Wednesday, 12 November 2025

የትውልድ ነቀርሳ - የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ክፍል - ፯

 Please read in PDF

4.    እውነት አንጻራዊ ናት፦ በአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተምህሮ መሠረት ፍጹም እውነት የለም፤ ምክንያቱም ኹሉም እምነቶች ትክክልና ትክክለኛ ናቸው። ለምሳሌ፦ በክርስትና አስተምኅሮ አንድ ሰው ከጋብቻ ውጭ የሚያደርገው ማናቸውም ሥነ ምግባራዊ ርኩሰት አመንዝራነት ነው፤ ለአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ግን ርኩሰት ሳይኾን ትክክል ነው። በጋብቻ ውስጥም፤ ከጋብቻ ውጭም የሚደረግ አመንዝራት እውነትና ውሸት ቢኾንም፣ ለነርሱ ግን ኹለቱም እውነት ነው።

ሰው የያዘውም የትኛውም አቋሙ ትክክልና እውነት ነው፤ ለአንዱ እውነት ኾኖ ለሌላው እውነት የማይኾን አመለካከት የለም። እውነት ግላዊ ወይም ግለሳባዊ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ወይም ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ወይም መንፈስ ቅዱስ የሚገልጠው እውነት አለ የሚለውን አስተምኅ  ሮ ጨርሰው አይቀበሉም። ይልቁን በራሳቸው በመሠረቱት መንፈሳዊ ልምምድና ዕውቀት ላይ ራሳቸው ባለሥልጣን እንደ ኾኑ ይገልጣሉ። የእያንዳንዱ ሰው ልምምድ እጅግ ትክክለኛ የሥልጣን ምንጭ እንደ ኾነ ያምናሉ። ለዚህም ነው፣ እግዚአብሔርነት በፍጥረተ ዓለሙ ባሉ ፍጥረታት ውስጥ መኖሩ(Pantheism) የሃይማኖቱ ዋልታና ማገሩ የነውና “እውነት በኹሉም ስፍራ አለች” ተብሎ የሚታመነው።


የእነርሱ እውነት የተቀዳው ከተለያዩ ባህሎች ተውጣጥተው፣ ከተለያዩ እምነቶችና ልምምዶችን ተዳቅለው፣ ከጥንታዊ ሃይማኖቶች ተዋሕዶ፣ ከምሥራቃዊ ፍልስፍናዎች ተቀንጭቦ በአንድነት የተፈጠረ “ግለ እውነት” ነው። ኹሉም እውነተኛ ደግሞም ኹሉም እውነተኛ ነው የሚለው ከዚህ የተነሣ ነው።

ክርስቶስ ብቻውን እውነት ነው የሚለውን ትምህርት አይቀበሉም፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ከእግዚአብሔርና ከቅዱስ ቃሉ በቀር ሌላ አንዳች እውነት እንደ ሌለ ፍጹም ይመሰክራሉ፤ ከቃሉ ውጭ ያለው ኹሉ ነገር ሐሰትና በከንቱ የተፈጠረ ተረት ነው፤ ክርስቶስና ቃሉ እውነት ነው፤ (መዝ. 119፥86፡ 142፡ 160፤ ዮሐ. 1፥14፤ 14፥6፤ 16፥7፤ 17፥17፤ ራእ. 16፥7፤ 19፥1-2)። ይህን እውነት በመካድና በመተው፣ ወደዚህ እንቅስቃሴ ገብታ ከብዙ ስቃይና ጥፋት በኋላ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመረዳት የተመለሰችው ቲና ኮልኒያክ ድንቅ ምስክር ናት፤ ምስክነቷንም በክርስቲያን ቱደይ ላይ ሰጥታለች፤ ሰውን ከሰው ትምህርት፣ ከሰው እስራትና ከሰይጣን መንፈሳዊ መሳይ የጥንቆላ ልምምድ የሚያወጣው እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።[1] 

5.    ራስ ተኰር “የሰው ወንጌል” ነው፦ እርካታን ለማግኘት በራሳችን ውስጥ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዳለ ያምናሉ። በተቃራኒው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ራስን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ በማተኰር የአጽናፈ ዓለሙ አስገኚና ፈጣሪ ላይ እንዲያተኵር ይጠይቃል (ኢያ. 1፥8)። ለእግዚአብሔር አለመውደቅና አለመሸነፍ፣ ለኹሉ ተሸናፊ፣ ወዳቂና ውዳቂ ያደርገናል።

የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ መንፈሳዊነት ተከታዮች የመጽሐፍ ቅዱሳዊ የውድቀት ትምህርቶችን፣ የሰውን ኃጢአትና ርኩሰት፣ የክርስቶስ መሥዋዕትን፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አስታራቂ አስፈላጊነትን እንደሚቃወሙ ባለፉት ጊዜያት ተመልክተናል። ከዚህ ባለፈ፣ የእንቅስቃሴውን በብዙዎች ዘንድ መወደድንና ተወዳጅነቱም እየጨመረ መምጣቱ ስንመለከት፣ የክርስቶስ ኢየሱስን መምጣት በቅርቡ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር አምላክ በመግቦቱ ካልረዳን በቀር፣ የማኅበረ ሰባችን በሥነ ምግባር በጥልቀትና በስፋት እየዘቀጠ መሄድን በግልጥ አመላካች ነው።

በጥልቅ ድንቁርና የሚኖር፣ ድህነቱ ሥር የሰደደ፣ በዘረኝነት የሚተላለቅና የሚጠላላ፣ ጦርነትን በየጥቂት ዐመታት ውስጥ ዘይቤው ያደረገ፣ ስንፍናና በአቋራጭ መበልጸግ በግልጥ የማይነቅፍ፣ ዝሙትና ትዳር መፍረስ እያየለ የመጣበት … ትውልድ መካከል ተቀምጠን፣ “ኹሉ ደህና ነው” ማለት መጀመር ፍጹም ተላላነትና ራስን መሸንገል ነው። በርግጥ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነት ተወድዶ እውነትና ፍትሕ ተረግጦአል።

የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ፣ “ሰው በተፈጥሮው መለኮታዊ ነው ወይም ኹሉም ነገሮች መለኮታዊ ናቸው” ከማለቱ ባሻገር፣ ሰው ኹለንተናዊ አቅም በውስጡ አለው ቢልም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” (ኤር. 17፥9)፣ በሌላ ስፍራም እንኳንስ ኹሉን ማድረግ የሚችል አቅም ሊኖረው፣ ከኀጢአት የተነሣ ሰዎች ኹሉ “በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል” (ሮሜ 3፥12) ብሎ በግልጥ ይናገራል

ከዚህም የተነሣ ያለ እግዚአብሔር ሰው ኹሉ እርባና ቢስና ፍጹም ከንቱ ነው። ያለ ሸክላ ሠሪ ሸክላው ምንም እንደ ኾነ እንዲኹ፣ ሸክላ የኾነውን የሰውን ልጅ፣ ሸክላ ሠሪው እግዚአብሔር ካልረዳው በቀር ምንምና ከንቱ ነው! እንዲያውም የጌታ ቃል በግልጥ፣

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው።” (ኤር. 17፥5)

የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥” (2ቆሮ. 10፥5)፡፡

ይቀጥላል …



[1] Tina Kolniakhttps://www.christianitytoday.com/2023/04/tina-kolniak-new-age-spiritual-danger-jesus

1 comment: