Friday, 8 May 2020

የሐሰት መምህራን የማይነኳቸው ርእሶች (ክፍል ፪)

Please read in PDf

·        ኀጢአት፦ በስህተት መምህራን ዘንድ ትርጉማቸው ከተበላሹ ወይም እንደ ገና ከተተረጐሙት መካከል፣ ኀጢአት አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኀጢአትን በማያሻማ ትርጉም፣ “የአንድ ሰው አለመታዘዝ” (ዘፍ. 3፥17፤ ሮሜ 5፥12፡ 15፡ 18፡ 19)፣ ከእግዚአብሔር ክብር መጉደል ወይም እግዚአብሔር ወዳሰበልን እውነተኛ ግብና ክብር አለመድረስ (ሮሜ 3፥23)፣ በራስ መንገድና ዝንባሌ መሄድ (ኢሳ. 53፥6)፣ ማመጽ (1ዮሐ. 3፥4) የሚሉና በሌሎችም ትርጉሞች በግልጥ ተርጉሞት እንመለከታለን።


   የስህተት መምህራን ግን፣ ይህን ትርጉም ኾን ብለው ሲያምታቱ ወይም መልሰው በሌላ ትርጉም ሲተኩ እንመለከታለን፤ ለምሳሌ፦ በአገራችንም ኾነ በውጭው ያሉ ኹሉም የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን፣ ለኀጢአት የሰጡት ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተቃራኒውን ትርጉም ነው። ትርጉሙም፣ አንድ ኀጢአተኛ የሚባለው ድኻ በመኾኑና በመታመሙ እንደ ኾነ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። በእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ዘንድ ዝሙት ወይም ግድያ ወይም አንዲት ሴተኛ አዳሪ ገላዋን ሽጣ የምታመጣው ገንዘብ ወይም ግብረ ሰዶማዊነት በራሱ ኀጢአት አይደለም።

   [ሐዋርያ?] ዘላለም ጌታቸው የሚባለው ሰው፣ በትዕግስቱ የተመሰከረለትን ኢዮብን፣ በጸያፍ ስድብ ለመሳደብ ያበቃው፣ የኀጢአት ትርጉም ስለተዛባበት ወይም ኀጢአትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በተቃርኖ በመተርጎሙ ነው፤ ምክንያቱም ኢዮብ በቁስል ለመመታቱ ኀጢአቱ እንደ ኾነ በግልጥ ሲናገር እንሰማዋለንና። ለእውነት ቃል አማኞች፣ አለመታመምና ድኃ አለመኾን መዳን ሲኾን ተቃራኒው ግን ኀጢአት ነው።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዐሳብ፣ የስህተት መምህራን ኀጢአትን ለመጠየፍ አንዳች መንፈሳዊ ብቃት የላቸውም፤ ለዚህም ነው፣ የሐሰት መምህራን የተገለጠ ኀጢአት ባለበት፣ ኀጢአተኝነትንና ፍርድን ከመናገር ይልቅ፣ ኹሉ ሰላም እንደ ኾነና ችግር እንደ ሌለ ሲናገሩ የሚስተዋለው።  በሐሰት ነቢያት በብዙ ነፍሱ የተሳቀየችው ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ይላል፦

   የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ እግዚአብሔር፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። (ኤር. 23፥16-17)

    በኤርምያስ ዘመን፣ አብዛኛው ነቢያት ሐሰተኞች ነበሩ፤ ትንቢቱንም ከራሳቸው እንጂ ከእግዚአብሔር ሰምተው የሚናገሩት የላቸውም፤ የሰው ልጅ ዝንባሌው በእግዚአብሔር የተበላሸ ነው፤ ራሱ ኤርምያስም እንደሚናገረው፣ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” (ኤር. 17፥9)። እንግዲህ እንዲህ ካለው ሰው፣ ምን ዓይነት ነገር ሊፈልቅ እንደሚችል ማስተዋል አያዳግትም፤ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም ካልተቀበለ ምንም የለውም፤ ያልተቀበለውን ለመስጠት ካሰበ፣ የሚሰጠው ዓመጽና ስህተት ብቻ ነው፤ እንደ ስህተት መምህራን።

   ከሰላሙ እግዚአብሔር መልእክትን ሳይቀበሉ፣ በዓመጽና በኃጢአት የተመላውን ዓለም ሰላምና ቅን ነው ይላሉ፤ ይህ የዘወትር ተግባራቸው ነው፤ የልብ እልኸኝነት በተደጋጋሚ ለተነገረው ለእግዚአብሔር ቃል፣ ይሁንታ አለመስጠት፣ አለመታዘዝ፣ ወደ ጣዖት ልብን ማዘንበልን የሚያመለክት ነው። ለራሳቸው ስተው ለማሳት እንዲመቻቸው፣ የዓመጽና ያለመታዘዝ መንገዳቸውን ሳይጠየፉ ሰላም ነው፤ ደህና ነው ይላሉ፤ ግን ሰላምም ደህንነትም የለም፤ (ኤር. 6፥14፤ 8፥11፤ 14፥13፤ 28፥8፤ ኢሳ. 48፥22፤ 57፥21)።

   ዘመናችን የቀደመውን የኤርምያስን ዘመን ይመስላል፤ የሐሰት ነቢያት ፈልተዋል፤ ተርመስምሰዋል፤ የዚያኑ ያህል ዓመጽና ክፋት አይሎአል፤ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ሳትቀር እንደ ዘረኝነትና ግብረ ሰዶማዊነት ባለ ኀጢአት ተመርዛለች፤ ነገር ግን ነቢያቶች ነን ያሉቱ፣ ከሰላምና ከብልጥግና በቀር፣ ስለ ኀጢአትና ፍርድ አንዳችም ፍርድ ሲናገሩ አንሰማም፤ ኀጢአትን ስለመጠየፍ ሲናገሩ አንሰማቸውም።  ክፉና ሐሰተኛ ነቢያትን በዚህ እናውቃቸዋለን፤ ኀጢአትን ተጠይፋችሁ ስትናገሩ ደግሞ፣ “ፍቅር አልባ ናችሁ” የሚል ክሳቸው ደግሞ አይሎ ከተከታዮቻቸው ይሰማል፤ ከክፉዎች መጠበቅ ይኹንላችሁ፤ አሜን።
ይቀጥላል …


1 comment:

  1. ዘመናችን የቀደመውን የኤርምያስን ዘመን ይመስላል፤ የሐሰት ነቢያት ፈልተዋል፤ ተርመስምሰዋል፤ የዚያኑ ያህል ዓመጽና ክፋት አይሎአል፤ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ሳትቀር እንደ ዘረኝነትና ግብረ ሰዶማዊነት ባለ ኀጢአት ተመርዛለች፤ ነገር ግን ነቢያቶች ነን ያሉቱ፣ ከሰላምና ከብልጥግና በቀር፣ ስለ ኀጢአትና ፍርድ አንዳችም ፍርድ ሲናገሩ አንሰማም፤ ኀጢአትን ስለመጠየፍ ሲናገሩ አንሰማቸውም። Melkam aytehal

    ReplyDelete