስለ እምነት የሚናገር ቢመስልም፣
ዕውቀትን በማምለክ ደግሞ ኖስቲዝምን “ቁርጥ ነው”፤ በልምምዶቹ ከጥንቁልና ጋር ቢመሳሰልም፣ ክርስቲያኖችን ለመምሰል ግን ከመጽሐፍ
ቅዱስ በመጥቀስ ደግሞ “የሰይጣንን ብርሃናዊ መልክ” ለመያዝ ይጥራል!
በኢትዮጵያ ምድር የዚህ ትምህርት ቀጥተኛ አስተላላፊዎችና አስተማሪዎች
ደግሞ አሸናፊ ታዬ፣ ኤልያስ ገብሩ(ዶ/ር)፣ ዳግማዊት ክፍሌ፣
ነፃነት ዘነበ፣ ማንያዘዋል እሸቱና ሌሎችም ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይህን ትምህርቶቻቸውን ከምዕራቡ ዓለም የስህተት አስተማሪዎች ቀድተውና
ኮርጀው ያመጡት እንጂ ከራሳቸው “ያፈለቁትና ያነቁት” አይደለም። እጅግ አስቂው የነዚህ ሰዎች መገለጫ ደግሞ፣ አልፎ አልፎ
“ሃይማኖተኛ” መስለው በቤተ እምነቶች ውስጥ “ሜዳዊ ሥርዓትን ሲፈጽሙ” እንመለከታቸዋለን፤ ነገር ግን ተቀባይነትንና ደጋፊን
ላለማጣት የሚያደርጉት እንጂ የትኛውም የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተማሪና ተከታይ የየትኛውም እምነት ተከታይ ሊኾን
አይችልም! ለዚህም ነው ከኹሉም እምነቶች የተውጣጣ “ሃይማኖት” እንጂ፣ ወጥና ቋሚ አስተምህሮ የሌላቸው። ከዚህም የተነሳ
ትምህርቶቻቸው ኹሉንም ቤተ እምነት መራዥና ተንኳሽ ናቸው።
ከዚህ በመቀጠልም፣ ትምህርቶቻቸው ከክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች ጋር በግልጥ እንደሚጋጭ ወይም የክርስትናን ዋና ዋና
ትምህርቶችን እንደሚቃወም በማሳየት አማኞች ከነርሱ እዲርቁና እንዲጠበቁ እናሳስባለን፤ የሚቃወሙአቸው ዋና ዋና ትምህርቶች የሚከተሉት
ናቸው፤
1.
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥልጣንን አያከብሩም!
ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ መለኮት ወይም መጻሕፍተ አምላካውያት
በመኾናቸው ምክንያት፣ ለአማኞች ኹሉ የተሰጡ የሕይወት ትእዛዛትን፣ መመሪያዎችን በውስጣቸው የያዙ ናቸው። ከኹሉ በሚልቅ መንገድ፣
ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ጌታ ክርስቶስ የሚመሰክሩ (ዮሐ. 5፥39) ናቸውና፤ ወደ ቀኝም ወደ
ግራም ሳንል (ኢያ. 1፥7) ሙሉውን ቃሎቻቸውን ልንቀበል ይገባናል፤ ደግሞም በማናቸውም ነገሮቻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
ሥልጣናዊና ገዢ እንደ ኾነ እናምናለን።
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰጠን በቂና እውነተኛ ትምህርትን
የያዘ መጽሐፍ ነው። በነቢያት እንደ ጥላ በትንቢትና በምሳሌ የተነገረው ኹሉ፣ በምልዑ መገለጥ በክርስቶስ አካልነት ፍጻሜ አጊኝተዋል
(ቈላ. 2፥17፤ ዕብ. 10፥1)። የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ “መገለጥ ኹሉ እንዳላለቀ፤ ገና አያሌ መገለጥ እንዳለ፤ ገና የሚጨምር
መገለጥ እንዳለ” እንደሚናገሩና እንደሚያምኑ በክፍል ሦስት ላይ ማንሳታችንን አንዘነጋም።
እኛ ክርስቲያኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስ በቂና ምሉዕ መገለጥ እንዳለው
ፍጹም እናምናለን። “በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ የተረከልን” እውነት (ዮሐ.
1፥18)፣ “በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ የተናገረን” (ዕብ. 1፥2)፣ “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ እንሆን ዘንድ፥
ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር የሚጠቅመን” (1ጢሞ. 3፥16-17) ስለ እግዚአብሔር ትክክለኛ
ዕውቀትና እውነት፣ ለመዳናችን የሚበቃና ምሉዕ መልእክትን የያዘ የመለኮት መገለጥ ያለበት መጽሐፍ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በቂ መገለጥ አለው ስንል፣ ለሕይወታችን፤ ለትምህርታችንና ለልምምዳችን ኹሉ ትክክለኛነት የሚያስረግጥ እውነተኛ ዋቢዎችን በውስጡ ይዞአል ማለታችን
ነው። የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ የኾነው ክርስቶስ ብቻ እንደ ኾነ እናምናለን፤ ለመዳናችንና ለዘላለም ጉዳያችን ክርስቶስ
ያልነገረን፤ እንዲነግረን የምንጠብቀው ሌላ ነገር የለንም፤ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረለት ክርስቶስን የማይሰማ ርሱ ምንም
ሊሰማ አይችልም፤ “ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ …” እንዲል (ሉቃ. 16፥31)።
የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን ማክበር ስንልም፣ በውስጣቸው ላሉ ቃላት መታመንን፣ ፍጹም መታዘዝን፣ ሳይነጥቡና
ሳይጎድሉ ፍጹም መቀበልን የሚያመለክቱ ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነትም በመመራትና ከዐውዱ ጋር ፍጹም በተዛመደ መንገድ
ለሚመጣልን መልእክት መታመንና መታዘዝ ማለትም ነው።
እውነተኛ አማኞች በክርስቶስ የተገለጠውን እውነተኛ መገለጥ የኾነውን መጽሐፍ ቅዱስን ጊዜ ወስደው፤ በጸሎት ተግተው፤
በመንፈስ ቅዱስ ብርሃንና ፍርሃት ውስጥ ኾነው ቃሉን ያጠናሉ፤ ይፈክራሉ፤ ይተረጒማሉ፤ ይመረምራሉ እንጂ፣ አዲስ መገለጥ
ይመጣልኛል እያሉ ራሳቸውን እንደ አዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ጨርሶ አያታልሉም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ነው፤ ስለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የሚጋፉ ሰዎች ራሱ እግዚአብሔርን
የሚቃወሙና የሚቃረኑ ሰዎች ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ “ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ
ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች” (ሐ.ሥ. 20፥29-30) ናቸው። ለዚህ ደግሞ እውነተኛ ምሳሌዎቹ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ
አስተማሪዎችና ተከታዮች ናቸው።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።”
(ኤፌ. 6:24) አሜን።
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment