በባለፈው ክፍል እንደ ተመለከትነው፣ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተማሪዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን
ሥልጣንን ጨርሶ እንደማይቀበሉና እንደሚያቃልሉ አንስተናል፤ በዚሁ ዐሳብ ላይ ጥቂት እንጨምርና ወደሚቀጥለው እንሄዳለን።
የጽድቅ መንፈስ የኾነው መንፈስ ቅዱስ ወደ ጽድቅና ቅድስና የሚመራና ደግሞም እርሱ የቅዱስ ቃሉ
ባለቤትና ደራሲ ነው፤ ስለዚህም ቅዱስ ቃሉ የሕይወታችን፣ የአምልኮአችን፣ የአገልግሎታችን፣ የአስተምኅሮና የምልልሳችን ኹሉ ማዕከልና
ቃኚ ነው። ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት በትክክል ሳንረዳ ተሳስተን ብንወድቅ፣ እኛ እንጎዳለን እንጂ ቃሉ እውነተኛና የታመነ
ነው። “ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” እንዲል (2ጢሞ. 2፥13)።
2. አንድ አምላክን ይክዳሉ፤
አንዳንዶች
የአምልኮ መልካቸውን እንደ ጠበቁ እግዚአብሔርን በተግባራቸው ይክዱታል፤ “… እግዚአብሔርን የሚያመልኩ መስለው ይታያሉ፤ የአምልኮትን ኀይል ግን ይክዳሉ፤ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ራቅ።”
(2ጢሞ. 3፥5) እንዲል። ከውጭ ሲታዩና ሜዳዊ ሥርዓትን ሲፈጽሙ፣ ጻድቅና አማኝ ሊመስሉ ይችላሉ፤ በልባቸው ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር
የማያምኑ በመኾናቸው፣ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ሊኖር አይችልም። ከዚህም የተነሣ አንዳችም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል የላቸውም።
እንዲህ ያሉ አሳች ወገኖች “የአምልኮ መልክ” ያላቸው ብቻ አይደሉም፤ ምናልባትም “ጥሩ የወንጌል
ሰባኪዎች” ሊኾኑ ይችላሉ፤ ታላላቅ ተአምራትንም ማድረግ “አይሳናቸው” ይኾናል፤ ነገር ግን ክርስቶስ “አላወቅኋችሁም” እንደሚላቸው
ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይመሰክራሉ፤ (ማቴ. 7፥22-23)። ዘወትር መዘንጋት የሌለብን እውነት ግን ጌታ የራሱ የኾኑትን ያውቃቸዋል
(2ጢሞ. 2፥19)። የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አማኞችና አስተማሪዎች አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ይክዳሉ ስንል፣
2.1.
የእግዚአብሔርን መለኮታዊ
ኃይል ፈጽሞ ይክዳሉ እያልን ነው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በኃይሉ ወሰን የሌለው አምላክ መኾኑን ያስተምራል። ሥላሴ የኾነው
እግዚአብሔር ዓለምን በኃይሉ ቃል ያጸና ነው፤ (ዘፍ. 1፥1፤ ዕብ. 1፥3፤ 11፥3)። ፍጥረት ሁሉ በኹለንተናው በእግዚአብሔር
ላይ የተመሠረተ ነው፤ መጽሐፍ፣ “ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ እርሱ ስለ ሆነ ምንም ነገር አይጐድለውም፤
የሰውም ርዳታ አያስፈልገውም።” (ሐ.ሥ. 17፥25) እንደሚል፣ ጌታ እግዚአብሔር አማካሪና ለመንገዱም ፍለጋ የሌለው፣ ብድራቱን
ይመልስ ዘንድ ማንም ምንም ያልሰጠው (ሮሜ 11፥33-35) ኃያል አምላክ ነው።
ይልቁን ደግሞ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራው ይህን ታላቅ ኃይሉን ገለጠ፤ (1ቆሮ. 1፥18፡
24)። ለሚያምኑ ኹሉ ደግሞ፣ እግዚአብሔር አምላክ የማዳን ኃይሉን እንዲኹ ሰጠ፤ (ዮሐ. 3፥16፤ ሮሜ 1፥16)። በተሰጠን በዚህ
ታላቅ ኃይሉ አማካኝነት እኛ ወደ አብ እንገባ ዘንድ አለን፤ “እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን።” (ዕብ. 4፥3) እንዲል። “ለያይቶን
የነበረውን የጥል ግድግዳ ያፈረሰና አይሁድንና አሕዛብን አንድ ያደረገ ሰላማችን ክርስቶስ ነውና።” (ኤፌ. 2፥14 ዐት)።
የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ግን የመስቀሉን ሥራ ያክፋፋል እንጂ ሲቀበለው አንመለከተውም፤ ከእግዚአብሔር
ኃይልን መቀበያው መንገድ የመስቀሉ ሥራ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ ይልቁን ዋናው ምንጭ የግለሰቡ ውስጣዊ፣ መለኮታዊ ማንነቱ
ነው፣ ርሱም ከኹለንተናዊ ኅልውና ከሚሠራው ኹለንተናዊ መለኮታዊ ኃይል ጋር የተገናኘ ነው። ይህም በውስጣቸው ያልተገደበ አቅምና
ከውስጣቸው እውነተኛ መንፈሳዊ ሥልጣን እንዳላቸው ያምናሉ።
“አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ[ሉሲፈር] ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ
ወደቅህ!” (ኢሳ. 14፥12)።
2.2.
እግዚአብሔር በፍጥረቱ
ላይ ያለውን ፍጹም ሉዓላዊነት ይክዳሉ እያልን ነው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው እግዚአብሔር ዘላለማዊ ሉዓላዊነቱን በፍጥረታቱ ላይ ገልጦአል፤
ስለኾነም እግዚአብሔር የወደቀውንና ኀጢአተኛውን መላለም በማይለወጥ ሉዓላዊነቱ ይመራል ብሎ ያስተምራል። ርሱ ሉዓላዊ ስለኾነም ኹሉም
ፍጥረት በእርሱ ላይ ጥገኛ ነው፤ “ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ
ያደርጋሉ።” (መዝ. 104፥27) እንዲል፣ ያለ እግዚአብሔር ሉዐላዊነትና መግቦት ፍጥረት ዕርባና ቢስና ከንቱ ነው።
እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለሙ ሉዓላዊ አምላክ በመኾኑ፣ ኀጢአት እንኳ ከወሰኑና ከልኬቱ ሳያልፍ
በእግዚአብሔር ቊጥጥር ሥር አለ እያልን ነው። አንዱ ፍጥረተ ዓለም፤ በአንዱ አምላክ ሉዓላዊነትና መግቦት የሚጠበቅና እንክብካቤ
ውስጥ ያለ ነው። ልክ እሱ በፍጥረቱ ደስ እንደሚለው (መዝ. 104፥31) ፍጥረትም ወዶና ፈቅዶ ይገዛለታል። “እግዚአብሔር
ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው።” (መዝ. 95፥4) እንዲል፣ በሉዓላዊነቱ ገንዘቦቹ የኾኑትን ፍጥረትም ፈጥሮአል (ዘፍ.
1፥31) ደግሞ ገዝቶ ይኖራል።
ስለዚህ እግዚአብሔር የፍጥረቱ አካል አይደለም፤ ፍጥረትም እግዚአብሔር አይደለም። “ለዘላለም
የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል” የተባለለት እግዚአብሔር አምላክ ብቻ ነው፤ (ኢሳ. 57፥15)።
የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ትምህርቱ ከዚህ በተቃራኒ ነው፤ በዚህ ረገድ ትምህርታቸው ብዙውን
ጊዜ ከብዝኀ አምላክ ወይም “ኹሉም ነገር አምላክ ነው” ከሚለው አስተምህሮ ጋር የተቆራኘ ነው።
2.3.
እግዚአብሔር በፍጥረቱ
ላይ ያለውን ዓላማ ጨርሶ ይክዳሉ እያልን ነው፦ እግዚአብሔር ፍጥረተ ዓለሙን የፈጠረው ለራሱ ክብር ነው፤ “እግዚአብሔር
ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ” (ምሳ. 16፥4)፣ “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም
ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና … ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤” (ቈላ. 1፥15-16)
እንዲል፣ የተፈጠረው ኹሉ የተፈጠረው ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ ነው።
ከኹሉ በላይ
ደግሞ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክና ምሳሌ ፈጥሮታል (ዘፍ. 1፥26፤ መዝ. 8፥6)፤ እግዚአብሔርን ከሚመስልበት መልክና
ምሳሌ አንዱ ደግሞ ፍጥረትን ኹሉ እንዲገዛ ነው። ሰው ግን በኀጢአት ምክንያት ይህን የእግዚአብሔርን መልክና ምሳሌ ባበላሸ
ጊዜ፣ ያው እግዚአብሔር የማዳንን መንገድ በዘላለም ዕቅዱ ውስጥ ነደፈ። ንድፉም በክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በተሠራ ሥራ
ማዳንና መድኀኒትን ማዘጋጀት ኾነ!
እናም በዳግመኛው አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ ከኀጢአት ድነን አዲሱን ሰው እንለብስ ዘንድ ዕድል
ተሰጥቶናል፤ ፍጥረትን በመዋጀት ያዳነው ያው ጌታ ደግሞ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያድነን ዘንድ ዳግመኛ ይገለጣል፤ ባላመኑትና ርሱን
በሚቃወሙት ኹሉ ላይ በመፍረድም በጌትነቱ ድል ይነሣል።
በአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ ውስጥ ግን፣ የፍጥረት ዓላማ ግለሰቦች ኹሉ የራሳቸውን የተፈጥሮ መለኮትነት
እና ከአጽናፈ ሰማይ ጋር አንድ እንደሚኾኑ ማስተማር ዋነኛ ግቡ ነው። ይህ እንዲኾን፣ እንደ ዮጋና ማሰላሰልን፣ ሻማኒዝም ማለትም
ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር መሳተፍን፣ ሪኢንካርኔሽን ማለትም ያለፉት ሕይወቶች ዳግመኛ ነፍስ ዘርተው በዚኹ ምድር በብዙ ሕይወት ውስጥ
በሚያደርጉት ጉዞ፣ ወደ “እግዚአብሔር ንቃተ ኅሊና” የሚመራ የመንፈሳዊ የዝግመተ ለውጥ ሂደት መከተል አለባቸው። የመጨረሻ ዓላማውም
የአንድን ሰው የሕይወት ኃይል ወደ አጠቃላይ የጠፈር ንቃተ ኅሊና መመለስ ነው፣ ከሁሉም ኅልውና ጋር[ከእግዚአብሔር ጋር ጭምር]
አንድ መሆን ነው። ሎቱ ስብሐት!
እግዚአብሔር ግን፣
“… ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ… እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤
አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (1ጢሞ. 6፥15-16)።
ደግሞም፣
“ሁሉ ከእርሱና
በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ 11፥36)።
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment