ከሰሞኑ ዶክተር ገመቺስ እንዲህ ብሎአል፤
“ዳዊት ድሪምስ የወደቀውን የሰውን ሥነ ልቦና
ለማነሳሳት የሚተጋ ሰው እንጂ የአዲሱ ዘመን ዕሳቤ አራማጅ አይደለም።”
ስለ
አዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አማኞችና ተከታዮች በሰፊውና በተከታታይ መጻፋችን ይታወሳል። ዶ/ር ገመቺስ ፈጽሞ እንደ ተናገረው ሳይኾን፣
እነ ዳዊት ድሪምስ፣ አሸናፊ
ታዬ፣ ኤልያስ ገብሩ(ዶ/ር)፣ ዳግማዊት ክፍሌ፣ ነፃነት ዘነበ፣ ማንያዘዋል
እሸቱና ሌሎችም በአገራችን የትምህርቱና የልምምዱ ዋና አቀንቃኞች መኾናቸውን አንስተን ጽፈናል፤ ዛሬ ደግሞ ዶክተሩ፣
ስለ ዳዊት ድሪምስ የተናገረውን በጥቂቱ እንቃኝ።
ይህን ንግግሩን ሳስብና የኹለቱን ሰዎች መሻረክ ስመለከት፣ በራእይ 13 ላይ
ያሉት፣ የኹለቱ አውሬዎች ተዛምዶ ከፊቴ ድቅን ይላል። ፊተኛው አውሬ ከባሕር የሚወጣ ነው፤ ባሕር ደግሞ ነውጥ አያጣውም፤ ሞገድ
ይበዛበታል፤ ወጀቡ ብዙ ነው። መዋጊያ ቀንዶቹም ብዙ ናቸው። ዳዊት ድሪምስ ልክ ከባሕር የሚወጣውን አውሬ ይመስላል። ሞገደኛ ነው፤
ሲናገር “አንድን የኢትዮጵያ ብር ከአንድ ዶላር ጋር ለማስተካከል” የሚሳነው ነገር ያለ አይመስልም፤ ፖለቲካውንም፤ ኢኮኖሚውምን፤
ማኅበረ ሰብ ተኰር እሴቱንም … አቅኚና አስተካካይ ሲመስል መዋጊያ ቀንዶቹ አንድ ብቻ አይመስሉም። በልቡ ዓለሙ ኹሉ እየተከተለው
“ዝናውን የሚያደንቅለትና” በምድሪቱ ላይ ቅሪት ቅዱሳን ያሉ እንኳ አይመስለውም!
ኹለተኛው አውሬ ደግሞ የሚወጣው ከምድር ነው፤ ምድር የጸናች ናት፤ አልፎ አልፎ
ካልኾነ በቀር በመንቀጠቀጥ አትመታም፤ ብዙ ጊዜ በጽናትዋ ትታወቃለች። ኹለተኛውም አውሬ የረጋና ጽኑ ይመስላል፤ ግን መጽሐፍ እንደሚናገር፣
“ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።” (ራእ.
13፥12)። ከባሕር ከሚወጣው አውሬ ይልቅ ከምድር የሚወጣው አውሬ አደገኛነቱንና አታላይ መልቲነቱም ሲናገር፣ “የበግ ቀንዶችን
የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት” ይልና መልሶ ደግሞ፣ “እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር።” ይላል። ይህም ማለት እንደ ፊተኛው ከባሕር
እንደ ወጣው አውሬ ጠባይ ማለት ነው።
ኹለተኛው አውሬ ዶ/ር ገመቺስን ይመስላል፤ ልክ እንደ ኹለተኛው አውሬ የበግ
ቀንዶች አሉት፤ አማኝ ይመስላል፤ መንፈሳዊ ነኝ ይላል፤ ከእግዚአብሔር ቃል ይጠቅሳል፤ ግን የሚመራው ወደ ፊተኛው አውሬ ማለትም
ወደ ዳዊት ድሪምስ ነው፤ በበግ መሃል የሚሰግድ ተኩላ ማለት ይህ ነው። የዳዊት ድሪምስን ተከታዮችና ሌሎችም ዳዊትን እንዲከተሉ፣
መንገድም የሚመራው እንዲህ በማለት ይመስለኛል፤ “ከአንድ አምላክ አስተማሪዎች ይልቅ ባለ ብዙ አማልክት አስተማሪዎችን ተከተሉ፣ ከክርስቶስ የፀጋ ትምህርት ይልቅ የካርማ ሕግ ይበልጥ ይጠቅማችኋል፣ ከዘላለም
ሕይወትና ከመንግሥተ ሰማያት መልካም ጣዕም በላይ፣ የማያልቀው ሪኢንካርኔሽን ይሻላችኋል፤ በላይ በሰማይ ካለችው ከበጉ ከተማና ከበጉ እራት ይልቅ የኒርቫና ሐሴትና
ተድላ ይበልጣል።”[ጌታ ይገስጸው!]
ተወዳጆች ሆይ፤ መንፈሳዊ መስለው፤ ከጌታ ቃል እየጠቀሱ መንገድ ከሚያስቱ አንዳንዶች
እባካችሁ ራቁ፤ መጽሐፍ እንደሚል፣ “ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።” (1ዮሐ. 5፥21)

No comments:
Post a Comment