Friday, 5 December 2025

የታይታ አገልግሎት የለንም!

Please read in PDF

ሽልማታችን ሰማይ፤ ዋጋችን ኹሉን በዓይኑ በሚቆጣጠር ጌታ ዘንድ እንደ ኾነ አውቀንና አምነን፣ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው የተከተሉ የጽድቅ መናንያን፤ የቅዱስ ቃሉን ሰማዕታት፤ እንደ ጨው በምድር ዳርቻዎች ኹሉ የተበተኑ ሐዋርያትን፤ እውነትና ፍትሕን እንደ ውኃ ከፈሰሰ ሕይወት ጋር የሰጡ ነቢያትን፤ ታርዶ እንደ ተወራረደ መሥዋዕት ኹለንተናቸውን የሰጡ ሰባክያንን፤ የምድረ በዳውን ዋዕይ፣ የበረሃውን ሚራዥ ታግሠው ሳይናወጡ የተጉና የኖሩትን እንደ ደመና ዙሪያችን ዘወትር የከበቡንን “ሕያዋን ጻድቃንን” አሠረ ፍኖታቸውን የምንከተል የተሰቀለው መሲሕ ማኅበረ ሰብ ነን። እናም መሲሑ እንዲልቅ፤ መንግሥቱ እንዲሰፋ፤ ለቤተክርስቲያን ጥቅምና መታነጽ እንጂ ለታይታ የምናደርገው አንዳችም የለንም።

“... እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ጀማሪና ፍጹም አድራጊውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት የምንሮጥ፤ ጌታችን ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ያለውን ውርደትና ንቀት ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ እንደ ተቀመጠ እንዲኹ፣ በነፍሳችን ዝለን እንዳንደክም፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን የምናስብ አገልጋዮቹ ነን።”

ለታይታ የማናገለግለው ከፊታችን መሲሐችንና ወዳጃቻችን ከፊታችን ያስቀመጠልንን ደስታ በማስተዋል ነው። ዝለን ተስፋ የማንቆርጠው፣ የማንንኮታኮተውም ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን መሲሕ ዘወትር በማሰብ ነው። ለአገልግሎታችን፣ እግዚአብሔርን ለሚያስከብር አኗኗር አቻ የሌለው የክርስቶስ ሕይወት፤ ትምህርትና ሥራውን የምንከተል  የስቁዩና የድል ነሺው መሲሑ ባሪያዎች ነንና ለታይታ አንከተለውም። 

የሚከብድና የሚያደናቅፍ ነገርን እናስወገሰድ፤ ሩጫ ከልካይ ከባባድ ሸክሞች ወይም ልብሶች ወይም የተፈታ የጫማ ክር ያለን እንዳንደናቀፍ ዝቅ ብለን የጫማችንን ክር እናጠባብቀው፤ ክፉ ባልንጀርነት ውስጥ ያለን ወደ ቀናው መንገድ እንመለስ፤ ኩራትና ከሌላው እንደ ተሻልን በልባችን የምናስብ ... ትልቁ መሲሑ ብቻ ነው። ስለዚህ ከሚከብበን ኀጢአት ከሚያደናቅፈን ዝትት እንውጣና መሲሑን እየተመለከትን ጨክነን እንከተል።

መሲሑ መላ ዘመኑን የሮጠና አባቱን አክብሮ ያስከበረ ነው፤ አባቱ እንደሚያየው ብቻ ኖረ እንጂ ሰዎችን ለማስደሰት ጨርሶ አልኖረም። ታይታ በኢየሱስ ዘንድ ጥዩፍና  ግብዝነት ነው። እባካችኹ ለታይታ አታገልግሉ፤ በጽድቅና በቀናነት ብቻ አገልግሉ!

ጌታችና ተወዳጃችን ኢየሱስ የማንም ዕዳ የለበትም፤ ርሱ እንደሚያያችኹ አገልግሉ፤ “በመቅረዞቹም መካከል የሚመላለሰውና ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል የነበሩት” ድል ነሺው የታረደ በግ ያያችኋልና፣ ሰው አየኝ አላየኝ፤ ደገፈኝ አልደገፈኝ፤ እያላችኹ ጸጉራችኹን አትንጩ፤ ያያልና ትጉ! ደስታችኹንና የምትዘሩትን ዘር መከር፣ የነዶ መታቀፊያ ስፍራችሁ በጉ ባለበት በጽዮን ተራራ እንደ ኾነ አስቡና በርቱ!

ደግሜ እላለኹ፤ ለታይታ የሚኾን አገልግሎት አይኑራችኹ፤ አታድርጉትም።

ኢየሱስን በማይጠፋ ፍቅር ለምትወድዱ ኹሉ ምሕረትና ጸጋ ይብዛላችኹ፤ አሜን።


1 comment:

  1. life-changing article! thanks and GBU more

    ReplyDelete