Sunday 17 May 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፬)

Please read in PDF

    3.  የእግዚአብሔርን ቊጣና ፍርድ አይናገሩም፦ ዓይን ያወጡ ሃሳውያን አገልጋዮች ብቻ ሳይኾኑ፣ በአከባቢያችን ያሉ አንዳንድ ለቀቅተኛ እንኳ፣ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ብቻ ማውራት አይበቃምን?” ሲሉ፣ በተደጋጋሚ እንሰማቸዋለን። ነገር ግን ከተነገረውና በግልጥ ከተቀመጠው ከእግዚአብሔር ዐሳብ መራቅ አደጋ አለው፤ ደግሞም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና አይሻሬነትን ማቃለል ነው።


   የእግዚአብሔር ቊጣና ፍርድ በኀጢአት ላይ የነደደ ነው፤ ኹላችንም በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ከማመናችን በፊት፣ “እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቊጣ ልጆች ነበርን።” (ኤፌ. 2፥2)፤ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።”፣ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3፥18፡ 36)። ሰው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰይጣንን፣ የራሱን መንገድ በመከተሉ ምክንያትና የእግዚአብሔርን ፍቅር በመግፋቱ ምክንያት፣ እንደ ሌሎቹ ማለትም እግዚአብሔርን እንደማያውቁት ከቊጣው በታች ኾነ።

   እግዚአብሔርን በማያምኑት ላይ ቊጣው ዘወትር የነደደ ነው፤ አላመኑበትምና እግዚአብሔር ለዘላለም ያጠፋቸዋል፤ ሰዎች ሊመጣ ካለው ቊጣ እንዲያመልጡ፣ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነት መንገድ ሰዎችን አስጠንቅቆአል፤ አዲሱ ኪዳን ሊከፈት ባለ በዋዜማው ላይ የተሰበከው፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የጌታ ኢየሱስ ስብከት፣ “ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” (ማቴ. 3፥1፤ ማር. 1፥14-15) የሚል ነበር። ስብከቱ ኹሉንም ያማከለ ነበር፤ እስራኤልን ማለትም በቀደመው ኪዳን ውስጥ የነበረችውንም ያካትት ነበር፤ “በወንጌልም እመኑ” የተባለው፣ የምንታመንበት ወንጌል ክርስቶስ ኢየሱስ የመጣው ለኹሉ ነውና።

   በብሉይ ኪዳን እንኳ እግዚአብሔር፣ ሕዝቡ ራሳቸው ከቊጣውና ከፍርዱ ይድኑ ዘንድ በተደጋጋሚ፣ በነቢያት አማካይነት መልእክት መላኩን እናስተውላለን፤ “በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ። … ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።” (መዝ. 95፥8፡ 11፤ ኢያ. 23፥16)፤ በዮሐንስ ወንጌል እንደ ተመለከትነው ደግሞ በልጁ የማያምኑ ኹሉ ደግሞ ሕይወትን አያዩም፤ ደግሞም የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ይኖራል። በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣትም፣ በተገለጠው አዳኝ ያላመኑ ኹሉ፣ የእግዚአብሔር ቊጣ ይነድባቸዋል፤ “የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።” (ራእ. 6፥15-17)።

  አዲስ ኪዳን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አለማመንና በኀጢአተኝነት ጸንቶ መኖር፣ የእግዚአብሔር ፍርድና ቊጣ እንዳለበትና እንደሚያስከትል በግልጥ ያስተምራል። የስህተት መምህራት ግን ይህን የተገለጠና በብዙ የተብራራውን የእግዚአብሔር ፍርድና ቊጣ ፈጽሞ አያስተምሩም፤ ምክንያቱም እነርሱም ራሳቸው በቊጣው የተዋጡና የተከበቡ ናቸውና። ልባቸውና ነፍሳቸው በሚሠሩት የዓመጻ ሥራ ደንዝዘዋልና፣ ቊጣውን ማስተዋል አይችሉም።

  ኹላችንም በፊቱ እንቆም ዘንድ አለን፤ “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።” (2ቆሮ. 5፥10)። እግዚአብሔር ሳያዳላ እያንዳንዱ ሥራችንን ወደ ፍርድ ያወጣዋል፤ “እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።” (ሮሜ 14፥12)። ፍርዱ አስፈሪና በፊቱ ማፈርና የዋጋ መቃጠልም እንደሚኖር የሚያሳይ ነው፤ (1ዮሐ. 2፥28፤ 1ቆሮ. 3፥13)። ስለዚህም የስህተት መምህራን ይህን አስፈሪ ፍርድ መናገርን አይደፍሩም፤ ይልቁን ተከታዮቻቸውን ያባብላሉ እንጂ።

   በእግዚአብሔር ፊት፤ የተደበቀው ምግባራችን፣ ጠባያችን (ሮሜ. 2፥5-11፡ 16)፣ ንግግራችን (ማቴ. 12፥36)፣ ዐሳባችን (ማቴ. 5፥22፤ 1ቆሮ. 4፥5)፣ በጐ ምግባራችንና (ኤፌ. 6፥8) ሌሎችም ታማኝ የኾንባቸውና ያልኾንባቸው ተግባራት፣ ዐሳቦች፣ ንግግሮች፣ አገልግሎታችን፣ ሥራዎቻችን ኹሉ በቁጣው ወይም በፍርዱ ፊት ይቀርባሉ። ንስሐ በመግባት በልጁ በማመን ካልተመለስን በቀር ከኩነኔው ማምለጥ አንችልም፤ (ሮሜ 8፥1)።

   አማኞች ይህን ታላቅና አስፈሪ ፍርድ አይቀሬነቱን በማመን፣ እግዚአብሔርን እጅግ ሊፈሩ ይገባቸዋል፤ እግዚአብሔር በልጁ ያዳነን ውድ አባታችን ነው፤ ደግሞም እርሱ እንደሚወደውና እንደ ፈቃዱ ብቻ የምንገዛለት ታላቅ አምላካችንም ነው፤ “እንግዲህ ኹሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል።” (2ጴጥ. 3፥11-12) እንዲል፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት በመጽናት መምጫውን ልናፈጥን ይገባናል።

    ቊጣውና ፍርዱ ጽድቅና ፍትሕ ማረጋገጫ ናቸው፤ የስህተት መምህራን ግን በቁልምጫ ቃል አባባዮች፣ እንደ ተኩላ አስመሳዮች፣ ጣፋጭ ምግቦችን ብቻ በማቅረብ፤ ለሥጋ ደስ የሚያሰኘውን በመናገር በሰፊው መንገድ ተከታዮቻቸውን የሚነዱ እንጂ፣ በአንድም ነገር እንኳ፣ ኹሉ ነገራቸው በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ የሚቀርብና ደግሞም የእግዚአብሔር ቁጣ በኀጢአት እንደ ነደደ መናገርን ወይም መስበክን ፈጽሞ አይሹም፤ አይፈልጉምም። አማኞች ሆይ፤ አምላካችን እኛን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን” ብሎ የሚወስድበት ቀን አለው፤ እርሱም ቀን የሠርጋችን ቀን ነው፤ ላላመኑትና በኀጢአት ጸንተው ለኖሩት ግን ያ ቀን፤ የፍርሃትና የድንጋጤ ቀን ነው፤ እናም ይህን ቀን በመጠባበቅና “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤” (1ጴጥ. 4፥7-8) እንዲል፣ በእውነትኛ መንፈሳዊነት ጸንተን ልንኖር እንዲገባን ማስተዋል አለብን።

   በክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሠላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment