የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አንድና ወጥ የኾነ የእምነት አቋም ወይም መርሕ የለውም። ነገር
ግን ከክርስትና፣ ከምሥራቃዊ ምስጢራዊነት፣ ሂንዱይዝም፣ ቡሂድዝም፣ ሜታፊዚክስ፣ ተፈጥሮአዊነት፣ ኰከብ ቈጠራ፣ አስማት ወይም ጥንቆላን
እና ከሳይንሳዊ ልቦለድ የተውጣጡ የተለያዩ ፅንሰ ዐሳቦችን እና ልምምዶችን በመጠቀም ወደ ሙሉ አቅም ለመድረስ መጣርን የሚያበረታታ
እንቅስቃሴ ነው። ኹሉም ቤተ እምነቶች ውስጥ ያለውን መልካም የተባሉትን ምግባራትና ልምምዶችን በመውሰድ የራሳቸው አድርገው ይጠቀማሉ።
አንድና ወጥ አስተምኅሮ የሌላቸው መኾኑ ብቻ ያይደለ፣ ከተደራጁ ሃይማኖቶች በተለየ፣ የአዲስ ዘመን መንፈሳዊነት መሥራች
ሰው፣ የተዋቀረ አመራር፣ ቋሚ አድራሻ ያለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በሁሉም ደጋፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ጽሑፎች የላቸውም።
እንደ ዋቄፈታ ወይም በጠቅላላው በዓለም ውስጥ እንዳሉት ባሕላዊ ሃይማኖቶች፣ ይህም የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ፣ ትምህርቱን በወጥነት
ለመተቸትና ምንጩን ለመመርመር አዳጋች ያደርገዋል። ይኹንና እንቅስቃሴው ከልምምዶቹና ከትምህርቶቹ የሚከተሉት በተደጋጋሚ ተጠቃሽ
ትምህርቶቹ ናቸው።
የእምነት መግለጫዎቻቸው ምንድር
ናቸው?
ከላይ እንደ ተናገርነው፣ ትምህርቶቻቸውንና ልምምዶቻቸውን ሰፍሮ ማስቀመጥ ጨርሶ የማይቻል ነው፤ ምክንያቱም ትምህርቶቻቸውና
ልምምዶቻቸው የተወሰደው ከብዙ አብያተ እምነቶችና ከአያሌ ባህሎች ውስጥ ነውና። ነገር ግን በተደጋጋሚ ከሚናገሯቸው እውነታዎች ተነስተን
የሚያምኑትን ትምህርቶቻቸውንና ልምምዶቻቸውን እንዲህ ማስቀመጥ እንችላለን፤
1.
ፍጥረተ ዓለሙ ኹሉም መለኮት ነው፣ መለኮትም ኹሉም ነው፤ እኛ ብቻ ሳንኾን
ፍጥረተ ዓለሙ በጠቅላላ መለኮት ነው ብለው ያምናሉ። ይህን በሌላ መንገድ ሲያብራሩት ኹላችን መለኮት ነን ወይም ወደ መለኮትነት
እንጨመራለን፣ ወይም የኹሉም መጨረሻ አንድ ነው፤ ሰው በተፈጥሮው መለኮታዊ ነው ወይም ሁሉም ነገሮች መለኮታዊ ናቸው። ሁሉ አንድ
ነው፤ ሁሉም እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የምንለው ግላዊ ያልሆነ ንቃተ ኅሊና እና ኃይል ነው በማለት ያምናሉ።
በነርሱ እምነት እግዚአብሔር እና መላለሙ(universe) በይዘታቸው
አንድ እንደ ኾኑ ያምናሉ። ከዚህም የተነሣ ብዝሃ አምላክነትን በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥሉስ አንድነትን ጨርሰው አይቀበሉም። ከዚህም
ባለፈ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አማኞች በእያንዳንዱ የአጽናፈ ሰማይ ክፍል ውስጥ፣ መለኮታዊ ኃይልና ችሎታ እንዳለ ያምናሉ። ከዚህም
ባሻገር ኃይልን ወይም መለኮታዊነትን ከአጽናፈ ሰማይ መልሶ ለማግኘት ከእያንዳንዱ የአጽናፈ ሰማይ ገጽታ ጋር መስማማትና መተባበር
አለብን ብለው ያምናሉ። ይህንም ለማድረግ ወደ ፊት የምንጠቅሳቸውን ልዩ ልዩ ልምምዶችን በማድረግም ይታወቃሉ።
2. በአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ አማኞች ዘንድ እውነት አንጻራዊት እንጂ ምልእት አይደለችም። በሌላ ንግግር በነርሱ እምነት
ፍጹም እውነት የለም። በዓለም ላይ ያሉት ኹሉም እምነቶች ትክክለኛና እውነተኞች ናቸው።
እንዲሁም እውነትን ከውስጥ ማለትም ከራሳችን ብቃትና ንቃት መፈለግ እንችላለን፤ ምክንያቱም ሰውም ኾነ ሌላው ፍጡር
በሂደት ወደ መለኮት ሙላት መድረስ ይችላልና። ከዚህም የተነሣ ሰዎችና ፍጡራን ወደ ፍጹም እውነት እንዳይደርሱ፣ እግዚአብሔር የሰው
ልጆች አብርሆት ጠላት ነው በማለት ያምናሉ። ክርስትና በዚህ ምክንያት በአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ እጅግ የተጠላ እምነት ነው፤ ምክንያቱም
ሰዎችን በዝቅተኛ አብርሆት ውስጥ የሚገዛ እምነት ነው ተብሎ ይታመናልና። እውነት አንጻራዊ ከመኾንዋም የተነሣ፣ በአዲሱ ትውልድ
እንቅስቃሴ ውስጥ መልካምና ክፉ የሚባል ነገር የለም።
ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ቃል፣ ስለ እግዚአብሔር ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፤
“ … ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ
አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና
አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም” (ሐ.ሥ. 17፥24-25)
“ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ
እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር[ነው] …” (ኢሳ. 45፥2)
እንግዲህ ኒው ኤጆች ሆይ፤
“ … ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ
ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን።”
አሜን።
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment