በባለፉት ክፍሎች ግቦቻቸውንና ዋና ዋና አስተምኅሮአቸውን ማየታችንን
እያስታወስን ዛሬም ቀጣዩን ዋና ዋና አስተምኅሮአቸውን እናነሳለን። የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አማኞች፦
3. ክርስቶስ አንድ “ዮጊ” ነው፤ ነገር ግን ከርሱም የሚበልጡና
የላቀ መገለጥ ያላቸው “ዮጊዎች” እንዳሉ ያምናሉ። ኢየሱስ ብሩህ አስተማሪ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ አልነበረም በማለት
ያስተማራሉ። ከዚሁ ጋ በተያያዘ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አማኙና አስተማሪው ኤልያስ ገብሩ(ዶ/ር) የተባለ ሰው፣ ራሱን ከእግዚአብሔር
ለማስተካከልና ኹሉም ነገር በውስጡ እንዳለ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች “ቦጫጭቆ በመስፋት” እንዲህ ይላል፣
“ … ፈጣሪ ውስጤ አለ፤ የርሱ ኃይል እኔ ጋ ይሠራል፤ … እኔና አብ አንድ እንደ ኾንን እነርሱም በእኛ አንድ ይኹኑ
ይላል፤ ክርስቶስ የእውነት እኔ ጋ ካለ ብዙ ነገር ማድረግ እንደምችል መጽሐፍ ቅዱስ ነው የነገረኝ። … ሰው ግን ይህንም ከዚህም
በላይ ማድረግ ትችላላችሁ ይላል። ሰው አቅም አለው፤ ይህ አቅም እንዳለው አውቆ የሚያደርግ ከኾነ እግዚአብሔር በርሱ እንደሚያደርግ ይረዳል። … መንፈስ ዛሬም ወደ [ሰዎች]
ይገባል፤ ስለዚህ ሰው [ኹሉን] ማድረግ ይችላል። …”
በርግጥ በክርስቶስ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያ
አይደለም። ከአርዮስ ቀጥሎ የተነሣው ኩሪንቱስ የተባለ መ’ና’ፍቅ “እስከ አኹን ወደ ምድር ከተላኩት 32 ኤዎኔሶች[1] መካከል ክርስቶስ 33ኛው ነው” በማለት አስተምሮአል።
4. በአዲሱ እምነት እንቅስቃሴ አስተምኅሮ የሚያድግ መገለጥ፤ የሚጨምር
አብርሆት፤ ያላበቃና ያልተገደበ የመንፈስ መነዳት እንዳለ ይታመናል። ይህን በተመለከተ ኤልያስ ገብሩ (ዶ/ር) እንዲህ ይላል፣
“... ሃይማኖት የሚያድግ ነገር ነው ስል፣ ትልቁ ምሳሌዬ ቅዱስ ያሬድ ነው፣ ቅዱስ ያሬድ ያመጣው
ቅድስና ከርሱ በፊት ያልነበረ ነው፤ ያ ብቻ በቂ ነው ብለው አባቶች ስላልተቀበሉት እግዚአብሔር ዛሬም አኹንም ያወራል፤ ይገልጣል።
ከእግዚአብሔር ከራሱ የሚያስወጣህ ካልሆነ አዲስ ነገርን ወደ ሕይወትህ ማምጣት እግዚአብሔር የሚጠላው ነገር አይደለም። … ቅዱስ
ያሬድ ያመጣው ነገር ኹሉ አዲስ ነበርና … እግዚአብሔር የሚናገረን ነገር በሙሴ፣ በጳውሎስ፣ በያሬድም ጊዜ ያበቃ አይደለም፤ አኹንም
አለ። …”።
በክርስትና ግን የመገለጦች ዳርቻ፣ የነቢያት ኹሉ ትንቢት መቋጫና
መደምደሚያ፣ የአበው ምሳሌ መከተቻና ማክተሚያ ክርስቶስ ነው። ሕልሞች፣ ራእያት፣ ትንቢታት፣ መገለጦች፣ ... ኸሉ በክርስቶስ ፍጻሜ
አጊኝተው፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ ኾኖአል። መጽሐፍ፣ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና
ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤”
(ዕብ. 1፥1-2) እንዲል።
5. የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ መዳንን የሚገልጥበት መንገድ፣ አንድ
ሰው ራሱን ለማወቅ በራሱ ላይ ማተኰር እንዳለበት፣ ራሱንም ማግኘት፣ ከመላለሙም ጋር አንድ መኾንና የራስን መለኮታዊነት ወይም አምላክነት
ማወቅ ከሚለው አስተምኅሮ ጋር የሚዛመድ ነው።
ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው ለመዳን ይህን አቅሙን በመጠቀም፣
በበጎ ሥራና በሪኢንካርኔሽን ሙሉ መዳን ማግኘት እንደሚቻል ያምናሉ። የራስን ጥንካሬ ማጐልበት፣ ዕውቀትን ማዳበርና መከታተል፣ ራስን
በጽኑ መገሰጽና “ክርስቶስ” ወደ ደረሰበት የላቀ ንቃተ ኅሊና መድረስም እንደሚቻል ያምናሉ። በእንቅስቃሴው አማኞች ዘንድ ሙሉ መዳንን
የፈጸመውና ፍጹም የኾነ የነቃ ኅሊናን የያዘ “ክርስቶስ” ነው ተብሎ ይታመናል።
6. የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ የሚያስተምረን እርካታን ለማግኘት
በራሳችን ውስጥ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዳለን ነው። ራሳችንን ለመምራት፣ ለመፈወስ እንዲሁም የራሳችንን ፍጻሜ ወይም ዕጣ ፈንታ
ለመፈፀም የሚያስችል ብቃትም በራሳችን ውስጥ እንዳለ ያምናሉ። በዚህም፣ ከመለኮት ጋር አንድነትን በመፍጠር ወደ እንቅስቃሴው የመጨረሻ
ግብ መድረስ ይቻላል።
ከዚኹ ጋር በተያያዘ በውስጣቸው ያለውን አዲስ ኃይልና አዲስ
መንፈሳዊነትን የሚያስተዋውቁና የሚያስተምሩ ከመኾናቸውም በላይ፣ በዚህ ውስጣዊ ኃይላቸው በመጠቀም አንድ ቦታ ተቀምጠው እስከ
300 ማይልስ ሄደው መመለስ ብሎም እስከዚያው ክበብ ያሉትን ነገሮች ማወቅ እንደሚችሉ ያምናሉ።
7. ጥፋትና ውድመት ጨርሶ እንዲነሣ አይፈልጉም፤ ይህን እንደ
“Negative Potential” ይመለከታሉ፤ ከዚህም የተነሣ ለሰው ዓይን ሳቢ የኾነውን ቊሳዊ ብልጥግናን እያንቆለጳጰሱ፣ ሰብዓዊ
ውድመትንና ማኅበረ ሰባዊ ቀውስና መፈናቀልን ግን ማስታወስ አይፈልጉም። ለምሳሌ፦ ተራብኩ የሚል ሰው ቢገጥማቸው፣ የተራብክ ነው
ያለህ አእምሮህ ነው እንጂ ዳቦና እንጀራ አለ፤ ስለዚህ ተርቤአለሁ አትበል ይሉታል፤ ከጦርነት የተፈናቀለ ሰው ቢገጥማቸው፣ ጦርነት
ጭንቅላትህ ውስጥ ነው እንጂ እኛ ጋ ሰላም ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ሰላም ጋር ተዛመድ ይሉታል፤ ልክ አንድ “መዝሙር”፣ “እኛ ቤት
ሰላም ነው” እንደሚለው።
እኒህ ዋና ዋና አስተምህሮአቸው ናቸው። አንድ ነገር ማስታወስ
ያስፈልገናል። የአዲስ ትውልድ እንቅስቃሴ ከብልጽግና ወንጌል አስተምህሮዎች ጋር ተመጋጋቢ ነው። ወደፊት ደግሞ በነዚህ ትምህርቶች
ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችንና ምላሾችን በመስጠት ትውልዱ ከዚህ ጥፋ‘ትና ዓመ‘ጽ ፈጽሞ እንዲጠነቀቅና እንዲጠበቅ እናሳስባለን።
በቀጣዩ ክፍል እስክንገናኝ ድረስ፣ ይህችን “ሕይወትህን አታባክናት”
(Don’t waste your life) በሚለው መጽሐፉ ላይ ጆን ፓይፐር የተናገረውን ምክር ማስቀመጥ እወዳለን፤ እንዲህ ይላል፦
“ …ለእኛም ይኹን ለማንኛውም ትውልድ ሊቀርብ የተገባው አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይኼ ነው፤ ምንም
ዓይነት ሕመም የሌለበት ሰማይ፣ በምድር ላይ የነበሩ፣ ያሉ የምትወዷቸው ጓደኞቻችሁ ሁሉ የሞሉበት ሰማይ፣ የምትወዷቸው የምግብ ዓይነቶች
በተትረፈረፈ መንገድ የሞሉበት ሰማይ፣ በሕይወት ዘመናችሁ ደስ ያሰኛችሁ የትርፍ ጊዜ ተግባራችሁ ኹሉ ያሉበት ሰማይ፣ ያያችኋቸው
ያላችኋቸው ልታዩ የምትጓጉላቸው አስደናቂ የተፈጥሮ ውብ ገጽታዎች የሚገኙበት ሰማይ፣ የቀመሳችሁት ያልቀመሳችሁት አካላዊ ደስታዎች
ሁሉ ያሉት ሰማይ፣ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ግጭት የማይገኝበት፤ ጦርነት የሌለበት፣ ሰላም የሰፈነበት፣ የተፈጥሮ አደጋዎች የማይከሰቱበት
ሰማይ ቢሰጣችሁ … ነገር ግን በዚያ ሰማይ ክርስቶስ ባይኖር ትሄዳላችሁ ወይ? ትረካላችሁ ወይ? እዚያ መኖር ትፈልጋላችሁ ወይ?
…”
ኢየሱስ የሌለበት የትኛውም ሕይወትና ቀና ጐዳና እርሱ የሞትና
የጥፋት መንገድ ነው!
ይቀጥላል …
This is so powerful and yet again so so true. The reality of what The Son of God did on the cross has been misinterpreted for so long. What is so sad just as you put it is that it's been done by those who portray themselves as true preachers and teachers.
ReplyDeleteThis a is a wake up call od all wake up calls. God bless you for your genuine?, sincere and above all scripture grounded exposition of the truth. I honestly couldn't get enough of it I am Blessed by this article. .tebarek. ..May God continue to guide you. ...