Sunday, 22 June 2025

“በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን” (ገላ. 6፥16)

 Please read in PDF

መሲሐዊው የክርስቶስ መንግሥት ወንጌል ሰውና እግዚአብሔርን ብቻ ሳይኾን ሰውና ሰውን ወይም ጎረቤቱንም የማስታረቅ ዓላማ አለው። ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅቶ በመጥራት (ራእ. 5፥10) በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በሰላም እንዲኖሩ ማስቻል የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል ቀዳሚ ዓላማ ነው።

የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣትና የእግዚአብሔር አገዛዝ መመሥረት፣ እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ብቻ የገለጠው ዐሳብ ሳይኾን ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር ፍጥረትን እንደሚያድስና የሰው ልጆችን እንደሚታደግ ቃል ከመግባቱ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የዚህ የእግዚአብሔር ተስፋ መፈፀም ዋነኛው ምልክት ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ መጨረሻ ላይ፣ “በዚህ ሥርዓት ለሚሄዱ ሁሉ” በማለት፣ “በክርስቶስ ኢየሱስ መገለጥ በማመን አዲስ ፍጥረት ለኾኑ ኹሉ፣ በረከት ይኹን”  በማለት በታላቅ ባርኮት ይባርካል። ሐዋርያው አስቀድሞ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መኾን ማለት፣ በክርስቶስ በማመንና በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን መሞቱንና ከሙታን መካከል መነሣቱን ብቻ እንደ ኾነ ገልጦአል (ገላ. 1፥3-5)። በዚህ አለማመን፣ “ከክርስቶስ ተለይቶ ከጸጋው መውደቅ” እንደ ኾነም በግልጥ ተናግሮአል፤ (ገላ. 5፥4)።

በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት አዲስ በኾኑት ኹሉ ላይ፣ ሰላምና ምሕረት በእነርሱ ላይ ይሁን፤ አሜን። ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ፣ የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩትን እንዴት ባለ በጽኑ ቃል እንደ ተቃወመና እንደ ረገመ አንዘነጋም፤ ምክንያቱም እነርሱ፣ የሚያጣምሙት የክርስቶስን ወንጌል ብሎም፣ የገላትያ አማኞች ከተቀበሉት የተለየውን ወንጌል የሚሰብኩ ናቸው በማለት ገልጦአቸዋል፤ (1፥7፡ 9)፤ ሐዋርያው እኒህን ፍጹም ተቃውሞአል። ነገር ግን በመታዘዝና በመታመን እንደ ወንጌሉ ቃል በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የኾኑትን ይባርካል፤ ይመርቃል። ሲያመሰግናቸውም፣ እነዚህ በእምነት የአብርሃም ዘር የኾኑ የእግዚአብሔር እውነተኛ እስራኤል ናቸው ይላል።

ለ“እግዚአብሔር እስራኤል” የተሰጠው ባርኮት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተቋቋመውን አዲስ ቃል ኪዳን ለሚቀበሉ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሰላምና ምሕረት የሚያበስር ታላቅ ቸርነት ነው። ይህም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች፣ ከየትም ቢመጡ፣ ምንም ወይም ማንም ቢኾኑ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል መኾናቸውን አጽንዖት ይሰጣል።

በእግዚአብሔር እውነት በኾነው በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚመላለሱ ኹሉ፣ የታዘዘ ሠላምና ምሕረት፤ በረከትም አለ። እግዚአብሔር፣ ልጁ ክርስቶስን ባመኑት መካከል አንዳች ልዩነት አላደረገምና፣ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (3፥29) እንዲል።  በርግጥ “እስራኤል” የሚለው መጠሪያ የሚያገለግለው፣ በትውልድ የአብርሃም ዝርያና የእግዚአብሔር ሕዝብ በመኾን የቀደመው ኪዳን ተካፋይ ለኾኑት ብቻ ነበር፤ ነገር ግን “እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።” (3፥30) ተብሎ ተጽፎአልና፣ “ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።” (3፥9)። እኛም ከወንድማችን ሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ኾነን እንዲህ እንላለን፤ “ይህን ትእዛዝ በሚከተሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በኾነው እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይኹን። (ገላ. 6፥16 ዐመት) አሜን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment