መግቢያ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዋና
ዋና ከሚባሉት ትምህርቶችና አማኞች ሊጠመቁት ከሚገባው ጥምቀት አንዱ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። የብዙዎች ትኵረትና መሻት ያለው
የውኃ ጥምቀትና በየዓመቱ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የሚከበረውን የከተራ በዓልን እንጂ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እምብዛም ግንዛቤው
ያላቸው አይመስልም። ነገር ግን አስገዳጅ ከኾኑ መንፈሳዊ እውነቶች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቀ
እርሱ እውነተኛ አማኝ ወይም መንፈሳዊ አይደለም።
በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ ማን ነው?
ቅዱሳት ወንጌላት፣ “እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ[ክርስቶስ]
ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።” (ማቴ. 3፥11፤ ማር. 1፥8፤ ሉቃ. 3፥16፤ ዮሐ. 1፥33) በማለት
የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት የሚያጠምቀው ክርስቶስ እንደ ኾነ ይመሰክራሉ።
ይህም ጥምቀት በበዓለ ኀምሳ ዕለት በቤተ
ክርስቲያን ላይ ተፈጸመ፤ (ሐ.ሥ. 1፥5፤ 2፥1-4)። አማኞችም መንፈስ ቅዱሳዊ ጥምቀትን በክርስቶስ ሥራ የክርስቶስ አካል ከኾነችው
ከቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ በመኾናቸው በቤተ ክርስቲያን የወረደውን መንፈስ ቅዱስን ይካፈላሉ፤ (1ቆሮ. 12፥13፤ ቲቶ 3፥3-5)።
የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን እነማን ይጠመቃሉ?
የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት የሚጠመቁት፣ በክርስቶስ
ኢየሱስ የሚያምኑና በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ዳግመኛ የተወለዱት ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማያት ከማረጉ በፊትና
ወደ ምድር ዳርቻ በመሄድ ወንጌልን ከመመስከራቸው በፊት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፣ “ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ
ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።” (ሉቃ. 24፥49፤ ሐ.ሥ. 1፥5)። ስለዚህም በክርስቶስ በስሙ የሚያምኑ
ኹሉ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን ይጠመቃሉ።
እንዲሁም ኀጢአትን ፈጽመው የሚጠየፉ፣ መንፈስ
ቅዱስን በብዙ የሚናፍቁና የሚራቡ መንፈስ ቅዱስን ይመላሉ፤ መንፈስ ቅዱስን መራባችንን የምንገልጠው፣ እጅግ በጸሎት በመትጋት፣ በማምለክ፣
ቃሉን በመመስከርና በማወጅ ከቶውን ያላቋረጥን እንደ ኾን ነው።
መቼ ይፈጸማል?
በደቀ
መዛሙርቱ ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚከናወነው፣ ጌታችን ወደ ሰማያት ካረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደ ኾነ ተናግሮአል
(ሐ.ሥ. 1፥5)። አስቀድሞ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ነበር (ዮሐ. 20፥22)፤ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ
እንደ ገና የመንፈስ ቅዱስን ኀይል ሊለብሱ እንደሚገባቸውም ነገራቸው። ቆርነሌዎስም፣ ካመነና ዳግም ከተወለደ በኋላ ልክ እንደ
ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቀ (ሐ.ሥ. 11፥16-17)።
በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ
ለመኾኑ
ግን “በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማለት ምን ማለት ነው?” ብለን ብንጠይቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማለት በመንፈስ
ቅዱስ መሞላት እንደ ኾነ ይነግረናል፤ ስለዚህም ደቀ መዛሙርትና ሌሎችም ከጌታችን ኢየሱስ ዕርገት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቁ
ወይም በግልጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። እንኪያስ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ወይም ሲሞሉ ምን ያደርጋሉ? ብለን በድጋሚ
ብንጠይቅ፣መጽሐፍ ቅዱስ እኒህን እውነቶች ይነግረናል፣
1. ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ሲሞሉ በኀይልና
በድፍረት የመዳንና የትንሣኤውን ወንጌል ይመሰክራሉ፤ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።”
(ሐ.ሥ. 4፥31) እንዲል፣ በተጨማሪም (ሐ.ሥ. 4፥8፤ 9፥17-20 ይመልከቱ)። መንፈስ ቅዱስ ቅዱስን ያልተሞላ ሰው የመዳንን
ወንጌል በድፍረት ይናገር ዘንድ አይችልም።
2. አማኞች መንፈስ ቅዱስን ሲሞሉ ልሳንን
ይናገራሉ፤(ሐ.ሥ.
2፥4፤)። ልሳን በሌላ ቋንቋ መናገር ነው፤ ይህም ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽና አማኙን ለማነጽ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ሊነጋገር
ይሰጣል። ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ሲሰጥ ሁከትና ነውጥን መፍጠር አይገባም፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነውና ኹሉ በሥርዓት ሊኾን
ይገባል።
3. መንፈስ ቅዱስን የተሞላ
ሰው ኀጢአትንና ኀጢአተኝነትን ፈጽሞ ይጠየፋል። በተለይም መንፈስ ቅዱስን ከሚያሳዝንና ከፈቃዱ ተቃራኒ ከኾነ ከማናቸውም ኀጢአታዊ
ተግባር ይርቃል። እግዚአብሔር በመጨረሻ በክፋትና በርኩሰት ላይ የሚፈርደውን ፍርድ በትክክል ከማወቁም በዘለለ የእግዚአብሔርን ጽድቅ
አብዝቶ ይሻል፣
4. ክርስቶስን እጅግ በሚያከብር
ሕይወት ይመላለሳል፤ (ዮሐ. 16፥13፤ ሐ.ሥ. 4፥33)። ክርስቶስን በሚያከብር ሕይወት ለመመላለስ ግለ ብቃት አያስመካም፤ ሰው
በግለ ብቃቱ እግዚአብሔርን ማርካትና ማስደሰት አይችልምና፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ሲመላ ክርስቶስን ፍጹም በሚያስከብር ሕይወት
ይመላለሳል። እንዲሁም አንድ አማኝ መንፈስ ቅዱስ ሲመላ አያሌ ስጦታዎች በሕይወቱ ይፈስሳሉ።
ማጠቃለያ
የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፣ መንፈስ ቅዱስ እኛን ክርስቶስ ራስ ወደ ኾነበት አካሉ
የሚከትትበት እጅግ አስደናቂ ሥራ ነው። አንድ አማኝ ወደዚህ አካል ሲገባ፣ ኹለንተናው ፍጹም በኾነ መንገድ መሠራትና መዋብ፤ መቀደስ
ይጀምራል። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በማያቋርጥ ግንኙነትና ዕለት ዕለት በሚታደስ ሕይወትም ይመላለሳል፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲህ
ያለውን ሕይወት ያብዛልን፤ አሜን።
Amen. Praise be to our LORD SAVIOUR & redeemer who baptised us all in the body.
ReplyDeleteIt’s really are so so so much powerfull
ReplyDeleteThank you Jesus!..U are Blessed
ReplyDeleteክብር ምስጋና ለአምላካችን ለ እግዚአብሔር ይሁን ! አሜን !!!
ReplyDelete