Wednesday 29 September 2021

ተሐድሶ ትርጉሙና ሕይወቱ!

 Please read in PDF

ተሐድሶ፣ “ሐደሰ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲኾን፣ ትርጕሙ “አዲስ አደረገ” የሚለውን ትርጕም ታሳቢ ያደርጋል። በተገብሮ (Passive) “ተሐድሰ” ከሚለው ቃል ደግሞ፣ “ተሐድሶ” የወጣ ሲኾን፣ ትርጕሙ “አዲስ ኾነ” ማለት ነው። ስለዚህም ስያሜው ድርጊትን እንጂ ተቋማዊነትን ወይም አደረጃጀትን ፈጽሞ አያመለክትም።


“ተሐድሶ” ድርጊትን ይመለከታል ካልን፣ ድርጊቱ የሚመሠረተው ባለ ነገር ላይ ወይም ያለን ነገር ታሳቢ ያደርጋል ማለት ነው። ይህንም በኹለት መልኩ ማየት እንችላለን።

1.   የሚጠበቅ፤ የሚፈለግ ነገር አለ፣

2.   የማይጠበቅ፤ የማይፈለግ ነገር አለ።

ተሐድሶአዊ ድርጊት እኒህ ኹለቱን ታሳቢ በማድረግ በገቢር ሲተረጐም፦

1.   የሚፈለግንና የእግዚአብሔር የኾነውን መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ከጠላት መከላከል፣ እንዳይጎዳ ተገቢውን ቅጥርን መቅጠርን ሲኾን፣

2.   እግዚአብሔር የማይፈልገውን ነገር ደግሞ እንዲወገድ፣ እንዲቆረጥ፣ እንዲገረዝ ማድረግንም ይመለከታል።

ይኸው ተሐድሶአዊ ድርጊት በተገብሮ ሲተረጐምም፣ እኒህን ኹለት ነገሮችን ገንዘብ ያደርጋል። እኒህም፦

1.   የእግዚአብሔር ኾኖ የሚፈለገውን ነገር ማጥበቅ፣ እንዲንከባከቡ፣ ከጠላት እንዲከላከሉ ማድረግ ሲያመለክት፣

2.   እግዚአብሔር የማይፈልገውን ነገር ፈጽሞ መወገዱን፣ መቆረጡን፣ መገረዙንም የሚያሳይ ወይም ማሳየትም ነው።

ይህን እውነት በትክክል ከተረዳን፣ ተሐድሶአዊ የቅዱስ ቃሉ ጎዳና የተስተካከለና የተቃና ይኾንልናል። ተሐድሶ ድርጊት ከኾነ፣ ከድርጊቱ በፊት ድርጊቱን ፈጻሚ አካል ማለትም የሰው ልጅ[አማኙ ደቀ መዝሙር]፣ በአዳሹ እግዚአብሔር መታደስ ይኖርበታል። እኛ በእግዚአብሔር ድርሻ ውስጥ የምንገባውና አብረን የምንሠራው፣ ታዳሽ[ዘወትር በቅዱስ ቃሉ የምንታነጽና የምንሠራ] መኾናችንን አምነን ስንቀርብና ራሳችንን ስናዘጋጅ ነው።

ሌላውና ትልቁ ነጥብ የማይፈለገውንና የእግዚአብሔር ያልኾነውን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ይወገድ ስንል፣ ቀድሞ ነገር የሚፈለገው እንዳይጠፋ በብርቱ መጠንቀቅ ይገባናል። ለምሳሌ፦ ተሐድሶ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠብቃል እንጂ አያድስም። እንዲሁ በእኛ ልብ ከክርስቶስ ውጭ የነገሠና የከበረ ነገር ካለ፣ ያንን በማስተማርና ዙፋኑን ለክርስቶስ ብቻ በማስለቀቅ ማደስ (ባዕዱን አካል ማስወገድ) ይገባል ማለት ነው።

ስለዚህ ተሐድሶ እንቅስቃሴ እንጂ ድርጅት አይደለም፤ እንቅስቃሴውን ደግሞ መሪው መንፈስ ቅዱስና ቃሉ ናቸው። በቃሉ መሠረትነት ላይ ቆመን፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የሚጠበቀውን ጠብቀን፤ የሚወገደውን ካላስወገድን አምልኮ ሊበላሽ፤ ደምግባቱንም ሊያጣ ይችላል። ገበሬ ተሐድሶ ለተክሉ እንዲያስፈልገው ሲያውቅ፣ በብልሃትና በጥበብ ከተክሉ አጠገብ ያለውን አረም ይነቅላል፤ ከዚያም ይኰተኩታል፤ ይንከባከባልም። ትምህርተ ሃይማኖትን ከሐራ ጥቃውያን ለመከላከል፣ ሥርዓተ አምልኮንም ለማስጠበቅ፣ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ለማደስና ወደ ነበረበት ክብሩ ለመመለስ፣ ቤተ ክርስቲያን ኹል ጊዜ በክርስቶስ ደም፣ ቃልና መንፈስ ልትታጠብ፤ ራስዋንም ልታጠራ ይገባታል።

አስቀድሞ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ አኹን ደግሞ “ሳይኾኑ ተሐድሶ ኾነው ሥራውን እየሠሩ ተሐድሶ አይደለንም በሚሉና ስሙን ጠልተው ሌላ ስም በሚሹ ወገኖች” ዘንድ፣ ቦታ ስተው ከተተረጐሙ ወይም ዓውድ ስተው ከተነገረላቸው ዓላማ ውጭ ከሚተረጐሙ ብዙ ቃላት መካከል አንዱ “ተሐድሶ” የሚለው ቃል ነው። አዎን፤ በብዙ ሰዎች ኅሊና፣ የማይጨበጥና አውሬያዊ መልክ እንዳለው ተደርጐ እንደ ተሳለው ሳይኾን፣ ተሐድሶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት ያለው እውነት ነው።

ይህ ያልገባው ሐዳሲ አይደለሁም ካለ፣ ሐዳሲ አይደለም፤ የገባውና የተቀበለ ግን ራሱ በክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት እያደሰ፣ እውናዊና ነባራዊ ተሐድሶን እንደ ቃሉ፣ በመንፈሱ ኃይል ያደርጋል፤ ደግሞም ጌታ ኢየሱስ በመንፈሱ፣ ቤተክርስቲያን አካሉን ዘወትር እስከ ሙሽርነትዋ ቀን ድረስ፣ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር እንዳይኾንባት ይኩላታል፤ ያድሳታል፤ ያስጌጣታል፤ ያስውባታል፤ ያቆነጃታል፤ አሜን።

1 comment: